(ኢ.ኤም.ኤፍ) በአዲስ አበባ የተሰቀሉት የመለስ ዜናዊ ፎቶዎች ስድስት ወራትን አስቆጠሩ። ፎቶዎቹ አንዳንድ ቦታ ላይ… ቆሽሸውና ነትበው መቀዳደድ ጀምረዋል። የከተማውንም ውበት እየቀነሱት ነው። አሁን የሚያስፈጽመው መገኘቱን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፤ “ፎቶዎቹ ይውረዱልን!” የሚሉት ወገኖች እየበዙ ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ “ፎቶዎቹ ይነሱ! በመለስ ስም መነገድ ይብቃ!” የሚሉትን ሃሳቦች የሰነዘረው ያቀረበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነበር። አሁን ጥያቄውን የሚያስተጋቡ ሰዎች ጨምረዋል። አቶ አዲሱ ለገሰ፤ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር በትላንትናው እለት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል። “በየጎዳናው የተሰቀሉት የመለስ ፎቶዎች እንዲነሱ” ብለዋል – በተለሳለሰ አነጋገር። አቶ አዲሱ ለገሰ ይህን ያሉት የመለስ ዜናዊ መታሰቢያ ድርጅትን ወክለው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው። አሁን ችግሩ ያለው “ይህንን ለማድረግ የሚመለከተው ማነው?” የአዲስ አበባው ከንቲባ ወ/ሮ አዜብን ይፈራል፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ህወሃትን ይፈራሉ። ፓርላማው ከኢህአዴግ ጽ/ቤት መመሪያ ካልመጣ ምንም መመመሪያ አያወጣም። “ማን ያስፈጽመው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ጠፍቶ ሁሉም ተፋጠዋል። የማይደፈረውን ሞት የደፈረው መለስ ዜናዊ እና ፎቶዎቹም ቀስ በቀስ እያረጁና እየተቀዳደዱ ናቸው። አንዳንዶች “ይህ ሁኔታ የስርአቱን መቆሸሽ እርጅና ያሳያል” የሚሉ ወገኖች አሉ። እኛ የማይደፈረውን የደፈረው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሲያልፍ R.I.P. (Rust in Pieces) ብለን ነበር። አሁን መንገድ ላይ አርጅተው ለተቀዳዱት ፎቶዎች በተመሳሳይ መልኩ R.I.P. (Rust in Pieces) ብንል አሁን የሚታየውን ሁኔታ አንጸባራቂ እውነታ ነው ብለን እናምናለን። በአጠቃላይ የአቶ መለስ ዜናዊ ያረጁ ፎቶዎች እንዲነሱ የመጠየቁ ሂደት ከኢህአዴግ ውጭ እና በኢህአዴግ ውስጥ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም ‘ፎቶዎቹን በድፍረት ማን ያንሳቸው?’ የሚለው ጥያቄ ምላሽ አጥቶ፤ የመንገድ ላይ ፎቶዎቹ የክረምት ውሃ እና የበጋ ጸሃይ እየተፈራረቀባቸው ይገኛሉ።
No comments:
Post a Comment