Friday, April 5, 2013

ኢህአዴግ ብቻውን እየተወዳደረም አልመረጥም ብሎ ሰግቷል


በተለያየ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው ያሉ ካድሬዎችና ደህንነቶች ሠራተኞችንና ነዋሪዎችን በየቀበሌው እንዲሁም በተለያዩ አዳራሾች እየሰበሰቡ ኢህአዴግን መምረጥ ግዴታ እንደሆነ ከዛቻና ከማስፈሪያ ጋር መመሪያ እየሠጡ መሆናቸውን ምንጮቻችን ለፍኖተ ነፃነት አስታወቁ፡፡
የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደህንነቶች በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ ካስደረጉ በኋላ ስብሰባው የተጠራበትን አጀንዳ በመተው “ኢህአዴግን መምረጥ ግዴታ ነው፤ ኢህአዴግን አለመምረጥ ፀረ ህዝብነት ነው፡፡” የሚሉና ሌሎች ማስፈራሪያዎችን እየሰጡ ነው ሲሉ ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ መምህራንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ከፍለ ከተማ ወረዳ 9 አስተዳደር መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ/ም ነዋሪዎችን ስብሰባ ጠርቶ እንደነበር የሚናገሩት ምንጮቹ “ስብሰባ የተጠራነው ስለአካባቢያችን ልማትና መልካም አስተዳደር ላይ ለመወያየት ተብለን ነው፡፡ ስብሰባውን የመሩት የወረዳው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አሰግድ (የወረዳው ኢህአዴግ ኃላፊ ናቸው፡፡) በስብሰባው ላይ ኢህአዴግን መምረጥ ግዴታ ነው፡፡ በሚል መንፈስ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲናገሩ ውለዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ምንጮቻችን አክለውም “ተሰብሳቢው በበኩሉ በየሠፈሩ ያሉትን ችግሮች እያነሳ ተናግሮአል፤ አንዳንዶቻችን እኛ ጥያቄአችን ምርጫ ሳይሆን የእለት ዳቦ ነው ብንልም ሰብሳቢው ተገቢ ያልሆነ መልስ ሰጥተውናል” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ/ም የመዝናኛ ክበባት ሠራተኞች በክፍለ ከተማ ደረጃ ስብሰባ ተጠርተው ነበር፡፡ ከስብሰባው በኃላ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት “የተጠራነው አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ለመወያየት ተብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግን መምረጥ ግዴታ እንደሆነ መመሪያ ተስቶናል፡፡ የፈለግነውን መምረጥ እንደምንችል ወይም ማንንም አለመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብታችን መሆኑን ሊረዱልን አልቻሉም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ነዋሪነታቸው ያልተረጋገጠና የቀበሌ መታወቂያ የሌላቸው ሰዎች ሁሉ በግዳጅ እንዲመዘገቡና ካርድ እንዲያወጡ ተደርጓል፡፡ የሚል ቅሬታዎች ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በመንግስት ደመወዝ እየተከፈላቸው ሙሉ ጊዜያቸውን የፓርቲውን ሥራ የሚሠሩና በመንግስት የሥራ ሰዓት ሠራተኛቸውን ለፓርቲው ሥራ የሚያውሉ የመንግስት ባለሥልጣናት በሙስና ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰጡ ናቸው፡፡
በመጪው የአካባቢና የአዲስ አበባ መስተዳድር ምርጫ ብቻውን የሚወዳደረው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ላይ ላልመረጥ እችላለሁ በሚል ስጋት ነዋሪዎችንና ሰራተኞችን በስብበሳ ማዋከቡ ብዙዎችን እያስገረመ ነው፡፡
ምንጭ፦ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment