Sunday, March 3, 2013

አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗል


አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗልበስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ ሢመት ፕትርክናውን አውግዟል
‹‹ዕርቀ ሰላሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በተናገረው መሠረት ይቀጥላል››
/ተመራጩ ፓትርያርክ/
አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች ለውድድር በቀረቡበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ሌሎች ዕጩዎችን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉበት ውጤት የምርጫውን ተሳታፊዎችና ተከታታዮች እያነጋገረ ነው፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የምርጫው ተሳታፊዎችና በተለያዩ መንገዶች የምርጫውን ሂደት የተከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን÷ የምርጫው አሸናፊ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሊኾኑ እንደሚችሉ ከወራት በፊት በሰፊው ሲነገር የቆየ ነበር፡፡ ይኹንና በምርጫው ድምፅ ከሰጡ 806 መራጮች መካከል ከ60 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉበት ውጤት÷ በዕጩነት ከተካተቱትና ለፓትርያርክነት ይበቃሉ የተባሉት ሌሎች ዕጩ ፓትርያሪኮች በተናጠል ካገኟቸው አነስተኛ ድምፆች አንጻር የምርጫውን ሂደት መለስ ብለው ለማጤን እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ፡፡
ስማቸውና የተወከሉበት አህጉረ ስብከት እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት መራጮች፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተከናወነውን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅርበት መከታተላቸውን፣ በአፈጻጸሙ ግልጽና ቀልጣፋ ከመኾኑም ባሻገር ለትችት የሚዳርግ የጎላ ችግር እንዳላዩበት አስረድተዋል፡፡ ይኹንና ከምርጫው ቀን በፊትና ምርጫው ከተካሄደበት አዳራሽ ውጭ ተፈጽመዋል የሚሏቸው ተግባራት ለተጠቀሰው የውጤት መራራቅ በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
አስተያየት ሰጭዎቹ በቅድመ ምርጫው ተፈጽመዋል ከሚሏቸው ተግባራት መካከል÷ መንግሥት አሸናፊው ዕጩ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ እንዲኾኑ ይደግፋል›› በሚል በሰፊው መወራቱና ይህንንም ተከትሎ በመራጮች ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ተፈጽሟል የሚሉት መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ነው፡፡ ቅስቀሳው በተወሰነ መልኩ ‹‹ብፁዕነታቸውን ባትመርጡ…›› የሚል ማስፈራሪያም የተቀላቀለበት እንደነበር መራጮቹ የራሳቸውንና የሌሎች ጓደኞቻቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ ይናገራሉ፡፡
በርካታ የካህናትና ምእመናን ጥቆማ ካገኙና በዕጩ ፓትርያሪክነት ለመወዳደር ይበቃሉ ያሏቸው ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት አለመካተታቸው ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት እኒህ አስተያየት ሰጭዎች÷ በምርጫው ለቀረቡት ዕጩዎች በአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጠው ትኩረትም ምክንያታዊና ሚዛናዊ አለመኾኑንም ለውጤቱ መራራቅ በመንሥኤነት ጠቅሰዋል፡፡ በድምፅ መስጫው ወረቀት ላይ አሸናፊው ዕጩ ብፁዕ ማትያስ በመጀመሪያ ደረጃ መቀመጣቸው በሢመተ ጵጵስና ዘመነኛቸው ከኾኑት፣ በዕድሜ ከሚበልጧቸውና በሁለተኛ ደረጃ ከተቀመጡት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አንጻር የራሱ ተጽዕኖ አሳርፏል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን አስተያየት ሰጭዎች አስተያየት የሚተቹትና ድምፃቸውን ለአሸናፊው ዕጩ መስጠታቸውን ገልጠው የተናገሩ ሌሎች መራጮች በበኩላቸው÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በአባታዊ ሞገሳቸው፣ በአገልግሎት ልምዳቸውና በዓለም አቀፍ ተሞክሯቸው ያገኙት ድምፅ ውጤት የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው እንዳልኾነ ይከራከራሉ፡፡ በቅድመ ምርጫው በየአቅጣጫው በብፁዕነታቸው ላይ ሲሰጡ የቆዩ ትችቶችን መከታተላቸውን የገለጹት መራጮቹ÷ በመጨረሻ ለውጤቱ ወሳኝ የሚኾነው መራጩ የሚወስደው አቋም ነውና በዕጩነት ከቀረቡት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕነታቸው በሰፊ ድምፅ መርተው የተመረጡበት ውጤት ተቺዎቻቸውን ጭምር ያስደነቀ መኾኑን በምርጫው ስፍራ ማረጋገጣቸውን መስክረዋል፡፡
በምርጫው በዕጩ ፓትርያሪክነት የተወዳደሩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ 98 ድምፅ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ 98 ድምፅ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል 70 ድምፅ እና ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ 39 ድምፅ ማግኘታቸው አስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ተገልጧል፡፡
ከምርጫው አንድ ቀን በፊት ከአዲስ አድማስ ዘጋቢ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት ተመራጩ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዕጩነት መካተታቸውን ያወቁት በሀ/ስብከታቸው ኢየሩሳሌም ሳሉ ከኢትዮጵያ በተደረገላቸው ጥሪ መኾኑን ገልፀዋል፡፡ “መንግሥት እርሳቸው ስድስተኛው ፓትርያሪክ እንዲኾኑ ይፈልጋል ስለመባሉ ተጠይቀው÷ ‹‹ስለዚህ ጉዳይ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰሜን አሜሪካ በስደት ላይ የሚገኘው ‹‹ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ›› የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም የሚካሄደው ሢመተ ፓትርያሪክ÷ ‹‹ኢ-ቀኖናዊና የቤተ ክርስቲያንን ክብር ዝቅ የሚያደርግ፣ ሥርዐተ አልበኝነትን የሚሰብክ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ነው፤›› በሚል ቀደም ሲል ያስተላለፈውን ውግዘት ማጽናቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ክብርና አንድነት፣ ሰላምና ሐዋርያዊ ተልእኮ መሳካት አብረውት እንዲቆሙና እንዲሠሩም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በውጭ በስደት ከሚገኙት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ለፍጻሜ ከማብቃት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ተቋማዊ መሻሻል በማፋጠን አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲመጣ ከመንቀሳቀስ አኳያ በርካታ ተግባራት የሚጠብቋቸው አሸናፊው ተመራጭ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት÷ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀጥተኛውንና ትክክለኛውን መንገድ እንድትይዝና መንፈሳዊነትን እንድትጎናጸፍ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡ ዕርቀ ሰላሙ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተናግሯል፡፡ በዚያው መሠረት ይቀጥላል፡፡ ከሲኖዶስ የተለየ ሐሳብ ሊኖረኝ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
በአስመራጭ ኮሚቴው በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የስድስተኛው ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት በነገው ዕለት የአኀት አብያተ ክርስቲያን ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም መገለጹ ይታወሳል፡፡
addis admas

No comments:

Post a Comment