“ኣዎ ኣሸባሪ ነኝ። ያሸበርኳቹ ያህል ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ባላሸብራቹ ኑሮ የኔን ፌስቡክ ለማስዘጋት ባልተረባረባቹ ነበር” መለስኩለት።
ስልኩን ጀሮየ ላይ ጥርቅም ኣድርጎ ዘጋው።
“ለካ እንዲህ ለነፃነት የሚቆሙ፣ የፈለጉትን የሚፅፉ፣ ስለ ፍትሕ የሚዘምሩ ግለሰዎች ናቸው ‘ኣሸባሪ’ ተብለው በኣምባገነን ገዢዎች የሚሰየሙት” ስል ኣሰላሰልኩ። “ኣሸባሪ” የሚለውን ስም ወድጀዋለሁ። “ኣሸባሪ” መሆን ደስ ይላል። ጥያቄው መሆን ያለበት ‘የሚሸበረው ኣካል ማነው?’ (ሰለማዊ ህዝብ ወይስ ገዢው መደብ) ነው። ምናልባት እኔ “ኣሸባሪ” ከተባልኩ በኔ የተሸበረው ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው።
ግን ገዢው መደብ የሚያሸብሩ ሰዎች ሌላ ስም ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም መሪዎቻችን ስልጣናቸውን ያለ ኣግባብ ተጠቅመው ሰለማዊ ህዝብ ሲያሸብሩ ምን ብለን ልንሰይማቸው ነው? መንግስትን የሚቃወም “ኣሸባሪ” ከተባለ፣ ህዝብን በጭቆና የሚያሸብር ባለስልጣንስ ????
ከጭቆና በላይ ሽብር የለም። ምክንያቱም ጭቆና ማስፈራራት፣ ግድያ ……… ምናምን (ሰው ፈርቶና ተሸብሮ ሳይቃወም እንዲገዛ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች የሽብር ተግባራት ናቸው)። “ሽብር” ማለት’ኮ ኣንድ ኣካል ራሱ የሚፈልገውን ተግባር በሌሎች ሃይል በመጠቀም ወይ በማስፈራራት ለመጫን ሲሞክር ነው። ሌሎችን እያስፈራራ ያለው ማነው??? እኔ ወይስ ገዢው ፓርቲ? ኣሸባሪ ማነው? ማነው ሰለማዊ ዜጎችን በማፈን እያሸበረ ያለው?
ይሄንን ሳስብ ከቆየሁ በኋላ ትንሽ ቀለል ኣለኝ። ‘መንግስትን መቃወም ትክክል ነው’ ማለት ነው ብዬ በራሴ ተፅናናሁ። ምክንያቱም መቃወም ኮ የሚያስፈልግ የምንቃወምበት ምክንያት ሲኖረን ነው። ይሄው ምክንያት ኣገኘን። የሚቃወም ሰው ማፈን ዓፈናን በመቃወም መንግስትን ለመቃወም በቂ ምክንያት ነው።
ዛሬ ጠዋት ኣንዳንድ መረጃዎች ደረሱኝ። ባለፈው ቅዳሜና እሁድ (ለህወሓት ጉባኤ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሰልፍ በተጠራ ግዜ) ስለ ሰልፉ ኣስፈላጊነትና የትእምት ንብረትነት ፅፌ ነበር። ከዚህ በመነሳት የተወሰኑ የፖሊስ መኮነኖችና የደህንነት ተጠሪዎች በጉዳዩ ተወያይተው እኔን ለማሰር ሓሳብ ኣንስተው ምክንያት በሚያፈላልጉበት ግዜ ሳይስማሙ ቀርተዋል።
የማክሶኞ ኣጀንዳ ባብዛኛው ‘የመለስ ታሪክ’ መተረክ ነበር (ከጉባኤው ኣጀንዳ ዉጭ)። ሰኞ በፃፍኳቸው ነጥቦች (ስለ ጉባኤው ኣሰራርና የድርጅት ሥራ ተግባራት፣ ስለ ፍትሕ ጉድለት፣ ስለ ህወሓት ምስጢር ባጠቃላይ) ትናንት ሮብ ኣጀንዳ ሁነው ውለዋል። “ሚስጢር እየወጣ ነው። የጉባኤው ምስጢር መጠበቅ ኣለበት” ተብሎ ከመድረክ ከባድ ማስጠንቀቅያ ተሰጥተዋል። ከቤትም “ምስጢራችን ከሌሎች ከምንሰማው በራሳችን የሚድያ ሰዎች ቢነገር ኣይሻልም ወይ?” የሚል ኣስተያየት ስለተሰጠ ሬድዮ ፋና ኣንዳንድ ነጥቦች (በተለይ ስለተቀነሱ የህወሓት ኣመራር ኣባላት ስም ዝርዝር) ማሰራጨቱ ሰምቻለሁ።
ሌላው ሳይታሰብ (በህወሓት ጉባኤ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ) ኣጀንዳ የሆነው የትእምት ጉዳይ ነው። “ትእምት ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ተከፍቶብናል” የሚል ሓሳብ ኣንስተው ድርጅቱ ጥሩ እየሰራ እንደሆነ ተሳታፊዎችን ለመጀንጀን ሞክረዋል። ትእምት ሌላ የብረታ ብረት ፋብሪካ እንደሚከፍትና በመሰቦ ሲሚንቶ በኩል ደግሞ የፕላስቲክ ፋብሪካ (በ ስድስት ቢልዮን ብር ካፒታል) እንደሚገነባ ተነግረዋል።
ትናንት ማታ ዛሬ ለሚመረጡ 45 የማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት 50 እጩዎች መርጠዋል። ኣርከበ ዕቁባይ፣ ስዩም መስፍንና ብርሃነ ገብረክርስቶስ ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ከማእከላዊ ኮሚቴ ኣባልነት ተቀንሰዋል። ኣብዛኞቹ (የተቀነሱት) ከነኣርከበ ዕቁባይ ቡድን ናቸው። ጉባኤው ዛሬ ይጠናቀቃል።
ባጠቃላይ ግን በፌስቡክ የሚነገሩ ወሬዎች በህወሓት ጉባኤ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። በርስበርሳቸው ኣለመተማመንና መወቃቀስ ተያይዘውታል። የኔ ፌስቡክ ለማስዘጋት ከተቋቋመ ግብረ ሃይል የተወሰኑ የማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት በኣስተባባሪነት ተሳትፈዋል። ከተወሰነ ኣከባቢ ወይ ወረዳ በመጡ ሰዎች (You may guess) የኔን ፌስቡክ እንዲዘጋ ለማድረግ “የራሱ ስም ኣይደለም” በማለት (ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ) ወደ Facebook Admin ሪፖርት እንዲያደርጉ መመርያ ተሰጥተዋል።
ኣዎ ኣሸባሪ መባል ደስ ይላል። ህወሓቶች እንዲህ በጣም ፈሪዎች መሆናቸው ኣላውቅም ነበር። በፌስቡክ እንዲህ ይሸበራሉ ብዬ ኣላሰብኩም ። ኣሁን ግን ራሳቸው ኣጋለጡ።
የህዝቦች ነፃነት ይቅደም።
No comments:
Post a Comment