Monday, February 4, 2013

የኢትዮጵያ መንግስት በታሰሩት የሙስሊም ኮሚቴዎች ላይ የሠራውን ፊልም ነገ ያስመርቃል።


ጥር 27 ቀን 2005 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ራሱን <<የጸረ-ሽብር ግብረ-ሀይል>>ብሎ የሚጠራው ገዥው ፓርቲ ያዋቀረው ወንጃይ  ቡድን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር በታሰሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች  ዚሪያ ያዘጋጀውን ዶክመንተሪ ነገ ማክሰኞ ምሽት እንደሚለቅ ኢቲቪ አስታወቀ።
<<ጂሀዳዊ ሀረካት>>በሚል ርዕስ የተቀናበረው ይህ ፊልም <<ቦኮ ሀራም በ ኢትዮጵያ>> በሚል ንኡስ ርዕስ  በሙስሊሞች የተጀመረው እንቅስቃሴ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ያለመ እንደሆነ በስፋት የሚተርክ ነው።
የፊልሙ ማጠንጠኛ ጭብጥም  እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በፈለጉ ሙስሊሞችና በመንግስት መካከል የሚደረግን ፍጥጫና ትግል አጉልቶ ማውጣት ነው።
በዚህ ፊልም በ በገፀ-ባህርይነት የሚሳተፉት፤ በእስር ቤት ያሉና በዱላ ብዛት ያላመኑበትን ቃል ለመስጠት የተገደዱ አንዳንድ ታሳሪዎችና መንግስት መልምሎ ያሰለጠናቸው ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል።
በአቶ አቡበክር አህመድ መዝገብ የተከሰሱ 31 እስረኞች ኢቲቪ የሚያቀርበውን ድራማ በመቃወም ለፍርድ ቤት ” የእግድ ትእዛዝ ” እንዲተላለፍላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ተከሳሾች “ፊልሙ ተጠርጣሪዎች ከፍርድ ቤት ነጻ ሆኖ የመገመት ህገመንግስታዊ መብት የሚጥስ መሆኑን፣ የፍርድ ቤቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ መሆኑን፣ ፊልሙን የሚመለከቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ተከሳሾችን ጥፋተኛ የሚላቸው ከሆነ በፍርድ ነጻ ቢወጡ እንኳን ሊካስና ሊተካ የማይችልና የማይመለስ ጉዳት የሚያደርስባቸው መሆኑን፣ ተከሳሾች ተከላከሉ ቢባል የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው እንዳያሰሙ ትልቅ ተጽኖ የሚያሳድር መሆኑንና ፊልሙ ሲቀርብ የታሰበውም ሚዛናዊነቱን ሳይጠብቅ ማለትም ተከሳሾች ስለሚቀርብባቸው ጉዳይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሳይጠየቅና ሳይፈቅዱ በመሆኑ የፕሬስ ህጉን የሚጥስ ነው” የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ የደሴ ቅዱስ ገብር ኤል እና መካነ-ኢየሱስ ቤተክርስትያናት ደሴ ለተካሄደው ለሙስሊሞች የሰደቃ ፕሮግራም ድንኳን መለገሳቸውን የ ኢሳት ዘጋቢ ከስፍራው ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል
ከዚህም በላይ ሙስሊሞች ለሰደቃ ፕሮግራሙ እንጀራ መጋገር ሲከለከሉ ፤ ብዙ ክርስቲያኖች ከየቤታቸው  እንጀራ በማዋጣት  ሰጥተዋል ፡፡

ከወር በፊት በዚያው በደሴ ከተማ <ሙስሊሞችን ደብቃችሗል>> የተባሉ ክርስቲያኖች መገረፋቸውና ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል ፡፡
በተመሳሳይ በ አዲስ አበባ  የጥምቀት በዐል እለት  ሙስሊሞች ምንም እንኳ የትግላቸው አንደኛ አመት ቀን ቢሆንም ፤የክርስቲያኖች በ ኣል በሰላም እንዲከናወን  በማሰብ በአንዋር መስጊድ ተቃውሞ ከማድረግ መቆጠባቸው ይታወሳል።

    No comments:

    Post a Comment