ትልቁን ድርሻ ኤፈርት ይዟል
“በራሳችን መሐንዲስ፣ በራሳችን ገንዘብ፣ በራሳችን የተባበረ ክንድ እንገነባዋለን” በማለት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመስቀል አደባባይ ታላቅ ህዝባዊ ድጋፍና “መዓበላዊ መነቃቃት” ፈጠሩበት የተባለለት የ”ህዳሴው” ግድብ 51 በመቶ ድርሻ የኢትዮጵያ እንዳልሆነ ነዋሪነታቸው በአውሮፓ የሆነ ዲፕሎማት በተለይ ለጎልጉል ገለጹ።
ስማቸው ምስጢር እንዲሆን የጠየቁት ዲፕሎማት እንዳሉት 51 በመቶ ባለድርሻ የሆነችው አገር አውሮፓ የምትገኝ የኢትዮጵያ አጋር አገር ናት። ለጊዜው የባለድርሻዋን አገር ስም መግለጽና የውሉን ዝርዝር ይፋ ማድረግ ያልፈለጉት ዲፕሎማት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የፈለገችውን ውሳኔ በራስዋ ለማስተላለፍ እንደማትችል፤ ያላት ድርሻ 49 በመቶ ብቻ በመሆኑ ድምጽን በድምጽ በሚሽረው በአብላጫ ድምጽ ህግ መሰረት በግድቡ ላይ የሚወሰነው ውሳኔ 51 በመቶ ባለድርሻ በሆነችው አውሮፓዊቷ አገር መሆኑን አብራርተዋል።
49 በመቶ ተብሎ የተገለጸው የድርሻ መጠን ጅቡቲን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች የተቀራመቱት መሆኑን ያመለከቱት የመረጃው ባለቤት፣ አገር ውስጥ ካሉት የንግድ ተቋማት መካከል ኤፈርት ትልቁን ድርሻ መውሰዱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የግል ባለሃብቶች፣ ማህበራት፣ ባንኮችና የተለያዩ ግለሰቦች በትዕዛዝ አክሲዮን መግዛታቸውን ያስታወሱት እኚሁ ዲፕሎማት “በግድቡ ዙሪያ ከሚፈራው የጸጥታ ችግር በላይ አስጊው ጉዳይ የባለድርሻዎች ምስጢር መሆን ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ለግንባታው የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ ከአውሮፓዊቷ አገር ማግኘቱን ያመለከቱት የጎልጉል ምንጭ፣ “ከአገር ውስጥ በአክሲዮን ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ ለአገር ውስጥ በጀት ማሟያና ለመንግስት የስራ ማከናወኛ የሚውል ነው” ብለዋል።
መንግስት በተለያየ መድረክ በተደጋጋሚ ፕሮጀክቱ “በአገር ውስጥ ባለሙያ፣ በአገር ውስጥ ሃብት፣ የሚከናወን የህዳሴ መገለጫ ነው” በሚል ብሄራዊ መነቃቃት የተፈጠረበት የአቶ መለስ ማስታወሻ እንደሆነ ከመግለጽ ውጪ ስለ አክሲዮን ድርሻና አክሲዮን ስለገዙ አገራት እስካሁን የተናገረው የለም።
ግድቡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ መገለጹ ይታወሳል። የአባይ ግድብ ከሱዳን ድንበር 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቤኒሻንጉል ክልል እንደሚገኝ መንግስት የግድቡን ሥራ ይፋ ሲያደርግ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እያለ ፋና በዛሬው እለት ባሰራጨው ዜና “የወንዙን ተፈጥሯዊ የፍሰት አቅጣጫ የማስቀየሩ ስራ እየተሰራ” መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ “ወንዙ ይሄድበት የነበረውን ቦታ 1780 ሜትር ከፍታ ያለው ግድብ የመካከለኛው ክፍል የሚያርፍበት እንደሚሆንም” የፕሮጀክቱ ሥራአስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው መናገራቸውን ጠቅሷል። “አቅጣጫውን የማስቀየሩ ስራ ከመጭው ክረምት በፊት” ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን መሃንዲሱ ጠቅሰው፥ በቅርቡም ዕውን ይሆናል ብለዋል። ግድቡ ግንባታው የተጀመረበት 1ኛ ዓመት በዓልም ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ በአዲስ አበባ፥ እንዲሁም መጋቢት 24 ፕሮጀክቱ በሚገኝበት ስፍራ በተለያዩ ስነ ጥበባዊ ዝግጅቶችና ‘መለስ ቃልህ ይከበራል፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብም በህዝባችን ተሳትፎ እውን ይሆናል’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል” በማለት የዜናው ዘገባ ገልጾዋል።
http://www.goolgule.com/abay-dam-not-ethiopias/
No comments:
Post a Comment