Sunday, February 24, 2013

ሰበር ዜና፡ አቡነ ሳሙኤል የአቡነ ማቲያስን ለፓትርያርክ እጩነት መቅረብ ተቃወሙ


የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቀሰላም እንደፈረሰ አድርገው እንዲያነቡ የወያኔ መንግስት የተጠቀመባቸው አቡነ አብርሃም ዛሬ ያሰቡት ሳይሳካ የተለየ አቋም ይዘዋል
(ዘ-ሐበሻ) ታማኞቹ የዘ-ሐበሻ የቤተክህነት ምንጮች “መንግስት ተጠቅሞብኝ ጣለኝ” እያሉ በመናገር ላይ ያሉት አቡነ ሳሙኤልና ስደተኛውን ሲኖዶስና የተጀመረውን እርቀሰላም ባልተፈረመ ፊርማና ማህተብ የሚያወግዝ መግለጫ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቭዝን ያነበበቡት አቡነ አብርሃም የአቡነ ማቲያስን ለፓትርያርክነት ለእጩነት መቅረብ መቃወማቸውን አጋለጡ። እጩ ፓትርያርክ መሆን አለባቸው በሚል አስመራጭ ኪሚቴው በመጨረሻም፦
1ኛው ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣
2ኛው ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣
3ኛው. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣
4ኛው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል
5ኛው. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ናቸው የሚለውን ውሳኔ አስመራጭ ኮሚቴው ካሰማ በኋላ አቡነ ማቴዎስ “በቀደመው የአበው ገዳማዊ ሥርዓት መሠረት በዕጩነት መግባት አይገባኝም። አባቶቼ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እኔን ተዉኝ” በማለት እጩ ሆነው መቅረባቸውን ቢቃወሙም በሲኖዶሱ አባላት ማግባባት አቡነ ማቴዎስ በመጨረሻም እጩነቱን ተቀበለው የፓትርያርክ አሯሯጭ ለመሆን ወደ ውድድሩ ገብተዋል ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ሌሎቹም ጳጳሳት እንዲህ ያለ አቋም በማሳየት “የሚመረጠውን ጳጳስ እያወቅን አሯሯጭ አንሆንም” ቢሉም በማግባባት ውሳኔውን ተቀብለዋል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ በመንግስት 6ኛው ፓርትያርክ ይሆናሉ ተብለው ቃል የተገባላቸው አቡነ ሳሙኤል በመጨረሻም በመከዳታቸው እጅጉን በመሳጨት “መንግስት ተጠቅሞብኝ ጣለኝ” በማለት በመቆጨት ላይ እንዳሉ ያወሱት የዘ-ሐበሻ የቤተክህነት ምንጮች የአስመራጭ ኮሚቴው አሠራር፣ ጥቆማና ውሳኔ ትክክል አይደለም በሚል ከረር ያለ ሐሳብ ያሰሙት አቡነ ሳሙኤል እና እርቀ ሰላሙ መፍረሱን እና ዳቦ መቆረሱን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በማብሰር ለወያኔ ተባባሪ የሆኑት አቡነ አብርሃም ባሰሙት ንግግር በተለይ በአቡነ ማትያስ ለዕጩነት መቅረብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ መረር ብለው መናገራቸውን ምንጮቻችን ነግረውናል። በመንግስት መጠቀሚያ ሆነው እንደ “ማስቲካ” ተጥለዋል የተባሉት አቡነ ሳሙኤልና አቡነ ማቲያስ የአቡነ ማትያስ ዜግነት ጉዳይ ዕልባት ሳያገኝና ነገሩም በሥርዓቱ ሳይጣራ ከዝርዝሩ ውስጥ መግባታቸውን አምርረው ቢቃወሙም አጠቃላይ የምርጫው ሒደት ትክክል አለመሆኑንም ለማስረዳት ቢሞክሩም አባይ ጸሐዬ ከጀርባው ሆኖ የሚሰማው ሃይል ምንም ሊያደምጣቸው እንዳልቻለና በወያኔ የተተፉትን አባቶች እንደውም ምልዓተ ጉባዔው ይህን ጥያቄ በዚህ ሰዓት ማንሳታቸው ተገቢ አለመሆኑን፣ “ትናንት ምርጫው እንዲካሔድ ስታቻኩሉ የነበራችሁ እናንተ ናችሁ፡፡ ይዋልና ይደር፣ ጉዳዩን በጥሞና እንመልከተው ስንላችሁ አይሆንም ብላችሁ አጣደፋችሁት፡፡ አሁን ስምንት መቶ መራጭ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ የውጭ እንግዶች እየተጠባበቅን ባለንበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ግርግር ማንሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዋረድ ነው” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ምንጮቻችን ነግረውናል። ይህም የሚያሳየው ሁለቱ አባቶችን ወያኔ እርቀሰላሙን እንዲያሰናክሉ ያዘጋጃቸውን እነዚህን አባቶች አንቅሮ መትፋቱን ያሳያል ሲሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ዘ-ሐበሻ አሁንም ይህን ጉዳይ እየተከታተለች፤ የደረሰበትን ጉዳይ ታሳውቃለች።
እውነት ያሸንፋል!!
Ze-Habesha Website is not responsible for accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.

No comments:

Post a Comment