(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)
መለስ “ከዋሸኸን ትሞታለህ”
መለስ ሀዋሳን ክልል ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር
የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች አቶ መለስ እድሜያቸው አጭር እንደሚሆንና እንደሚቀሰፉ ነግረዋቸው እንደነበር ተሰማ። በክልሉ የአገር ሽማግሌ ከሚባሉት መካከል አንዱን በማነጋገር በተለይ ለጎልጉል የተላከው መረጃ እንደጠቀሰው መለስ እድሜያቸው ሊያጥርና በድንገት ሊቀሰፉ የሚችሉት የሲዳማን ባህላዊ ልብስ ለብሰው ከዋሹ ነበር።
እንደመረጃው መለስ በ1997 ዓ ም ምርጫ ውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት አራት ተከታታይ ቀናት ሃዋሳ የብሄር ብሄረሰቦች አዳራሽ ውስጥ የብሄረሰቡን ተወላጆች ሰብስበው አነጋግረው ነበር። “አዲስ አበባ ያለው ድንኳናችን ፈርሷል። እዚህም ከፈረሰ በቃን ማለት ነው” በማለት የአገር ሽማግሌዎችን በተማጸኑበት ንግግራቸው መለስ አስቀድሞ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።
ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ሙሉ ልብስ ለብሰው መድረክ ላይ ተቀምጠው የነበሩትን መለስ “ማን እዛ ላይ አወጣህ? አውርደንሃል” በማለት ሽማግሌዎች ሲናገሩ በወቅቱ የጸጥታ ሃይሎችና የአቶ መለስ ጠባቂዎች ተደናግረው ነበር። ሽማግሌዎቹ አቶ መለስን ከመድረክ አውርደው “አስቀድመህ ያገራችንን የባህል ልብስ ለብሰህ ነው መድረክ ላይ የምትወጣው” በማለት ከመድረክ አውርደው ጓዳ በማስገባት “ሴማ” የሚባለውን የባህል ቡሉኮ አለበሱዋቸው።
“ይህንን የሚለብስ እውነት የሚናገር ብቻ ነው” በማለት አቶ መለስ መዋሸት እንደማይገባቸው ሽማግሌዎቹ አሳስበው እንደነበር የጠቆመው መረጃ፣ “ይህንን የሚለብስ መሪ የሆነ፣ እውነት የሚናገር ብቻ ነው። የሚዋሽ ይሞታል። እድሜው ያጥራል። ይቀሰፋል” በማለት በሲዳምኛ ደጋግመው መናገራቸውንና አቶ መለስም የተባሉትን ለማድረግ ተስማምተው እንደነበር አመልክቷል።
በዚሁ መሰረት አቶ መለስ በ1997 ምርጫ ተከትሎ ካጋጠማቸው ቀውስ ለመውጣት ሃዋሳን ከሌሎች የደቡብ አካል በመነጠል ራስዋን የቻለች ክልል ለማድረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ሃዋሳን ክልል ማድረግ አስቀድመው ቃል በመግባት በወቅቱ ከሲዳማ ህዝብ ማግኘት የፈለጉትን ድጋፍ ለማግኘት እንደተጠቀሙበት መረጃው ያስታውሳል።
አሁን በስደት የሚገኝና በወቅቱ ስብሰባው ላይ ተገኝቶ እንደነበር የገለጸ ለጎልጉል እንደተናገረው ቢችልም አቶ መለስ የገቡትን ቃል ለማስፈጸም የተመረጡትን 20 ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ትልቅ ሆቴል በማስቀመጥ ገንዘብ በመስጠትና መሬት በማደል በሲዳማ ቅንጅት እንዲመረጥ የቀሰቀሱ ሰዎችንና ዋና አስተባባሪዎች ላይ የቂም ርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል።
ጉዳዩ አፈታሪክና ወይም ተረት ቢመስልም የሲዳማ አባቶች መለስ በፈጸሙት ክህደት እንደረገሟቸውና ሞቱ ተብሎ የሚታመነውም በዚሁ ርግማን እንደሆነ ያመለከተው መረጃ የሲዳማ ህዝብ አሁን እየደረሰበት ያለው በደልና ግፍ እያየለ በመሄዱ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ “ሲአን” ራሱን ከምርጫ ማግለሉ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው አመልክቷል። ድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከ787 በላይ አባሎቻቸው በመታሰራቸውና ባለፈው ሳምንት በዳሌ ወረዳ እጩ ተወዳዳሪው ተሾመ ካሰና የሚባል ሰው ተገድሎ በመገኘቱ እንዲሁም የሲአን አባላትን ማዋከብ፣ ከስራ ማፈናቀል እና ተማሪዎችን ማባረሩ በመቀጠሉ ድርጅቱ ራሱን ለማግለል መወሰኑን ዋና ጸሀፊው ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ተሰማርተው በድርጅቱ አባሎች ላይ ወከባ እየፈጸሙ መሆኑን ዋና ጸሀፊው ተናግረዋል። መንግስት ከምርጫው እንዳይወጡ ለምኗቸው እንደነበር ዋና ጸሀፊው መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቧል።
አንደበት
“ዛሬ ውድ ሀገራችን ደብዘዋ ጠፍቶ፣ ሕዝቧ ምስቅልቅሉ ወጥቶ ፣ሥነልቡናው እየተሰለበ፣ዓይኑ እያየና ጆሮው እየሰማ፣ ባህሉ እየተንቋሸሸና እየተጓደፈ፣ ታሪኩ እየተደለዘና ቅርሱ እየተመዘበረበት የውሻ ሞት እየሞተ ነው። በእንደዚህ ያለ የመከራ ጊዜና ወቅት አንገቱን ደፍቶ፣ያልከፋው መስሎ ሆደሰፊ በመሆንና ሳይቸኩል ፈጣሪውን ለምህረት እየተማፀነ ራሱን ሳያጋልጥ ለትግል የሚሰናዳ ታላቅ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው። http://www.ethiotube.net/video/19536/Professor-Asrat-Woldeyes ፕ/ር አስራት ወልደየስ በመዐህድ የወጣቶች ስብሰባ ላይ ከተናገሩት የተወሰደ።
