Saturday, February 23, 2013

ወጣቷን ማን ገደላት?

መስከረም 2 ቀን 2000ዓ.ም ነው፤ በድንገት መተንፈስ አቅቶኝ በጣም ታመምኩ፤ ፈረንሳይ አካባቢ በሚገኘው < ቅድስተ ማሪያም ከፍተኛ ክሊኒክ> ተወሰድኩ፤ በአስቸኳይ መተኛትና ኦክሲጅን ከስታብላይዘር ጋር መውሰድ እንዳለብኝ..ዶ/ር ገለፀ። የመኝታ አንድ ሺህ ብር ተያዘ።..አልጋ ይዤ አንድ ሰዓት እንኳ ሳይሞላኝ …የክሊኒኩ ነርስ መጥታ « ይቀርታ ኦክሲጅን የለንም..ስለዚህ ወደ ጳውሎስ ሆ/ል ሪፈር ተብለሃል» ብላ ወረቀት ሰጠችኝ። ምንም ህክምና ሳላገኝ 500 ብር ቆርጠው ግማሹን ሰጡኝ። ወደ ጳውሎስ ተወስጄ በድንገተኛ ክፍል ያለአንዳች ህክምና እርዳታ ለ10 ሰዓታት ቆየሁ፤ ስቃዬ ጨምሮዋል፤ ከምሽቱ 4ሰዓት ሲሆን በጣም ስለደከምኩ ኦክሲጅን ተሰጠኝ፤…ከአጠገቤ 3 ሰዎች ተኝተዋል፤ አንዷ ወጣት አስቸኳይ ደም ያስፈልጋት ነበር፤ ቤተሰቦቿ የታዘዘውን አደረጉ፤….ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ድረስ ደም ስላልተሰጣት በጣም ደከመች፤ ቤተሰቧ ተረብሸው ተረኛው ነርስ የተኛበት ክፍል ሄደው ለረጅም ሰዓት ተማፀኑት፤ እየተጨናበሰ « ምን ከእንቅልፌ ትበጠብጡኛላችሁ..» እያለ መጣ፤ ከዛ ለተዳከመችው ወጣት ደም ቀጠለላት፤ ወዲያው ነርሱ ሲደናገጥ አየሁት….የወጣቷን አስታማሚዎች ጨምሮ..የኔን እንዲሁም የሌላውን ከክፍሉ እንዲወጡ አደረገ፤…በደረብኩ ጋቢ አሸንቁሬ ሂደቱን እከታተላለሁ፤…ወዲያው,….ወዲያው.. የወጣቷን የደም ግፊት ይለካል። አንዲት መለከ መልካም ዶ/ር መጣች፤ ሃዘን በተቀላቀለበት የለሆሳስ ድምፅ « እንዴት?…እንዴት እንዲህ አይነት ስሀተት?…» አለችው ለነርሱ ..እንባዋን እያፈሰሰች፤ ወጣቷ ላትመለስ በሞት አንቀላፍታለች፤ የታዘዘው ደምና የተሰጣት ልዩነት ስለነበረው ለሞት ዳረጋት፤ ሴቷ ዶ/ር ያለችውም ይህንኑ ነው « ከመስጠትህ በፊት ለምን ቼክ አላደረክም?» የሚል፤…ያቺ ወጣት በዛ አይነት ስህተት መሞትዋን ቤተሰቧ አያውቅም። ያው « እ/ር ፈጠራት..እራሱ ወሰዳት » እንደሚሉ አያጠራጥርም። ግን ወጣቷን የገደላት ነርሱ ነው፤ ቀይ መስቀል ነው!!.. ያን ከወንጀል ያልተናነሰ ድርጊት የምናውቅና ያየን ደግሞ ፥ ዶ/ሯ፣ነርሱ እንዲሁም እኔ ነን። የዚህን አገር ህክምና አሰጣጥ ስመለከት…ከሕሊናዬ የምትጠፋው ይህቺ ሟች ወጣት ድቅን አለችብኝ። ..አወይ አገሬ፥ ዳቦ፣ የፍትህ እጦት፣ የህክምና ችግር….መከራ በመከራ የተደራረበባት….መቼ ይሆን ወገኔ ከዚህ ሁሉ የሚላቀቀው?…እንባዬን ጨምቄ የማነሳው የዘወትር ጥያቄ ነው!!

No comments:

Post a Comment