Tuesday, March 5, 2013

ፍሬ-አልባ ጩኸት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም


አንሰ እቤ አምግዕዝየ ኵሉ ሰብእ ሐሳዊ ውእቱ!
(የዳዊት መዝሙር 115)
መስፍን ወልደ ማርያም
የካቲት 2005
አቶ ዳንኤልን አላውቀውም፤ ለካ ብዙ ጭፍሮች ያሉት ሰው ነው፤ በጣም ተንጫጩለት፤ የሎሌ ነገር ሆነና ጩኸታቸው አንድ ነው፤ ጉዳዩን ጭራሽ አያውቁትም፤ ያንገበገባቸው መሪያቸው መነካቱ ነው፤ ለሎሌዎቹ መልስ መስጠት ባልተገባ ነበር፤ ነገር ግን ያደረጉት ትክክል መስሎአቸው እንዳይኩራሩና በያዙት የመክሸፍ መንገድ አንዳይቀጥሉ አንዳንድ ነጥቦችን ላብራራላቸው ፈለግሁ፤ ውጤት ይኖረዋል ብዬ ሳይሆን ለኔው ለራሴና ለማኅበረሰባችን ጤንነት ነው፤ ራሴን ከአቶ ዳንኤል ጭፍሮች ለመከላከል ፈልጌ እንዳይመስል፤ አትኩሮት በጉዳዩ ላይ እንዲሆን ለመሞከር ነው።

አንዳንዶቹ ዲያቆን የሚል ቅጽል ባለመጨመሬ ሆን ብዬ መስሎአቸዋል፤ ባለማወቅ ነው፤ ራሴን ተጠራጥሬ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከፈትሁና የማውቀውን ነገረኝ፤ — የተካነ፣ ምሥጢር ያየ፤ ቀዳሽ — የሚል፤ በዚህ መስፈርት እኔም ዱሮ ዲያቆን ነበርሁ፤ ዛሬም ይህንን የሚያሙዋሉ ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚልዮን ባይሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ይኖራሉ፤ በዚያ ላይ እኔ እንደማውቀው ዲያቆን ሦስት ደረጃዎች ሲኖሩት የዲያቆኖች አለቃ ሊቀ ዲያቆናት ይባላል፤ አቶ ዳንኤል ሊቀ ዲያቆናትም አልሆነም፤ የአቶ ዳንኤል ዲያቆንነት የቱ ዘንድ እንደሚወድቅና ምን ማለትም እንደሆነ አላውቅም፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ያለ ማዕርግ መስጠት ጀምራ እንደሆነና ለነማን እንደምትሰጥ አላውቅም፤ እኔ ዱሮ የማውቀው ዲያቆን የቅስና ሥልጣን(በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ይሆናል፤) ሲያገኝ መምሬ መባሉን ነው።
ወደተነሣሁበት ጉዳይ ልግባ — አንድ መጽሐፍ አሳተምሁ፤ አውቃለሁ የሚለው አቶ ዳንኤል ተነሥቶ ስለመጽሐፉም ስለሌላ ሌላም የማያውቀውን ጻፈ፤ ስድስት የግድፈት ነጥቦችን ለቅሜ በማስረጃ እያስደገፍሁ የማያዳግም መልስ ሰጠሁት፤ ይህንን ያደረግሁበት ምክንያት ጭፍሮቹ እንዳሉት ሥራዬን አትንቀፉት በማለት በመታበይ አይደለም፤ ማናቸውም ሥራ አደባባይ ሲወጣ መነቀፉ አይቀርም፤ ስሕተትም አይጠፋም፤ አንድ ሰው በአንድ የአገር ወይም የማኅበረሰብ ጉዳይ ላይ ሲጽፍ ወይም በአደባባይ ሲናገር ራሱን ማጋለጡ ነው፤ የአቶ ዳንኤል ጭፍሮች ይህንን የማያውቁትን ጉዳይ ለእኔ ለማስተማር መከጀላቸው ጨቅላነታቸውን ያሳያል፤ በእኔ ላይ ባወረዱት ውርጅብኝ እንኳን ጉድጓድ ቆፍረው ራሳቸውን ቀብረው ነው፤ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው ነው፤ እነዚህ ጭፍሮች ስለመጋለጥ የሚያውቁት የለም፤ ስለዚህም ጉርጓድ ውስጥ ተቀብረው ስለማያውቁት ነገር መጮሁ የመጀመሪያው ስሕተታቸው ነው፤ ለነገሩ ስሕተት አይደለም፤ ወኔ-ቢስነት ነው።
እነዚህ ሁሉ ጭፍሮች ለጩኸት ከመጠራራታቸው በፊት መጽሐፉን ለማንበብና የክርክሩ መነሻ የሆኑትን ነጥቦች ለመጨበጥ አልሞከሩም፤ ወደው አይመስለኝም፤ ንዴታቸውን ለመግለጽና ግዳይ ለመጣል ስለቸኮሉ ለእነሱ ችሎታ የሚቀልለውን
‹‹የአንተ አሽከር፣ የአንተ ቡችላ፣
ኩፍ ኩፍ ይላል እንደጉሽ ጠላ!
በማለት በአደባባይ አቅራሩ፤ የችሎታ ማነስና ችኮላ ተለውሶ ያንን ጫጫታ አስከተለ፤ ገና ይቀጥላል፤ ባገኙን ቦታ ሁሉ ይህንን ጀብዱአቸውን ሊገልጹልኝ የሞከሩም አሉ፤ ከመሀከላቸው አንድም አንኳን ጉዳዩን ለመገንዘብና በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት የሞከረ አለመኖሩ የአስተሳሰብ ደረጃቸውን በግልጽ ያመለክታል፤ የሁሉም ዘገባ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው።
  • ከመሀከላቸው ስለመጽሐፉ የተናገረ አንድም የለም፤
  • ከመሀከላቸው አንድም ሰው አቶ ዳንኤል ስለጻፈው የተናገረ የለም፤
    • መጽሐፉን ሳያነቡና የአቶ ዳንኤልን ጽሑፍ ሳያነቡ እንዴት ብለው   እኔ በጻፍሁት ብቻ እንደዚያ ያለ የንዴት ጫጫታ ማሰማት ቻሉ?
ለጭፍራዎቹ በመጽሐፉና በአቶ ዳንኤል ጽሑፍ መሀከል ምንም ግንኙነት እንዳላዩበት ግልጽ ነው፤ ሊያዩበትም አይችሉም፤ ስለዚህ የእውቀት ጉድለታቸውን በንዴት ተኩት፤ እነሱው ራሳቸው የተገነዘቡትን የእውቀት ጉድለታቸውን እያጋለጡ ስለመጽሐፉ ለመናገር ወኔ አላገኙም፤ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማምለጫና መብለጫ በሆነው የብልጣብልጥ ዘዴ ተጠቅመው በእነሱ ግምት እነሱን ከፍ እኔን ዝቅ አድርገው ለማሳየት ሞከሩ፤ ጭፍሮቹ በሙሉ እውቀቱ ስለሌላቸው መጽሐፉን ረሱት፤ ስለዚህም ራሳቸውን የሥነ ምግባር ሊቃውንት አደረጉና ትንሽነታቸውን ወደበላይነት ለመለወጥ ጣሩ፤ ይህ ብልጣብልጥነት እንደማያዋጣ ስለገባቸውና የእውቀታቸውንም ጎዶሎነት ስለተገነዘቡ ማንነታቸውን ሳይገልጹ ስማቸውን ደብቀው በአደባባይ ደነፉ፤ ደስ አላቸው፤ አስደሰቱ፤  ‹‹ያንን ፕሮፌሰር ነኝ ብሎ የሚኮፈስ ሰውዬ ልክ ልኩን ነገርነው! ልኩን እንዲያውቅና ከእኛ የማይሻል መሆኑንም ነገርነው!›› አንዳንዶቹ የእውቀት ደረጃቸውን አዘቅት ሲያወርዱ ከመስፍን ጋር ፕሮፌሰርነትንም አብረው ይኮንናሉ! አይ ፕሮፌሰርነት! እንዲህ ከሆነ ይቅርብን! እያሉ ዘላበዱ።
ተመካክረው የተነሡት በእነሱ ሚዛን ስለመስፍን ወልደ ማርያም ምግባረ-ብልሹነት ለዓለም ለመንገር ነው፤ አዋጃቸውን እንቀበለው፤ ስለመስፍን ወልደ ማርያም አንድ እውቀት ያስጨብጠናል፤ ዋናው ጉዳይ ግን መስፍን ወልደ ማርያም አይደለም፤ ዋናው ጉዳይ መጽሐፉ ነው፤ እንግዲህ ስለመጽሐፉ ምንም የማያውቅ ሰው ስለመስፍን ወልደ ማርያም መናገር የሚችለው ስንት ገደሎችን ዘልሎ ነው? ሁሉም ያሉት መስፍን ወልደ ማርያም ለአቶ ዳንኤል የሰጠው መልስ ስድብ ነበር የሚል ነው፤ ነገር ግን ከመሀከላቸው አንድም ሰው ስድቡ ምን እንደነበረ አልተናገረም፤ አንዴም ደህና አድርጎ ያላነበበውን ደጋግሜ አንቤዋለሁ ብሎ ሐሰት የተናገረን ሰው ሐሰት ተናግረሃል ማለት፣ የማያውቀውን አውቃለሁ ብሎ የተናገረ ሰውን አታውቅም ማለት፣ የማያውቀውንና ያልሆነውን ነገር ሲለጥፍብኝና የተናገረውን መልሶ ምሥጢር በማድረጉ የደብተራ ተንኮል ማለት፣ ለእኔ ስድብ አይደለም፤ እውነትን መናገር፣ ወይም ፈረንጆች እንደሚሉት አካፋን አካፋ ብሎ መጥራት ነው፤ ማሰብ የሚችል ሰው ለተናገርሁት ማስረጃ እንዳይጠይቀኝ ማስረጃዎቼን ሁሉ ቁልጭ አድርጌ አቅርቤአለሁ፤ እንዲያውም ትልልቅ ግድፈት የምላቸውን ነገሮች አልገባሁባቸውም፤ እዚያ ብገባ የበለጠ አንጫጫ ነበር፤
ከጭፍሮቹ አንዱም እንኳን መጽሐፉን ያነበበ አይመስለኝም፤ ከጭፍሮቹ አንዱም እንኳን በአቶ ዳንኤል ጽሑፍ ውስጥ ምንም እንከን አላዩም፤ ሊያዩም አይችሉም፤ ከስድብም አልፎ ወንጀል ሊለጥፍብኝ ሲከጅለውም አልታያቸውም፤ ወንጀልን በሰው ላይ መለጠፍ አላዋቂነት፣ ተንኮል፣ ውሸት ቢባል ስሕተቱ ምኑ ላይ ነው? እውነት ከማይከበርበት ቤት የወጡ ጭፍሮች እውነትን አላዩም ብሎ መውቀስ ባይቻልም አለማየታቸውን መናገር ግን ተገቢ ነው።
የአቶ ዳንኤል ጭፍሮች የመጽሐፉን ቁም-ነገር መጨበጥ ስላቃታቸው የሥነ-ምግባር ጉድለት የመሰላቸውን የመመጻደቅ ስብከት አወረዱት፤ ነገራቸው ሁሉ እንደአህያ መልክ አንድ ዓይነት ነው፤ ራሳቸውን አፋፍ ላይ እኔን ደግሞ ገደል ውስጥ ጨምረው እንደናዳ ሊያወርዱብኝ ሞከሩ፤ ከጭፍሮቹ መሀል አንድም እንኳን እሱም ራሱ ሆነ ጓደኞቹ የጻፉት የምግባረ ብልሹነት መግለጫና ማረጋገጫ መሆኑን የመገንዘብ ችሎታ ያለው አልተገኘም፤ በነዚህ ጭፍሮች የማሰብ ችሎታ እውነት መናገርን እንደስድብ ከመውሰዳቸው በላይ እነሱ ግን ለመሳደብ ልዩ ፈቃድ ያላቸውና የሥነ ምግባር ደረጃቸውም  የተለየ ነው፤ እነሱ ሲሳደቡ የሥነ ምግባር ብልሽት አይታያቸውም! እውነትን በደረቅ ቋንቋ ከመስማት ይልቅ ውሸትንና ተንኮልን በለስላሳ ቋንቋ መስማት የሚበልጥባቸው ጭፍሮች አቶ ዳንኤል ለተናገረው ዓይኖቻቸውን ሸፍነው እኔ በሰጠሁት መልስ ላይ ማተኮራቸው ያጋደለ የሆዳምነት ሚዛናቸውን በገሀድ ያሳያል፤ ውሸት የተናገረን ውሸታም ማለት፣ ተንኮልን የሸረበን ተንኮለኛ ማለት ትክክል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእውነት የተራበ፣ ለእውቀት የተራበ ሆኖ ለብዙ ሺህ ዓመታት ባለህበት ሂድ ሲል የኖረው በእንደነዚህ ያሉ የእውነትና የእውቀት ጸር የሆኑ ጭፍሮች እየታገተ ነው።
ሳያውቁት የመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ ዋናውን መልእክት በተግባር አሳዩ፤ እውነትንና እውቀትን (ሁለቱን መለየት አይቻልም፤ እውነትን የማይቀበል እውቀትን አያገኝም፤ እውቀትን የማይቀበል እውነትን አያገኝም፤) አርክሰው እነሱ ጨዋነት የሚሉትን አወጁ፤ አንዱ በማያሻማ መንገድ ገልጦታል፤ መስፍን ኃይለ ማርያም ነኝ የሚል እንዲህ አለ፤‹‹ከእርስዎ ምሁራዊ ስድብ የዳንኤል ክብረት ጨዋዊ መሃይምነት በእጅጉ ይሻላል፡፡›› ይህ ሰው እሱና ጓደኞቹ በያዙት ሚዛን ‹‹ስድብ›› ያሉትን ተቀብሎ ከመታረምና ወደእውነትና ወደእውቀት መንገድ ከመግባት ይልቅ ‹‹ጨዋዊ መሃይምነትን›› መርጦ ለመኖር መወሰኑ ያሳዝናል፤ የዳንኤል ክብረትን አስመሳይነት፣ ደፋርነት፣ አላዋቂነትና ተንኮል በማያሻማ ቋንቋ ለመግለጥ የወሰንሁት በእንደዚህ ያሉ ምስኪን ‹‹ጨዋዊ መሃይሞች›› ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ገምቼ ልከላከልላቸው ብዬ ነበር፤ ተመችቶናል ስላሉ እግዚአብሔር ያውጣቸው፤ ሌሎች ሕመሙ እንዳይጋባባቸው ይጠንቀቁ!
በመጨረሻ በእውቀት ጉዞ ይሉኝታ፣ መግደርደር፣ መሸፋፈን፣ ማድበስበስ፣ መቀላመድ፣ የተጠሉና የእውቀት ጸር በመሆን የሚፈረጁ ዝንባሌዎች ናቸው፤ ሀ ማለት ሁለት ነው፤ ለ ማለት ሦስት ነው፤ ከተባለ ሀ+ለ አራት ነው ሲል የተጻፈውን አላነበብህም፤ ወይም አልገባህም፤ ስለዚህም መልስህ ልክ አይደለህም ማለት መማር ለፈለገ ነውር አይደለም፤ እውነትንና እውቀትን ለማራመድ መንገዱ ይህ ነው፤ የተገነዘበው ይራመዳል፤ እውነትን የሚፈራው ወደኋላ ይቀራል፤ መክሸፍ ማለት እንዲህ ነው።

No comments:

Post a Comment