ግንቦት 7 የህቡዕ ሃይል ተደራጅቷል አለ
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዘር ፖለቲካና አገሪቱ እየተጓዘችበት ያለው አደገኛ አቅጣጫ ያሳሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ራሳቸውን በህቡዕ በማደራጀት በቅርቡ ከሌሎች ለለውጥ ከሚታገሉ ሃይሎች ጋር በመሆን ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ለመሸጋገር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ግንቦት 7 አስታወቀ። ንቅናቄው በድረ ገጹ እንዳስታወቀው በህቡዕ የተደራጀው ቡድን ስያሜና ኣላማ “ኢትዮጵያን አድን” የሚል ነው።
በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ የህዋሱን መሪ እንዳነጋገረ፣ ነገር ግን ለደህንነት ሲባል ስማቸውንና ድምጻቸውን ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን የጠየቀው የንቅናቄው ዜና ቡድኑ ከአራት ዓመት በፊት እንደተቋቋመ አስታውቋል። በ“አገርህን አድን” ቡድን ስር በመደራጀት ላይ የሚገኘዉ ሠራዊት አላማ የሠራዊቱን መብትና ነጻነት አስጠብቆ ወደ ሠፈሩ መመለስ ሳይሆን የቡድኑ ተቀዳሚ አላማ ለህዝብ በገባዉ ቃል መሠረት ኢትጵያንና ህዝቧን ከወያኔ ዘረኝነትና ከፋፍለህ ግዛዉ ፖሊሲ ማዳን መሆኑንን የቡድኑ ቃል አቀባይ በመጥቀስ አመልክቷል። የንቅናቄው ድረገጽ አፕሪል 13/2013 ይፋ ያደረገው ዜና “በአሁኑ ወቅት አያሌ ኢትዮጵያዉያን ወያኔን ለመታገል መሳሪያ ካነሱ ወገኖች ጋር በየቀኑ እየተቀላቀሉ ስለሆነ የኛም አላማ የትግል ስልትና የተለየ የትግል ቦታ ሳንመርጥ ወያኔን ያዋጣናል ባልነዉ ስልትና ይመቸናል ባልነዉ ቦታ ሁሉ እስከእለተ ሞቱ እንታገለዋለን” በማለት ከፍተኛ መኮንን የተባሉት የቡድኑ ቃል አቀባይ መናገራቸውን አመልክቷል። ግንቦት 7 በተለያዩ ጊዚያት ተመሳሳይ ወታደራዊ ዜናዎች ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ኳታር ወደ ኢትዮጵያ ኢሳያስ ወደ ኳታር
የኳታር መንግስት በአሚር ሼኽ ሐሚድ ቢን ካሃሊፍ አልታሃኒ የሚመራ የልዑካን ቡድን በመያዝ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር። በዚሁ ጉብኝት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መምከሩና በጋራ ለመስራት መስማማታቸው በተለያዩ መገናኛዎች ተዘግቧል።
በተመሳሳይ ሳምንት የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኳታር አምርተው ነበር። የኳታር የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ኳታር በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራውን የኤርትራ ልዑክ በክብር ተቀብላ አነጋግራለች። ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ሃይሎችን ትረዳለች በሚል በተደጋጋሚ ክስ ስትሰነዝርባትከነበረችው ኳታር ጋር በግልጽ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመስራት አዲስ ስምምነት ማድረጋቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል። ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በይፋ ባይናገሩም ኳታር ወዳጇ የሆነችውን ኤርትራንና ኢትዮጵያን ለማስማማት ውስጥ ውስጡን እየሰራች እንደሆነ ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
ኳታር ከኤርትራ መንግስት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስ ሲከሳት የነበረው ኢህአዴግ ይፋ ባያደርገውም በተመሳሳይ ሳምንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኳታር ማምራታቸው ኳታር ሁለቱን አገሮች ለማሸማገል እየተንቀሳቀሰች ለመሆኑ አመላካች እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል። ኤርትራን በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ የምትታወቀው ኳታር በሶማሊያ የተፈጠረውን ሰላምና መልሶ ግንባታ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆኗን ኢትዮጵያ አስታውቃለች። ኢትዮጵያ በኳታር ላይ ክስ ከማቅረብ አልፋ ኤምባሲዋን ዘግታ እንደነበር ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment