Friday, February 1, 2013

በኢትዮጵያ ከትልልቅ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ የካሳ ክፍያዎች እየተመዘበሩ ነው


ጥር ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከከፍተኛ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ወጪው እስከ 15 በመቶ ይደርሳል ተብሎ የሚገመተው የካሳ ክፍያ አፈጻጸም ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ከመንግስት ፕሮጀክቶች የካሳ ክፍያ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የፌዴራል የጸረ ሙስና ኮምሽን ያዘጋጀውና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን፣የስኳር ኮርፖሬሽን፣የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር፣የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የመሳሰሉ መንግስታዊ ተቋማት በተገኙበት ትላንት በአዲስአበባ ራስሆቴል በተካሄደው ውይይት ላይ ኮምሽኑ ያቀረበው    ክፍያ ጋር በተያያዘ ዓይን ያወጣ ዘረፋ እየተካሄደና የሕዝብ ሐብት በሌቦች እየባከነ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡
ይኸው ጥናት ፕሮጀክቶች በሚነኩአቸው አካባቢዎች ለተነሺዎች የሚከፈለው ካሳ ከፕሮጀክቱ ወጪ ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረና ዓይን ያወጣ ዘረፋ እየተካሄደበት መሆኑንና ችግሩን ለማቆም በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ2003 እስከ 2004 ዓም ብቻ ኮምሽኑ በምርመራ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ፣ከመንገዶች ባለስልጣን ፣የአዲስአበባ ክፍለከተሞች፣በአዲስአበባ ቤቶች ልማት፣በደቡብ ክልል መንገዶች ባለስልጣን፣በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገዶች ባለስልጣን በድምሩ 18 ያህል ክሶች ላይ ተይዘው ምርመራ ላይ መሆናቸውንና የአቤቱታና የክሱ ሁኔታ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን ተጠቁሟል፡፡
በየክልሉ ከትልልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በየግዜው በዕቅድ በሚያዘውና በሚፈጸመው የካሳ ክፍያ መካከል ሰፊ ልዩነቶች መከሰታቸው አስደንጋጭ መሆኑን ያስታወሰው የኮምሽኑ ጥናት 10 ሚሊየን ብር ለካሳ ክፍያ የተያዘለት አንድ ፕሮጀክት የክፍያ መጠኑ 600 ፐርሰንት አድጎ 65 ሚሊየን ብር መከፈሉን፣ሌላ ፕሮጀክት ደግሞ 42 ሚሊየን በዕቅድ ይዞ 244 ሚሊየን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሞ መገኘቱን እንደአብነት አንስቶታል፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቶች እነማን እንደሆኑ በስም አልጠቀሰም፡፡
ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ይፈጸማሉ ከተባሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች መካከል አዋጅ፣ደንብና መመሪያ ተግባራዊ አለማድረግ፣ ካሳ ይሰጣል ሲባል አዳዲስ ግንባታዎች ማካሄድ፣የተጋነነ ግምት መስጠት፣ክፍያውን በትክክል ለተነሺዎች እንዲደርስ ያለማድረግ፣ለካሳ ሲባል አዳዲስ ቋሚ ሰብሎችን መትከል፣በአመራሩ አካባቢ አካባቢውን ሰው በተለየ ለመጥቀም ማሰብ፣ ካሳ የተከፈለበትን የመሬት ይዞታ አለማስለቀቅ፣እና የመሳሰሉት ችግሮች በተግባር የታዩ  ናቸው ተብሎአል፡፡
የኢትዮጽያ መንግስት በአምስት ዓመት በያዘው መርሃግብሩ መሰረት በመንገድ፣በባቡር፣በቤቶች
ልማት፣በስኳር፣በማዳበሪያ ፋብሪካ ልማቶች፣በውሃና ኢነርጂ ልማት፣በኮብል ስቶንና በመሳሰሉት 700 ቢሊየን ብር በጀት የያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በትንሹ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ከልማቱ ጋር ተያይዞ ከየአካባቢው ለሚነሱ ግለሰቦችና ተቋማት የካሳ ክፍያ ይውላል ተብሎ የሚገመት መሆኑ የሕዝብ ሐብት አለአግባብ ይባክናል የሚለውን ሥጋት እንዳባባሰው ተጠቁሟል፡፡

    No comments:

    Post a Comment