Friday, April 19, 2013

ሰበር ዜና – ‹‹ለፓትርያሪኩ መመሪያ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል›› የተባሉት ኣባይ ፀሃየ ከደጅ ተመለሱ


  • በሦስት ቡድኖ የተደራጀው የጨለማው ቡድን ‹‹የኣባይ ፀሃዬን አመራር›› ያቀናጃል
  • መመሪያው÷ የልዩ ጽ/ቤት፣ ፕሮቶኮል፣ ጥበቃ ሓላፊዎችን ምደባ ይመለከታል ተብሏል
  • ‹‹ኣባይ ፀሃዬ ከስኳር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በበላይነት እንዲመሩ ከመንግሥት ትእዛዝ ተላልፏል፡፡ የትግራይ ተወላጆች የግቢውን አመራር ሙሉ በሙሉ እንረከበዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን በትግራዎት እንጂ በአማራ አትመራም፡፡ ለሚኒስትሮች የሚፈለገውን ጥቅም እያቀረብን እናስፈጽመዋለን፡፡››
/ኣባይ ፀሃዬ ለፓትርያሪኩ የሚሰጡትን ‹‹አመራር›› ከእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ ያስተባብራሉ የተባሉት በምሥራቅ ትግራይ የደብረ ኣላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም አበምኔት አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ ዛሬ ጠዋት የተናገሩት/
  • ፓትርያሪኩ ‹‹አባ›› ነኝ ባዩን ከግቢው እንዲያርቁላቸው መመሪያ ሰጥተዋል፤ ተፈጻሚነት ይኖረው ይኾን?
  • መንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና ምእመኑ ጉዳዩን ከምር አጢነው አቋም እንዲወስዱ ተጠይቋል፡፡
abai-tsehaye-tigraionline
አቶ ኣባይ ፀሃዬ
ከአምስተኛው ፓትርያሪክ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ፣ የመንበረ ፓትርያሪኩን ላዕላይ መዋቅሮች በመቆጣጠርና ለተቋማዊ ለውጥ የታቀዱትን ተግባራት በማምከን÷ 1)ቡድናዊና ግለሰባዊ ጥቅሙን አስጠብቆ ለመቆየት፣ 2)ኦርቶዶክሳዊ ማንነትን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ደብዛውን ለማጥፋት በልዩ ኹኔታ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የጨለማው ቡድን÷ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በጎጠኝነት፣ በፖሊቲካዊ ታማኝነትና በጥቅም ስቦ እና አቅርቦ ማሰለፍ መጀመሩ ተዘገበ፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎችና ድርጅቶች ውስጥ በሓላፊነት ደረጃ የተቀመጡ ጥቅመኞችን ጨምሮ የታወቀ ሹመት የሌላቸውን ነገር ግን የሁሉ ፈጣሪና ገባሪ ለመኾን ‹‹ሥልጣን›› ያገኙ ግለሰቦችን የሚያካትተው የጨለማ ቡድኑ÷ በፓትርያሪኩ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ላይ ማሰለፍ የጀመረው ‹‹የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ነው›› ተብሏል፡፡ ቡድኑ በዚህ ስትራተጂው የህወሓት/ኢሕአዴግን ባለሥልጣናት ተጽዕኖ በመጠቀም በማንኛውም ቦታ በተለይም በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር ላይ ተጽዕኖውን ለማጠናከርና ያሻውን ለመፈጸም ማቀዱ ነው የተነገረው፡፡
ይኸው ስትራተጂ ባለፉት ኻያ ዓመታት መንበረ ፓትርያሪኩ ለክፍፍልና ትርምስ የተዳረገበት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለጥቃትና ድብደባ የተጋለጡበት እንደነበር ያስታወሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ስልቱ በመልኩ አዲስ ባይሆንም በይዘቱ ግን ቡድኑ የተለየ ቁመና ይዞ የተደራጀበት መኾኑን ያስረዳሉ፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ፅልመታዊ ቡድኑ ለሦስት ኀይል ተከፍሎ በተለያዩ ግለሰቦች የሚመራ ሲሆን የተመረጡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እየተፈራረቀ በመወትወት/በማግባባት ተመሳሳይ ጉዳይን ከተለያየ አቅጣጫ እያስተነተነ ስለጉዳዩ አንድ ዐይነት ቀለም/ሥዕል ለመፍጠር ግፊት ያሳድራል፤ ለኾነ ርምጃ የሚያበቃ ውሳኔ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ በዚህም ቡድኑና አባላቱ ለመንግሥት ቀራቢና ተቆርቋሪ፣ ለቤተ ክርስቲያን አሳቢ መስለው ጋርዮሻዊና ግለሰባዊ ጥቅማቸውንና ሥልጣናቸውን ያስጠብቃሉ፡፡
ለሦስት ኀይል የተከፈለውን ‹‹የጨለማ ቡድን›› የሚመሩት ግለሰቦች፡-
  • አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ – በምሥራቅ ትግራይ የደብረ ኣላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም አበምኔ
  • አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል – በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ሓላፊ                              
  • ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ – በመዋቅር የማይታወቀው የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ                           
በአሁኑ ወቅት በሦስት ኀይል የተደራጀው የጨለማ ቡድን ከውጭ ኀይል ይሰጠዋል በተባለ አመራር፣ የመንበረ ፓትርያሪኩን ከፍተኛ መዋቅሮች ለመቆጣጠር በሚያደርገው መፍጨርጨር፣ ለዓላማዬ ዕንቅፋት ናቸው ብሎ በሚያስባቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎችና በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ላይ መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደ ነው፤ ለዚህም የፓትርያሪኩ ድጋፍ እንዳለው አስመስሎ ነው መቀሳቀስ የያዘው፡፡ እንዲያውም ከመረጃው ምንጮች አንዳንዶቹ÷ አዲሱ ፓትርያሪክ ‹‹ሳያውቁ በቡድኑ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርተው ለመወሰንና የውሳኔያቸውን አፈጻጸም ለመከታተል በማይችሉበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡
ምንጮቹ ለዚህ ድምዳሜያቸው በአብነት የሚጠቅሱት፣ ከየካቲት ወር አጋማሽ አንሥቶ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት እና በአስተዳደሩ መካከል የተነሣውን ውዝግብና አያያዙን ነው፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ውዝግቡ በአጭር ጊዜ እልባት እንዲሰጠው አይፈለግም፡፡ ለዚህም ጣታቸውን የሚቀስሩት ‹‹ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በደብዳቤ የተሠየመኹትና የሚመለከተኝ እኔን ብቻ ነው፤›› በሚሉት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያው ሓላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ላይ ነው፡፡
ከደቀ መዛሙርቱም ከሓላፊዎቹም መካከል ምንጮቹ በስም የሚጠቅሷቸውን ግለሰቦች በመያዝ ውዝግቡን ሳብ ረገብ እያደረጉ ይዘዋል የተባሉት አባ ሠረቀ ብርሃን፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ ፓትርያሪኩን እንዲያነጋግር ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ኣባይ ፀሃዬ ጋራ መክረዋል ተብሏል፡፡ አባ ሠረቀ ብርሃን ታዲያ ይህን የሚያደርጉት፣ በርግጥም አካዳሚያዊ መብታቸውንና መልካም አስተዳደርን በመጠየቃቸው በረኀብ እየተቀጡ ላሉት ደቀ መዛሙርት ከአንጀት በማዘን አይደለም፡፡
አባ ሠረቀ ብርሃን ችግሩም መፍትሔውም በግልጽ የሚታወቀውን የደቀ መዛሙርቱንና የአስተዳደሩን ውዝግብ ከዐውዱ ውጭ እያወሳሰቡ በስም የተጠቀሱትን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ወትውተዋል፡፡ በዚህም ጥንተ ጠላታቸው ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም እና ‹‹የማኅበሩን ተልእኮ የሚያስፈጽሙ ናቸው›› የሚሏቸውን የኮሌጁን ሓላፊዎች እንደ ግለሰብ በከፍተኛ ደረጃ ወንጅሎ (አንዱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ እንደወሸከተው) ፖሊቲካዊም አስተዳደራዊም ርምጃ እንዲወሰድባቸው የማድረግ ፍላጎታቸው የናረ ኾኗል፡፡ እስከ መጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በማሰንበትም ጉዳዩ ተለጥጦና ዐቢይ አጀንዳ ኾኖ ውሳኔ እንዲተላለፍበትም ነው ዕቅዳቸው፡፡
ሳይገባቸው በተቀመጡበት መምሪያ ረብ ያለው ቁምነገር ለመፈጸም አቅሙም ዝግጁነቱም የሌላቸው አባ ሠረቀ ብርሃን፣ ለዚህ አካይስት አድራጎታቸውና ዕቅዳቸው ተባባሪ አላጡም፤ በቀደሙት ዘገባዎቻቸው እንዳስነበብነው የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር በማሰናከል የሚያግዟቸው የፅልመታዊ ቡድኑ የበላይ ተቆጣጣሪ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ አሉላቸው፡፡ ንቡረ እዱ የፓትርያሪኩ አማካሪ መስለውና ራሳቸውን በአማካሪነት ሾመው በቀጣይ የፓትርያሪኩን ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት መመሪያ ለመቆጣጠር አቶ ኣባይ ፀሃየ ለፓትርያሪኩ ‹‹የሚሰጡላቸውን መመሪያ›› የሚጠባበቁ ናቸው፡፡
ሐራዊ ምንጮች በደረሰው ጥቆማ መሠረት፣ አቶ ኣባይ ፀሃየ ለፓትርያሪኩ መመሪያ እንዲሰጡ ማግባባት ያደረገው በምሥራቅ ትግራይ የደብረ ኣላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም አበምኔት ነኝ የሚሉት አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ‹‹አባ›› ነኝ ባዩ ገብረ መድኅን አበምኔት ነኝ በሚል በስሙ ከሚነግዱበትና ለሀ/ስብከቱ ከማይታዘዙበት ገዳም ‹‹አበምኔትነት›› በቀር በመንበረ ፓትርያሪኩ ይህ ነው የሚባል ሹመት የሌላቸው ናቸው፤ በገዳማት ርዳታ ስም ከፍተኛ ፈንድ ለማጋበስ የቋመጡባትን የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊነት ለቀም እስኪያደርጓት ድረስ!!
የአሲራ መቲራው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በሽግግሩ ወቅት ፊት በሰጧቸውና አለመጠን ባቀረቧቸው ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ተሸጋግረው ከቀድሞም ባደለቡት የዝርፊያ ሀብት ላይ አያሌ የግል ሀብት ለማካበት ኹኔታዎችን አመቻችተዋል፤ ራሱን በዳግም አደረጃጀት ባጠናከረው ፅልመታዊ ቡድን ውስጥም በቅድመ ግንባር የተሰለፉ፣ ስንኳን ለመነኲሴ ለሰብአ ዓለም አጸያፊ በኾኑ የድፍረት ኀጣውእ ተሰነካክለው በማሰነካከል የታወቁ፣ በሄዱበት የማይለዩትን ሽጉጥ በሠባራ ሰንጣራው ምክንያት ባገኙት ላይ (በሀ/ስብከታቸው ሊቀ ጳጳስ ላይ ሳይቀር) እየመዘዙ የሚደነፉ ግልፍተኛ ናቸው፡፡
የሹመት ተስፈኛው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
ዝርዝሩ ለኋላ ይቆየንና ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ባለፉት ሦስት ቀናት በአቶ አባይ ፀሃየ ላይ አካሂደውታል በሚባለው ውትወታ÷ በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ግንኙነት መምሪያ፣ የፓትርያሪኩ መጋቤ ሥርዐት (ፕሮቶኮል)፣ የጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ(የግቢ) ጥበቃ ሓላፊ መኾን የሚገባቸውን ሰዎች መልምለውና አሳምነው እንደጨረሱ ከራሳቸው አንደበት በዛሬው ዕለት ሲነገር ተደምጧል፡፡ ካለፉት ኻያ ዓመታት ልምድ ለመገንዘብ እንደሚቻለው እኒህ የሓላፊነት ቦታዎች (በቀጣይ እስካልተስተካከሉ ድረስ)÷ ፓትርያሪኩን በመቆጣጠር፣ ባለጉዳዮችን በማጉላላትና የቤተ ዘመድ ሰንሰለት በመዘርጋት አስከፊ ሙስናና በቤተ ክርስቲያን ስም ሕገ ወጥ ተግባራት የሚፈጽምባቸው እንደነበሩ አሌ አይባልም፡፡
ለአስረጅነት እንዲኾን ከሙስናውም ከሕገ ወጥ ተግባሩም አብነት እንጥቀስ፡፡ ፓትርያሪኩ እንደተሾሙ ሰሞን ‹‹አላምዳለኹ፤ አማክራለኹ›› በሚል ተጠግተው ቢሯቸውን በዚያው በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ ያደረጉት ንቡረ እድ ኤልያስ በቤተ ክርስቲያኗ ስም በሚደረግ ትብብር ሁለት ሰዎችን ገንዘብ ተቀብለው ወደ አሜሪካ ለመላክ ያደረጉት ሙከራ ተይዞባቸዋል፡፡ በመለያ ስሙ ‹‹ሃይለ ሰይጣን›› የሚባለውና በቀድሞው ፓትርያሪክ እገዛ በዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሕገ ወጥ ሹመቶች የተደራረቡለት ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ከፓትርያሪኩ ምርጫ ወቅት ጀምሮ በአዲስ አበባ ይገኛል፡፡
ሃይለ ሰይጣን የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ በኾኑት አቡነ ገሪማ አማካይነት ከአዲሱ ፓትርያሪክ ጋራ ዕውቂያውንና መቀራረቡን ማጠናከሩ ይነገራል፡፡ የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑ ኦርቶዶክሳዊነት በሌለው ፕሮቴስታንታዊ ማንነቱ ያገኘው ሕገ ወጥ ሹመት ኾኖ ሳለ፣ በልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ አስፈጻሚነትና በእነ ንቡረ እድ አስተናባሪነት የቀድሞው የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ሠራተኞቻቸው የደከሙበትን ሀ/ስብከትና መንበረ ጵጵስና ሳይገባው ለመረከብ የሚያስችለውን ደብዳቤ ሰሞኑን አጽፎ ወደዚያው ለመብረር ተዘጋጅቷል፡፡
ሃይለ ሰይጣን ለመልስ ጉዞ ሲዘጋጅ የያዘው ሰለባ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በቆይታው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የታገደውንና ደርሶ ማኅበረ ቅዱሳንን እገዳደራለኹ ባዩን ‹‹የጉባኤ አርድእት›› ጉዳይ ከግንባር ቀደም የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆችና ሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋራ በመኾን በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በአዲስ መልክ በተዘጋጀው የሃይማኖት ማኅበራት ምዝገባ ሕግ ፈቃድ አግኝቶ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከመሰሎቹ ጋራ ጅር ጅር ሲል ሰንብቶ ነው የሚሄድ፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ ሰሞኑን ‹‹አባ›› ገብረ መድኅንና ፅልመታዊው ቡድን በሚያካሂዱት ውትወታ ታዲያ የውጭ ግንኙነት መመሪያውንና የልዩ ጽ/ቤት ሓላፊነቱን ጠቅልለው በመረከብ ይመራሉ የሚባሉት ‹‹ሰይጣንን በዘመን እንጂ በተንኰል እንደሚወዳደሩት›› የሚነገርላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ የፓትርያሪኩ መጋቤ ሥርዐት (ፕሮቶኮል) እንዲኾኑ አሳምኜ መልምያቸዋለኹ የሚሏቸው ደግሞ አቶ ተወልደ በኀይሉ የተባሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ አሁን በዜግነትና ኤሚግሬሽን ጉዳይ ሠራተኛ መኾናቸው ይነገራል፡፡ ግለሰቡ በ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ምልመላና ማግባባት የመንግሥት ሥራቸውን ለቀው የፓትርያሪኩ ፕሮቶኮል ለመኾን እንደተስማሙ ከራሳቸው ከአባ ገብረ መድኅን በዛሬው ዕለት ተሰምቷል፡፡ ሌላው የአባ ገብረ መድኅን ምልምል ለጊዜው ስማቸው ተለይቶ ያልተገለጸና በቀድሞው የግቢው ጥበቃ ሓላፊ አቶ ብርሃኔ ኀይሉ ላይ/ምትክ የሚሾሙ ሰው ናቸው፡፡
