Saturday, March 23, 2013

የተመስገን ደሳለኝ ብዕር እየዶለዶመ ይሆን


ከሳምንት በፊት ተመስገን ደሳለኝን ሲያዳልጠው የምትል ጽሁፍ አስነብቤ ነበር፡፡የጽሁፉ አጠቃላይ ምልከታ ተመስገን በልዕልና ጋዜጣ ‹‹የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት››በማለት ላቀረበው ሰፋ ያለ ጽሁፍ በተለይም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን በተመለከተ ለሰነዘራቸው አንድ ጫፍ ለረገጡ አስተያየቶች በበኩሌ የማውቃቸው እውነታዎች በተመስገን እንደተባለው አለመሆኑን ለማሳየት ነበር፡፡ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለንባብ የበቃችው ልዕልና ጋዜጣ እኔ በፌስ ቡክ የለቀቅኩትን ጽሁፍ የፓርቲው ማስተባበያ በማደረግ ‹‹አንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ቡድኑን አስመልክቶ የወጣውን መግለጫ አስተባበለ፡፡››በማለት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
እኔ በራሴ ስምና የግሌ አስተያየት መሆኑን ደጋግሜ የገለጽኩበት ጽሁፍ እንዴት ተደርጎ የአንድነት ማስተባበያ ተደርጎ ሊገለጽ እንደሚችል የሚያውቁት ከመነሻው ፓርቲውን ለመተቸት ብዕራቸውን ከወረቀት ያገናኙ ብቻ ናቸው፡፡የተቃዋሚዎች ውስጣዊና ውጫዊ ችግር ተፈትቶ ለስልጣን የሚበቁበት ዘመን እንዲመጣ እመኛለሁ በማለት እንደ አንድ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ ስትራቴጂስት ስልት ሲቀይስና ሲመክር የነበረ ግለሰብ እንዴት ፓርቲው ያልሰጠውን ማስተባበያ ፓርቲው እንደሰጠ በማድረግ አንባቢን ውሸት ይመግባል፡፡በዚህስ በውሸት ከምንከሳቸው የገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫዎች በምን እንለያለን ?
በኒውስ ሌተርና በኦን ላይን ሚዲያ አማካኝነት እንዲሰራጭ በመደረጉ ሊሆን ይችላል፡፡ለማንኛውም ይህም ቢሆን ፓርቲው ማስተባበያ እንደሰጠ ተደርጎ ለመውሰድ የሚያስደፍር አይደለም፡፡ምክንያቶቼን ልዘርዝር
1)ጽሁፌ የሚጀምረው ለተመስገን ያለኝን አድናቆት በመግለጽ ነው፡፡ለእርሱ ያለኝን ወዳጃዊ ስሜት ለማንጸባረቅም በቁልምጫ ‹‹ተሜ››በማለት ስሙን አንስቼያለሁ፡፡እንዴት ነው ወዳጆቼ ፓርቲ ማስተባበያ በቁልምጫ እየጠራ ሲያወጣ አልታያችሁም ?
2)ፓርቲው ለጽሁፉ ምላሽ እንዲሰጥ በመሻት ከአመራሮቹ ለአንዱ በመደወል ጆሮዬን ጭው ያደረገ ምላሽ እንደሰጠኝ ገልጬ ነበር፡፡እንዴት ነው የፓርቲው ጆሮ ጭው የሚለው?
3)በጽሁፌ ደጋግሜ ፓርቲው እያልኩኝ ጠቅሻለሁ ፡፡ማስተባበያው በፓርቲው እውቅና የወጣ ቢሆን ኖሮ ‹‹ፓርቲያችን››በሚሉ ቃላቶች የሚደገፍ ይሆን ነበር፡፡አይመስላችሁም ?
4)የጽሁፌ ማሳረጊያ‹‹በግሌ ተሜ የመግለጫውን ሙሉ ቃል ሳያነብ ለትችት መቻኮሉ አግራሞት ጭሮብኛል፡፡››የሚል አረፍተ ነገርን ሰርቷል፡፡በግሌ ማለት ምን ማለት ይሆን ;እረ ኤቲክሱን ምን በላው ?
5)በአንድነት ልሳን ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ላይ ስሰራ እንደ መቆየቴ በፍኖተ ነጻነትና በፓርቲው መካከል ያለውን ቁርኝት እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ፓርቲው ጋዜጣው በፓርቲው አመለካከት ብቻ እንዳይታጠርና የሌሎች ሀሳብ እንዳይታፈን በማሰብ ፍኖተ ነጻነት የሁሉም ልሳን እንድትሆን በወሰደው ውሳኔ መሰረት ኢህአዴጋውያን ሳይቀሩ ሀሳብን በሀሳብ ለመሞገት ቢነሱ በሩን ክፍት በማድረግ የማገልገል የሞራል ዝግጁነት ነበረው፡፡ፍጹም የስራ ነጻነት የነበራቸው የጋዜጣው አዘጋጆች(ዋና አዘጋጁ ነብዩ ሀይሉ የፓርቲው አባል አልነበረም) ሞያው ለሚጠይቀው ዲሲፕሊን በመገዛት መንፈስ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ገዢው ፓርቲን የተቹ የባልደረቦቼ ብዕሮች በተቃዋሚው ጎራ (አንድነትን)ጨምሮ ለተመለከቷቸው ስህተቶች አልራሩም፡፡ይህም ጋዜጣይቱን ከፓርቲ ልሳንነት ባሻገር የሁሉም አድርጓት በሳምንት ሁለት ጊዜ እስከ መታተም በመድረስ የአንባቢዎቿን ቁጥር 20.000 አድርሳ ነበር፡፡በዚህ አጋጣሚ የእኛ ጋዜጣ በመሆኗ እኛ ብቻ ልንናገርባት ይገባል ያላሉትን የፓርቲውን አመራሮችና አባለት ላመስግን፡፡እናንተ ለስልጣን ብትበቁ ኢቴቪ ምን አይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል በፍኖተ ነጻነት አሳይታችሁኛልና ምስጋና ይሁንላችሁ፡፡
6)ከጽሁፉ ስር ዳዊት ሰለሞን የሚለው ስሜ መስፈሩ ምን ያመለክታል ይህ ጥያቄ ነጩን ነጭ የማለት ድፍረት ለሌለው ብዕር መጠየቅ አንድነት እንዴት ዳዊት ይሆናል፡ልዕልና የእኔን ጽሁፍ የፓርቲው በማድረግ ካወጣች በኋላ አንድ ወዳጄ ደውሎ እንደምን ዋሉ ክቡር ሊቀምነበር ብሎኛል፡፡እንዴት ነው ዶ/ር ነጋሶ ላይ መፈንቅለ ስልጣን አደረግኩ እንዴ ?
አስቂኙ የማስተባበያ ማስተባበያ
አንድነት ማስተባበያ አወጣ በማለት ዜና የሰራችው ልዕልና ጋዜጣ ሳትነግረን ለማስተባበያው የራሷን ማስተባበያ አውጥታለች፡፡አንድነት የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን አከበረ ያለው የተመስገን ጽሁፍ የመረጃ ምክነት እንዳለበት መጥቀሴ አይዘነጋም፡፡አሁን ልዕልና ያኔ ተሜ ያልጠቀሰውን መረጃ በማውጣት ፓርቲው በ2003 ቀኑን ማክበሩን ፍትህ ጋዜጣ ዘግባ ነበር ብላናለች፡፡አስቂኙ ነገር ፍትህ ዘግባ ነበር መባሉ ነው፡፡በቃ ፍትህ የዘገበችው ሁሉ እውነት ነው ማለት ነው፡ወይ ልዕልና;አሁንም መረጃው ስስ ነው፡፡አንድነት የባህል ቀንን እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን በኢህአዴግ ቀረርቶ አክብሮ አያውቅም፡፡ለአንድነት የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ በዕለቱ ከመጨፈር ብዙ ይርቃል፡፡ገዢው ፓርቲ የብሄር ጉዳይን የያዘበት መንገድ ለኢትዮጵያ የማይበጅ መሆኑን በማመኑን አጥብቆ ይታገለዋል፡፡ልዕልና ሆይ ይህን ማወቅ ከፈለግሽ የፓርቲውን ፕሮግራም ለማንበብ ሞክሪ፡፡
ስለ ብሄራዊ ቡድኑ የጠቀስኩት ነገርም ቅንነት በጎደለው መልኩ ተንሸዋርሮ ቀርቧል፡፡አንድነት መግለጫውን ማውጣቱን አስተባበለ በማለት ልዕልና አቧራ ለማስነሳት የሞከረች ቢሆንም በወቅቱ እኔ ያልኩት ተመስገን የመግለጫውን መንፈስ አልተገነዘበውም ፡፡የመልእክቱን አንኳር ነጥብ ስቶታል እንጂ መግለጫው አልወጣም አላልኩም ፡፡በአንድ ቋንቋ እየጻፍን ይህን ያህል የባቢሎን ግንብ ሰራተኞች የመሰልንበት መንገድ ምስጢር ሆኖብኛል፡፡እናም ነገሬን ልስፈር የሳምንቱም ጽሁፍ ሆነ የአሁኑ የእኔ (የዳዊት)እንጂ የፓርቲው አይደለም፡፡ሳላውቀው የሳምንቱን ጽሁፍ በአንድነት ማህተም አውጥቼው ከነበረም ይነገረኝና ሂሴን ላዋጥ፡፡

No comments:

Post a Comment