Monday, February 18, 2013

የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በኖርዌይ


በኖርዌይ ለኢሳት የተደረገ የገንዘብ መዋጮ ስብሰባ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ሄለን ዘውዱ አየለ የሚባሉ የጎልጉል ድረገጽ ጋዜጣ ተከታታይ በላኩት የኢሜል መልዕክት አስታውቀዋል፡፡ በስብሰባ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን የገለጹት ሄለን ዘውዱ አየለ “አለም ወደ አንድ መንደር በመጣችበት በዚህ ዘመን መንግስት አልባዋ ሱማሌ እንኳን በነጻነት በግል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የራዲዮ እና የቲቪ ጣቢያዎች ባለቤት ናት። መገናኛ ብዙሃን የአንድ ሃገር የዲሞክራሲ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዕድገትም መሰረት ነው፤ በቅርቡ ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው ዓለም አቀፍ ወርሃዊ መጽሄት እንደዘገበው የስካንዲኒቪያ ሃገሮች ከሌሎች የበለጸጉ ሃገሮች ልቀው የሚገኙት በሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ዕድገታቸው ነው ብሎ ዘግቦአል። ስለዚህም የፖለቲካ ትግላችን የሚዲያ ግንባር ቀደምተነት ያገናዘበ መሆን ይገባዋል” በማለት መናገራቸውን በላኩልን መልዕክታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
ከንግግራቸው በተጨማሪም የገንዘብ ስብሰባውን አስመልክቶ የራሣቸውን ምልከታ እንደሚከተለው ልከውልናል፤
‹‹የኖርዌይ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ዕሑድ የካቲት 10 ቀን 2013 በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። አዳራሹን ሞልተው በጉጉት የጠበቁት በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተወዳጁ የኪነ ጥበብ ሰው ታማኝ በየነ ወደ አዳራሹ ሲገባ በጋለ ስሜት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል። የተለያዩ የእንኳን ደህና መጣህ ንግግሮች ተደርገዋል።
‹‹ተወዳጁ የኪነ ጥበብ ሰው ታማኝ በየነ በሃገርና በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ረገጣ አስመልክቶ በመረጃ የተደገፉ ትንታኔዎችን አቅርቧል። ልምዱንም አካፍሏል። በቀጣይ የጥበብ ሰው አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ ዋናው የገቢ ማሰባሰቢያ የጨረታ መርሃ ግብር ተሸጋገረ። ለጨረታ የቀረበው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ነበር ።ጨረታውን ለማሸነፍ የነበረው ፉክክር የአገር ፍቅር ሰሜት የተንጸባረቀበት ሲሆን፣ በዚሁ ታላቅ ታሪካዊ ባዋጋው ከፍተኛ በሆነበት ጨረታ አሸናፊው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በክብር ተረክበውታል።
‹‹በአርቲስት እንዳለ እና በወጣቶች የተዘጋጀ የምርጫ 97 ድምፃችን ይመለስ በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው የተገደሉ ወጣት ሰላሚዊ ሰልፈኞችን ሁኔታ ያስታወስ ታሪካዊ ድራማ እና በየዝግጅቱ ጣልቃ አዝናኝ ሙዚቃዎች ቀርቦአል።››
ለኢሣት የተደረገውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አስመልክቶ ኢሣትን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ ከተመሠረተ ከሚያዚያ 16፤2002ዓም (April 24, 2010) ጀምሮ ፕሮግራሞቹን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያደርስ ተደጋጋሚ የስርጭት አፈናና ሽበባ ከህወሃት/ኢህአዴግ እየደረሰበት እንደሆነ የሚገለጸው ኢሣት ዕለታዊ ፕሮግራሞቹን ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በዩ ትዩብ (You Tube) ለህዝብ እንዲደርስ እያደረገ ይገኛል፡፡
http://www.goolgule.com/brief-17/

No comments:

Post a Comment