Saturday, March 16, 2013

ዛሬ በሻሸመኔ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ድብደባ


ዛሬ በሻሸመኔ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ድብደባ “ፈስቢር” እንደሚከተለው ዘግባዋለች፡፡ ዛሬ ጁምዓ 06/07/2005 “ድምፃችን ይሰማ፤ በሁሉም ከተማ” በሚል መርሃ ግብር መሰረት ልክ እንደተቀሩት 44 ከተሞች ሁሉ፤ የሻሸመኔ ሙስሊምም የአሚሮቻችንን ትእዛዝ ተቀብሎ ገና ከማለዳው ጀምሮ ነበር ወደ አል-ሂከም መስጂድ የተመመው፡፡ የጁምዓ ሰላት ተሰግዶ እንዳበቃም፤ ህዝቡ ሳምንታዊውን ሰላማዊ ተቃውሞውን ጀመረ፡፡ የ”ፈስቢር” ሪፖርተር እንዳደረሰን ከሆነ፤ በዛሬው ተቃውሞ ላይ በርካታ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡ ከነሱም መካከል ድምፃችን ይሰማ፤ መሃይም አይመራንም፤ አሸባሪ አይደለንም፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የ”ፈስቢር” ሪፖርተር ከስፍራው ሆኖ በዘገበው መሰረት፤ ሙስሊሙ ድምፁን በማሰማት ላይ እያለ፤ የኦሮሚያ ፖሊስና የፌደራል ፖሊሶች፤ ከአድማ በታኝ ፖሊሶች ጋር በመሆን ወደ መስጂዱ የሚያዳርሱትን መንገዶች በሁሉም አቅጣጫዎች ዘግተው ሲያበቁ ሙስሊሙን መፈናፈኛ በማሳጣት ከመስጂድ ውጪ የነበረውን ሰላማዊውን ሙስሊም መደብደብ ጀመሩ፡፡ የከተማውንም ህዝብ ረበሹት!!! አሸበሩትም!!! ፖሊሶቹ ከመስጂዱ ቅጥር ግቢ ውጪ የነበረውን ሰው በሙሉ ደብድበው ከፊሉን ደግሞ አፍሰው ካባረሩ ወዲያ መስጂዱ ውስጥ የነበረው ሰው እንዳይወጣ በማሰብ፤ የመስጂዱን ዋናውን በር በምእመናኑ ላይ ዘጉበት፡፡ ይህን ተከትሎም ህዝቡ ተቃውሞውን በተክቢራ ቀጠለ፡፡ ፖሊሶቹም ወደ መስጂዱ ቅጥር ግቢ ቢገቡም ህዝቡ ተክቢራውን አላቋረጠም፡፡ ፖሊሶቹም በሰላም ከመሰጂድ ውጡ በሚል በያዙት የድምፅ ማጉያ ጥሪ ሲያሰሙ ወደ ስምንት የሚጠጉ ሰዎች እሺ ብለው ቢወጡም፤ እነዚህን ሰዎች ይዘው በመደብደብ መኪና ላይ ጭነዋቸው ሲሄዱ ማየቱን የ”ፈስቢር” ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ ግቢው ውስጥ የነበረው ሙስሊም ከፖሊሶቹ ዱላ ለመሸሽ ሲል ወደ ዋናው መስጂድ ውስጥ ተጨናንቆና ተጣቦ ገብቶ የተቀመጠ ሲሆን፤ እዚህጋ የኢማሙ ታላቅ ስራ ሳይደነቅ አይታለፍም፡፡ በመጀመሪያ ኢማሙ ህዝቡ ወደ መሰጂድ እንዲገባ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የማረጋጋት ስራ ሰርተዋል፡፡ በመቀጠልም ኢማሙ እጅግ በተረጋጋ መንፈስ ዱዓ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን፤ ህዝቡም ዱዓውን ተቀምጦ አሚን በማለት መቀበል ጀምሯል፡፡ ፖሊሶቹም በቅርብ ርቀት ሆነው በያዙት ካሜራ ለመቅረፅ ቢሞክሩም፤ ህዝቡ መስጂድ ውስጥ ገብቶ በሩን ስለዘጋው ሳይሳካላቸው መቅረቱን የ”ፈስቢር” ሪፖርተር ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ፖሊሶቹ አካባቢውን ለቀው የሄዱ ለመምሰል ሁለት ጊዜ መስጂድ ውስጥ ካለው ህዝብ አይን ለመሰወር ቢሞክሩም፤ ህዝቡ ግን ቀድሞ ስለነቃባቸው ከመስጂዱ አልወጣም ነበር፡፡ በዚህም ተስፋ የቆረጡት ፖሊሶች ከቀኑ 8፡45 ገደማ አካባቢውን ለቀው ሄደዋል፡፡ በዛሬው የሻሸመኔ ተቃውሞ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ፤ መስጂድ ውስጥ አንድ የመንግስት ሰላይ (ሲቪል) ስራውን ሲሰራ በህዘቡ ይያዛል፤ ከዚያም የመስጂዱ ኢማም ማንም እንዳይነካው ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ ምናልባትም ከመስጂዱ እንዲወጣ ከተፈቀደለት፤ በፖሊሶቹ አረመኔያዊ ተግባር በመበሳጨት ስሜታዊ የሆኑ ሰዎች እርምጃ እንዳይወስዱበት በመስጋት፤ ሰላዩ በመስጂዱ ውስጥ እንደውም ኹጥባ በሚደረግበት ሚንበር (መድረክ) ላይ በክብር እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ይህም ሙስሊሙ በሰላማዊነቱና በሰላም ወዳድነቱ ረገድ ላይ ምን ያህል መንግስትን ጥሶ መሄዱን የሚያሳይ ታላቅ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ነው እንግዲህ አሸባሪ ተብሎ እንደከብት የትም የሚደበደበውና የሚገደለው!!!አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ለ”ፈስቢር” ሪፖርተር እንደገለፁት ከሆነ፤ መንግስት ዛሬ የኀይል ተግባር የወሰደበት ምክንያት፤ በትላንትናው እለት የከተማዋን የመስጂድ ኢማሞች በወቅታዊው ጉዳይ ላይ እንነጋገር በሚል መንግስት የጠራቸው ቢሆንም፤ አንድም የመስጂድ ኢማም ጥሪውን አክብሮ ባለመሄዱ መንግስት በብስጭት የወሰደው እርምጃ ይሆናል ብለው ገምተዋል፡፡ መንግስት ይህን ይበል እንጂ ኢማሞችን ለስብሰባ የጠራበት ምክንያት፤ ኢማሞቹ ሳምንታዊውን ተቃውሞ እንዲያስቆሙና በፀረ ኢስላም እንቅስቃሴው ላይም ከጎኑ እንዲሰለፉ ለማድረግ እንደሆነም ተገምቷል፤ ሲል የ”ፈስቢር” ሪፖርተር ዘግቧል፡፡በዚህ በዛሬው መንግሰታዊ ሽብር ላይ አጅግ በርካታ ሰዎች የተደበደቡ ሲሆን፤ በተጨማሪም የ”ፈስቢር” ሪፖርተር እንደዘገበው፤ በድብደባው እግሩ የቆሰለን ሰው፤ የተደበደቡ በእድሜ የገፉ ሽማግሌ አባትን እና አንድ ሌላ የተደበደበ አካለ ስንኩልን በአይኑ ማየቱን ሪፖርተራችን ገልፆልናል፡፡መንግስት አጉል እልህ ውስጥ በመግባት ወዳልሆነ እርምጃ ከሚያመራ ይልቅ፤ የሙስሊሙን ቀላል ጥያቄ ቢመልስ የተሻለ ይሆናል፡፡ ሙስሊሙ ለእምነቱ እስከ ምን ድረስ መስዋእት እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ እንኳን በማስፈራራት፤ በማሰርና በመደብደብ ይቅርና በመግደልም ቢሆን እንኳ ወሏሂ ሰላማዊ ትግላችንን በፍፁም ሊገታውና ሊያስቆመው አይችልም!!!“ፈኢነ መዓል ዑስሪ ዩስራ” “ከችግር ጋር በእርግጥ ምቾት አለ (ይመጣል)”፡፡ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!!!አላሁ አክበር!!
source.ፈስቢር

No comments:

Post a Comment