Tuesday, March 5, 2013

የሰብዓዊ መብት ሊጉ የዩኒቨርሲቲው ውሳኔ ፖለቲካዊና ዘረኝነት ላይ ያነጣጠረ ነው አለ።


የካቲት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ሊግ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረን ግጭት ተከትሎ 10 የኦሮሞ ተወላጆች ከትምህርታቸው እንዲታገዱ መደረጋቸውን አጥብቆ አወገዘ።
የሰብዓዊ መብት ሊጉ ከትምርታቸው የታገዱትን ተማሪዎች ፎቶ አስደግፎ ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው የታገዱት  የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተናቸውን አጠናቅቀው የሁለት ሳምንት እረፍት ወስደው ከተመለሱ በሁዋላ ነው።
ሊጉ ከውስጥ የደረሱትን መረጃዎች ዋቢ አድርጎ እንደገለጸው ይህ በግልጽ ፖለቲካዊ የሆነውና ዘረኝነት ላይ ያነጣጠረው ውሳኔ የተላለፈው "ዲሲፕሊን ኮሚቴ" ተብሎ በሚጠራው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አካል ሲሆን፤ኮሚቴው ለዚህ ውሳኔ ምክንያት የሆነውም  ባለፈው ጥር ወር በኦሮሞና በትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል  የተፈጠረው ግጭት ነው።
በሁለቱ ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል ግጭቱ ሊፈጠር የቻለውም ጥቂት የትግራይ ተወላጅ የ ኦሮሞ ብሄረሰብን አስመልክቶ ተገቢ ያልሆነና ቆስቋሽ ጽሁፍ ጽፈው በመለጠፋቸው ምክንያት እንደሆነ ማረጋገጡን ሊጉ አውስቷል።
ይህን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በግጭቱ ሳቢያ ከ10 በሚበልጡ ተማሪዎች ላይ የ እስራት፣የግርፋትና የድብደባ እርምጃ መወሰዱን፤ ከታሰሩት መካከል ብዙዎቹ የ ኦሮሞ ተወላጆች እንደሆኑ ይፋ ማድረጉንም ሊጉ አስታውሷል።
በግጭቱ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ የተደረጉት አስሩም ተማሪዎች ኦሮሞዎች መሆናቸውን እና ከመካከላቸው አንዷ ሴት መሆኗን ያመለከተው ሊጉ፤ሁሉም ለ አንድ ወር ያህል ታስረው በዋስ ከተለቀቁ በሁዋላ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እንደነበር ጠቅሷል።
ከትምህርታቸው የታገዱት የኦሮሞ ተማሪዎች ከወለጋ ነቀምት የመጣው የ 3ኛ ዓመት ተማሪ ታደለ ታረቀኝ፣ ከደቡብ ሸዋ ኦሮሚያ የመጣው የ3ኛ ዓመት ተማሪ አበጀ ቱጂ ጫላ፣የ 4ኛ ዓመቱ ተማሪ ገመቹ ደለቶ ዳፎ፣የ 4ኛ ዓመት ተማሪ መልካሙ ሙሉጌታ፣የ 3ኛ ዓመት ተማሪ ፈቃዱ መሰራ፣ የ4ኛ ዓመቷ ሴት ተማሪ አዲስ ጋቴራ ያደሳ፣የ 4ኛ ዓመቱ ተማሪ በቃሉ ስዩም ተሻለ፣የ3ኛ ዓመቱ ተማሪ ቀጀላ አድማሱ ደሬሳ፣የ 2ኛ ኣመት ተማሪው ኢሳያስ ኢታና እና የ 4ኛ ዓመት ተማሪው አራርሳ ዋቅቶላ ኦልጅራ ናቸው።
ግጭቱን ከቀሰቀሱትም ሆነ በግጭቱ ከተሳተፉት የትግራይ ተወላጆች አንድም ተማሪ ላይ እርምጃ አለመወሰ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተብየው ውሳኔ በግልጽ ፖለቲካዊና ዘር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን እንደሚያሳይ የሰብዓዊ መብት ሊጉ አመልክቷል።
ይህ ውሳኔ ከሰብዓዊ መብት ሊጉ ባሻገር ብዙዎችን ያስገረመ እና  ጥቂት በማይባሉም ታዛቢዎች ዘንድ፦<<በ እርግጥም ይህች አገር የማናት?>>የሚልን ጥያቄ ያጫረ  ሆኗል።

No comments:

Post a Comment