በ‹‹አባ›› ገብረ መድኅንና በጨለማው ቡድን ዕቅድ መሠረት፣ እኒህ ሦስት የሓላፊነት ቦታዎች ተይዘው ሲያበቁ በቀጣይ ካነጣጠሩባቸው የአስፈጻሚው አካል (የጠቅላይ ቤተ ክህነት) የሓላፊነት ቦታዎች አንዱ የበጀትና ሒሳብ መምሪያው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ መምሪያ ላይ እየሠሩ የሚገኙት ሓላፊዎች የማኔጅመንትና አካውንቲንግ ሥልጡኖች ናቸው፡፡ ከትውፊታዊውም ከዘመናዊውም ትምህርት የሌሉበት እነአባ ገብረ መድኅን ግን እኒህን ባለሞያዎች አስወግደው መመለስ የሚፈልጉት ገብረ መስቀል ድራር የተባሉ የአስተሳሰብና ተግባር መሰላቸውን ነው፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የበጀትና ፋይናንስ መመሪያ ከተነሡ በኋላ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የቁጥጥር ሓላፊው ገብረ መስቀል ድራር የሁለት ቪላዎች ባለቤት ከመኾናቸውም በላይ ለዓመታት ያካበቱት ገንዘብ ‹‹ባንኩን አጣቦታል›› በሚል ይወራባቸዋል፡፡
እንግዲህ እነ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን÷ ‹‹የትግራይ ተወላጆች የግቢውን አመራር ሙሉ በሙሉ እንረከበዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን በትግራዎት እንጂ በአማራ አትመራም፡፡ ለሚኒስትሮች የሚፈለገውን ጥቅም እያቀረብን እናስፈጽመዋለን›› የሚሉት በእኒህ ስንኩል ግለሰቦች በሚዘወሩ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ መዋቅሮች አማካይነት ነው፤ ትግራዎት በእኒህ የአስተሳሰብና የተግባር ስንኩላን ሊወከሉም ሊጠሩም አይችሉም፤ አይገባቸውም እንጂ!
የዜናው ምንጮች፣ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅንና የጨለማው ቡድን ይህን ፍላጎታቸውን በዛሬው ዕለት አቶ ኣባይ ፀሃዬን ከፓትርያሪኩ ጋራ በማገናኘትና ፓትርያሪኩን በማግባባት ለመጨረስ ዕቅድ ነበራቸው፡፡ አልያዘላቸውም እንጂ!
በእነ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ፕሮግራም መሠረት፣ አቶ ኣባይ ፀሃዬ ዛሬ፣ ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡15 ላይ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ገብተው በደጃፉ ቆመው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ታይተዋል፤ እየመሯቸው የገቡትም ሲወተውቷቸው የሰነበቱት ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ አመጣጣቸው ግን በመንገደኛው ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ቀጠሮ እንጂ እንደ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ወጉን (ፕሮቶኮሉን) የጠበቀ አልነበረምና የፈለጓቸውን ‹‹መመሪያ ተቀባይ›› አላገኟቸውም፤ ‹‹መመሪያ ተቀባዩም ለስብሰባ ወጥተው በቢሯቸው አልነበሩም፤›› ይላሉ ምንጮቹ፡፡ በርግጥ አቶ ኣባይ ‹‹መመሪያ ሊሰጧቸው ተዘጋጅተውባቸዋል›› በተባሉት ቅዱስነታቸው ምትክ እዚያው በቆሙበት በአልፎ ሂያጅ ካገኟቸው ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ተቀብለዋል፡፡ ከዚህ በቀር ጨዎታቸው ከግቢው ጥበቃ አባላት ጋራ ነበርና ከቆይታ በኋላ በመጡበት አኳኋን ተመልሰዋል፡፡
