Sunday, February 3, 2013

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት አቆሙ


የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአስተዳደራዊ ውሳኔ ከትምህርታቸው የተባረሩ አሥር ተማሪዎች ካልተመለሱ ትምህርታቸውን እንደማይማሩ በማስታወቅ ቅዳሜ ማለዳ የተቃውሞ ሠልፍ አደረጉ፡፡
ካምፓሳቸውን ለቀው ወጥተው ከተማ መግባታቸው ታውቋል፡፡
ተማሪዎች ለተቃውሞ የወጡት ከአንድ ወር በፊት የዳቦ ዱቄት በመበላሸቱ ምክንያት ቁርስ መመገብ ባለመቻላቸው፣ ተባረዋል የተባሉት አሥር ተማሪዎች ተወካይ ሆነው አቤቱታ ማቅረባቸውን ተማሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች የተፈጠረው ችግር ያገኛል በማለታቸው አቁመውት የነበረውን ችግር መቀጠላቸውን አስታውቀው፣ መፍትሔ ሳይሰጥ ተማሪዎች መባረራቸው የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብና ተማሪዎች ማስደንገጡን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ እያሉ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን የማቅረብ መብት እንዳላቸው የታወቀ ሆኖ ሳለ፣ ተወካዮቻቸው ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲባረሩ መደረጉ ትክክል ባለመሆኑ ድርጊቱን በመቃወም ትምህርታቸውን ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎቹ እንዲባረሩ የተደረገው ጥያቄያቸውን በስብሰባ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዲያቀርቡ ከተነገራቸው በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ የተወሰደው ዕርምጃ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው በመውጣት ተቃውሞአቸውን በአደባባይ ለመግለጽ ቢሞክሩም ፖሊስ ያገዳቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን እግዱን ጥሰው ወደ ከተማ ሲገሰግሱ ፖሊስ ወደ ሰማይ ቢተኩስም ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ተማሪዎች አረጋግጠዋል፡፡ ለተቃውሞ ከወጡት በተጨማሪ በርካታ ተማሪዎች በዩቪርሲቲው የተወሰደውን ዕርምጃ ሲቃወሙ እንደነበር የዓይን እማኞችም ተናግረዋል፡፡ ተወካዮቻቸው ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ላቀረቡዋቸው ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ምላሽ ባያገኙም ጥያቄዎቹ ካልተመለሱ ትምህርት እንደማይጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ ተማሪ በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ለተፈጠረ የምግብ መበላሸት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ ማቅረብ ከትምህርት የሚያስባርር ከሆነ፣ መማር ጥቅም የለውም ሲል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ለቀረቡት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች ምላሽ በመንፈግ ተማሪዎችን በማባረሩ ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ በመግባት የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተማሪዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በሰከነ መንገድ ሊመለሱ ካልቻሉ የመማር ማስተማሩ ሒደት ፋይዳው ምንድነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ከተማሪዎቹ ጥያቄዎች በስተጀርባ የሌሎች ኃይሎች አጀንዳዎች እንዳሉ በዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ዘንድ ይታሰባል በሚል ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ተማሪዎች፣ ጥያቄያቸው ከአስተዳደራዊ ጉድለት ጋር የተያያዘ ሰላማዊና ሕጋዊ በመሆኑ የሚነገረው በሙሉ ሐሰት ነው ብለዋል፡፡ ከትምህርት ገበታቸው የተባረሩት ተማሪዎች ከአንድ ወር በኋላ የበቀል ዕርምጃ የተወሰደባቸው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጭምር ጥያቄያቸውን በስብሰባ ላይ እንዲያነሱ ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ እንደነበር ተማሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ችግሩ ይስተካከላል ተብሎ ይህ ዕርምጃ መወሰዱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በርካታዎቹ ተማሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የመጡ በመሆናቸው ትምህርት ቆሞ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ከተቋረጠ ለችግር እንደሚዳረጉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ ከተማ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስለተፈጠረው ተጨማሪ ነገር ማተሚያ ቤት በመግባታችን ምክንያት ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የተማሪዎቹን ጥያቄ በተመለከተ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡
ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment