Tuesday, March 12, 2013

ከ140 በላይ የሒልተን ሠራተኞች ያላግባብ ከሥራችን ልንፈናቀል ነው አሉ


 የሥር ፍርድ ቤቶች ቢወሰኑላቸውም ሰበር እንደገና ይታይ ብሏል
በተለያዩ ጊዜያት ተቀጥረው በአስተናጋጅነትና በተለያዩ የሥራ መደቦች በተለይ በባንኩዌት የሥራ መደብ ከሁለት እስከ 15 ዓመታት አገልግለናል የሚሉ 148 የሒልተን ሆቴል ሠራተኞች፣ ያላግባብ ከሥራቸው ሊፈናቀሉ መሆኑን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ሠራተኞቹ እንደሚሉት ወርኃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው ከቆዩ በኋላ፣ ሆቴሉ ‹‹ቋሚ›› ለሚላቸው ሠራተኞች የሚሰጣቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ጠይቀዋል፡፡ ሆቴሉ ደግሞ ቋሚ ሠራተኞች ባለመሆናቸውና አልፎ አልፎ ለሚሠራ ሥራ ጊዜያዊ መሆናቸውን በመግለጽ ጥቅማ ጥቅም እንደማይገባቸው ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡
ሠራተኞቹ የሆቴሉን ምላሽ በመቃወም መብታቸውን በሕግ ለማስከበር በተለያዩ አምስት የክስ መዝገቦች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ሆቴሉንና ሠራተኞቹን በማከራከር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ሠራተኞቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ላይ እንዳብራሩት፣ የተቀጠሩት ለመደበኛ ሥራ ነው፡፡ ሆቴሉ ለተወሰነ ጊዜ በጊዜያዊነት መቀጠራቸውን እስካላስረዳ ድረስ ቋሚ ሠራተኞች አይደሉም በማለት የሰርቪስ ቻርጅ፣ የቦነስ ክፍያና በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ መብቶቻቸውን ሊነፍጋቸው እንደማይገባ አብራርተዋል፡፡
ሆቴሉ ሠራተኞቹ ላቀረቡበት ክስ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው፣ ከሠራተኞቹ ጋር የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የለውም፡፡ የተቀጠሩት አልፎ አልፎ ለሚሠራ ሥራና ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ በገንዘብ የሚተመኑም ሆኑ የማይተመኑ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው አይገባም፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ወይም ኅብረት ስምምነት ወይም ሁለቱም ወገኖች በየግላቸው የተፈራረሟቸው የሥራ የቅጥር ውል እንደሌለ በማስረዳት ክሱ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
የሁለቱንም ተከራካሪዎች ክስና ክርክር ያየውና ያዳመጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ እንዳብራራው፣ በሠራተኞቹና በሆቴሉ መካከል የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አለ፡፡ ሆቴሉ ሠራተኞቹ ቋሚ አይደሉም ብሎ ከመከራከሩ ውጪ በሒሳብ ስሌቱ ላይ ክርክር አላቀረበም፡፡ በመሆኑም ለእያንዳንዳቸው ሠራተኞች 2,956 ብር ከ80 ሣንቲም የወር ደመወዝ መክፈል አለበት፡፡ በገንዘብ የማይተመኑ ብለው ሠራተኞች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ወደፊት የሚታሰቡ ከመሆናቸው ሌላ ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጿል፡፡
የሕክምና አገልግሎት፣ የ24 ሰዓት የሕይወት ዋስትናና የፕሮቪደንት ፈንድ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ፍርድ ቤት መወሰኑን የውሳኔው ግልባጭ ያስረዳል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው ሆቴሉ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም፣ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅደቁ ሆቴሉ የፈለገውን የፍርድ ውሳኔ አላገኘም፡፡
ሁለቱም የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበት በመጥቀስ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታውን ያቀረበው ሒልተን ሆቴል፣ አቤቱታው ተቀባይነት ማግኘቱን የውሳኔው ግልባጭ ያብራራል፡፡
ሠራተኞቹ የተቀጠሩት በመደበኛነት ለሚሠራ ሥራ ሳይሆን አልፎ አልፎ ለሚሠራ ሥራ መሆኑንና ውልም የተዋዋሉ መሆኑን በይግባኝ አቤቱታው የዘረዘረው ሆቴሉ፣ የሥር ፍርድ ቤቶች ሠራተኞቹ ያደረጉትን የውል ስምምነት በማለፍ ይገባቸዋል ብለው መወሰናቸው በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁም ሆነ በሌሎች አዋጆች ተገቢ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
ሰበር ችሎቱ ሆቴሉ ያቀረበውን አቤቱታ ‹‹ያስቀርባል›› ካለ በኋላ ሠራተኞቹ ጥሪ ተደርጐላቸው በጠበቃ ተወክለው መቅረባቸውንና ስለጉዳዩ ማስረዳታቸውን የሚያትተው ውሳኔው፣ በመልሳቸውም ሠራተኞቹ በተከታታይ ለረጅም ዓመታት እየሠሩ መሆናቸውንና የሥር ፍርድ ቤቶችም አረጋግጠው ውሳኔ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱም በተለያዩ መዝገቦች ተመሳሳይ ውሳኔዎችን መወሰኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም አቀፍና የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ማስረዳታቸው በውሳኔው ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የተከራከሩበትን ነጥብ ያደመጠው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ የሥር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሰጡት ተገቢውን ማጣራት አድርገው ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምሯል፡፡
ችሎቱ እንዳብራራው፣ ሠራተኞቹ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 10 መሠረት ያደረጉት ውል የለም፡፡ የባንኩዌት ሥራ ለመሥራት የተቀጠሩ መሆኑንና ላልተቋረጠ ጊዜ እየሠሩ መሆናቸውን በክርክራቸው ውስጥ መገለጹ አልተካደም፡፡ ነገር ግን የሥር ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሠሩና ሆቴሉም ‹‹በመደበኛ ሥራ ማሠራቱ ተረጋግጧል›› በሚል ምክንያቱን የሆቴሉን ማስረጃ ሳይቀበል መቅረቱን ጠቅሷል፡፡ ሆቴሉ የሚሠራቸው ሥራዎች ዓይነትና ብዛት፣ በመደበኛ ሥራ ላይ የሚይዛቸው የሠራተኞች ቁጥር፣ ሠራተኞቹ አልፎ አልፎ የሚሠሯቸው ሥራዎች ቀጣይነት ይኑራቸው አይኑራቸው፣ በቀን ወይም በወር ለአንድ ሠራተኛ ሊመደብ የሚችለው የሥራ ሰዓት ምን ያህል እንደሆነ፣ በሠራተኞቹ ማስረጃም ሆነ በሆቴሉ ማስረጃ አለመረጋገጡን ችሎቱ ገልጿል፡፡
የሥር ፍርድ ቤቶችም የሚመለከታቸው ወገኖች እንዲያረጋግጡ ያደረጉበት የክርክር ሒደት አለመኖሩን ውሳኔያቸው እንደሚያሳይ ሰበር ችሎቱ ጠቅሶ፣ ለጉዳዩ አወሳሰን ወሳኝ የሆኑ ፍሬ ነገሮች በማስረጃ ሳያነጥሩ ትክክለኛና ፍትሐዊ ዳኝነት መስጠት የማይቻል መሆኑን በማብራራት፣ በተከራካሪ ወገኖች ማስረጃዎች ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሚቀርቡ የሚመለከታቸው አካሎች ወይም የባለሙያ ማስረጃዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን አብራርቷል፡፡ በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በደንብ በማጣራት ሌላ ውሳኔ እንዲሰጥ መዝገቡን ወደ ፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት መልሶታል፡፡
የመዝገቡ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መመለስ ሥጋት የገባቸው ሠራተኞቹ፣ ‹‹ከሰበር ችሎት ከተመለሰ ምን ተስፋ አለን?›› በማለት ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ጉዳያቸውን ተከታትሎ ከሥራ አጥነት እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡
reporter.com

No comments:

Post a Comment