ይህም ስለሆነ የስኳር ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ኣባይ በዛሬ ዕለት ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ መጥተው ከደጃፍ ስለተመለሱበት ጉዳይ በግልጽ የተረጋገጠው፣ ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በተመለደ ግልፍተኝነታቸው ድምፃቸውን አሰምተው ሲናገሩ ካደመጧቸው እማኞች ነው፡፡ እማኞቹ ለሐራዊ ምንጮች እንደመሰከሩት፣ ኣባይ ፀሃየ በዛሬው ዕለት ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ የመጡት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ መመሪያ ለመስጠት እንደነበር ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን በበስጭት ተናግረዋል፡፡ በአጭሩ በብዙ እማኞች የተረጋገጠው የ‹‹አባ›› ገብረ መድኅን ቀጥተኛና አሳዛኝ አነጋገር የሚከተለው ይዘት ነበረው፡-
‹‹ለፓትርያሪኩ አመራር ሊሰጡ ነበር የመጡት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በኋላ በትግራዮች እንጂ በአማራ አትመራም፡፡ የፓትርያሪኩን ፕሮቶኮል በቅርቡ አስመጥቼ ጨርሻለኹ፡፡ የጥበቃ ሓላፊውንም አስመጥቼ ጨርሻለኹ፡፡ ከዚህ በኋላ በኣባይ ፀሃዬ መሪነት ቤተ ክርስቲያን ትመራለች፡፡ መንግሥት ኣባይን ከስኳር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በበላይነት እንዲመሩ ትእዛዝ ተላልፏል፡፡ የትግራይ ተወላጆች የግቢውን አመራር ሙሉ በሙሉ እንረከበዋለን፡፡››
በዕሥራ ምእቱ መባቻ ሙስናን፣ የዘመድ አዝማድና ዐምባገነናዊ አስተዳደርን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለማስወገድ ተደርጎ የነበረው ትግል ብፁዓን አባቶችን በመከፋፈል፣ ከዚያም አልፎ በማንገላታት መምከኑን ያስታወሱ የዘዜናው ምንጮች ‹‹አቶ ኣባይ አሁን ደግሞ ምን ቀራቸው?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ጉዳዩን መንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራርና ካህናትና ምእመናን ሁሉ የምር ሊያስቡበት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡
በርግጥ በሐራዊ ግምገማ፣ ፓትርያሪኩ በጨለማው ቡድን አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ መደምደሙ ከጊዜው የቀደመ ይመስላል፡፡ የፓትርያሪኩ አቋም በጣልቃ ገብነት የቅ/ሲኖዶሱን አቋምና የቤተ ክህነቱን አሠራር የሚያበላሹትን ‹‹ድሮም አሁን እቃወማለኹ፤ አልፈቅድም›› ሲሉ አረጋግጠዋልና፡፡ ‹‹ሰውን መጥላትም መውደድም የምንችለው በዘሩ ሳይሆን በግብሩ ነው፤ አንድ ሰው ሊመሰገፈንም፣ ሊሾምም ሊሻርም ሊወቀስም የሚገባው በጠባዩ፣ በግብረ ገብነቱ፣ በትምህርቱ ብቻ እየተመዘነ መኾን አለበት፤›› በማለት ጎጠኝነትን በዐደባባይ አውግዘዋልና፡፡ ‹‹የተሟላና የተቃና ሥራ ለመሥራት ከሁሉ አስቀድሞ ብቃትና ጥራት ያለው ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰው በሰው ላይ መደራረብ ሳይሆን ትምህርትና ችሎታ ያለው፣ ለተመደበበት ሥራ የሚመጥን ሰው መቀመጥ አለበት፡፡ ለዚህች ታላቅ መንፈሳዊ ተቋም የሚመጥኑ ሰዎች መቀመጥ አለባቸው፡፡ ቅ/ሲኖዶስ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል የሚል እምነት አለኝ፤›› በማለት ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ በማስቀመጥ ተቋማዊ ለውጡን ወደፊት ለማራመድ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋልና!!

No comments:

Post a Comment