በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራው ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ በተገባደደው ሳምንት በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ያደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የበለጠ ለማቆራኘት መሠረት የጣለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን መሠረታዊ መብቶች ማለትም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ግን በአውሮፓ ኅብረት በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ነጥሮ የወጣ ጥያቄ ሆነ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሩት የኢትዮጵያ ልዑክ ከአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ እንዲሁም ከኅብረቱ ሊቀመንበር ማኑኤል ባሮሶና ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር በኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ብራስልስ ውስጥ ተወያይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትኩረት ባደረገው ውይይት ከኅብረቱ ፓርላማ ጋር የተነጋገረው የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ቡድን፣ በተለይ በውጭ ኩባንያዎች የመሬት ወረራና ይህንን ተከትሎ ተፈጠረ ስለተባለ የነዋሪዎች መፈናቀልና ተያያዥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ማብራሪያ ተጠይቋል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባለው የመሬት ወረራ በኢትዮጵያ አለመኖሩንና ሊኖርም የማይችል እንደሆነ ገልጸው፣ የተባለው ወቀሳ የፖለቲካ ፍላጐት ያላቸው ተቋማት ዘመቻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 400 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ ለውጭ ኩባንያዎች በሊዝ መሰጠቱን፣ እየተባለ ያለው ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን ዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ መንግሥታቸው የበለጠ መሥራት የሚጠበቅበት መሆኑንና ለዚህም ቁርጠኝነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሰጡት ማብራሪያ ቢኖርም፣ የአውሮፓ ኅብረት ግን ከማብራሪያው በኋላም በዚህ ጉዳይ ላይ ጠበቅ ያለ አቋም የያዘ ይመስላል፡፡
ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ የጋራ መግለጫ የሰጡት የኅብረቱ ሊቀመንበር ማኑኤል ባሮሶ ኢትዮጵያን የበለጠ ለማሳደግ ስለተያዘው ዕቅድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ያደረገችውን ለውጥ ያደነቁት ሊቀመንበሩ፣ የዚህ ዕድገት ቀጣይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ግን የአገሪቱ ሕዝብ መሠረታዊ መብቶች፣ የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነቶች ሲከበሩ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት እንቅስቃሴ
ጥሩ መሆኑን፣ በተለይ በፀረ ሽብርና በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ዙሪያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም መልካም እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ መስክም ኅብረቱ በጋራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ጥሩ መሆኑን፣ በተለይ በፀረ ሽብርና በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ዙሪያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም መልካም እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ መስክም ኅብረቱ በጋራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በኢኮኖሚያዊ ትብብር የበለጠ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጐት መኖሩን ከኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ጋር የተደረገው ውይይትም ይህንን ዕውን ለማድረግ ዕድል የፈጠረ እንደሆነ በኅብረቱ ሊቀመንበር ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም መንግሥታቸው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያለው ግንኙነት ከዕርዳታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲሻገር ፍላጐቱ መሆኑን ማስረዳታቸው ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment