Wednesday, April 3, 2013

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ ያቀረቡ የሀገር ሽማግሌዎች ታሰሩ


በዘሪሁን ሙሉጌታ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን ቁጫ ወረዳ የሚኖሩና በወረዳዋ የልማትና የማንነት ጉዳይ ላይ ጥያቄ
አንስተዋል የተባሉ ዘጠኝ የሀገር ሽማግሌዎች መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።
… ነዋሪዎቹ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በወረዳዋ ከልማትና ከማንነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው 22 ጥያቄዎችን
በመያዝ ከ2001 ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ የደቡብ ክልል የአስተዳደር አርከኖች ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ
ባለማግኘታቸው ጥያቄአቸውን ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲሁም ለፌዴሬሽን ም/ቤት ቢያቀርቡም ተገቢውን
ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል። በቅርቡም በድጋሚ ጥያቄአቸውን በመያዝ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
አቅርበው ወደ ወረዳዋ ከተመለሱ በኋላ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በቁጫ ወረዳ ዋና ከተማ ሰላም በር ፖሊስ
ጣቢያ መታሰራቸውና ከመጋቢት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውን ተናግረዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ከወረዳው አስተዳደር በላይ የወረዳውን ነዋሪ የማስተባበር ስራ በመስራታቸውም በአስተዳደሩና ሕዝቡ
መካከል ግንኙነቱ መቋረጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ ከ25 ጊዜ በላይ
ለክልሉና ለፌዴራል የመንግስት አካላት ጥያቄአቸውን አቅርበው ምላሽ ባለማግኘታቸው የወረዳው ሕዝብ ልጆቹን
ወደትምህርት ቤት እንዳይልክ፣ ግብር መክፈል እንዲያቆም፣ የኢህአዴግ አባላት ጭምር ማናቸውንም የልማት መዋጮ
እንዳይከፍሉ፣ ሕዝቡ አስተዳደሩ በሚጠራው ስብሰባ እንዳይወጣ፣ ከወረዳው ርዕሰ ከተማ ሰላም በር ካድሬዎች ወደ ሌሎች
ቀበሌዎች በተሽከርካሪ እንዳይገቡ መንገድ በመዝጋት፣ ሞዴል አርሶ አደሮችን ጨምሮ አንድ ለአምስት አደረጃጀት መዋቅር
ስር ከተደራጁ አካላት ጋር ሕዝቡ እንዳይተባበር በማድረግ የወረዳው አስተዳደርና በነዋሪው መካከል ግንኙነቱ ሙሉ
በሙሉ እንዲቋረጥ ለማድረግ መቻላቸውና በአሁኑ ወቅትም አስተዳደሩ ግብር መሰብሰብም አለመቻሉን ቀደም ሲል በወረዳው
ነዋሪዎች አስተባባሪነት በተሰራው ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርት እንዲያቆሙ በማድረግ ጥያቄአቸውን ወደአጠቃላይ
ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲያመራ ማድረጋቸው ለወረዳው ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልፀዋል።
የነዋሪዎቹ ተወካዮች ወደዚህ እርምጃ ቢገቡም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በወላይታ ዞን መንገድ
ለመጎብኘት ሲመጡ፤ ጥያቄአቸውን በአካል ማቅረባቸውንም ነዋሪዎቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።
ጥያቄ አቅራቢዎቹ በወረዳው ካነሱት የአስተዳደራዊ ጥያቄዎች በተጨማሪ የማንነት ጥያቄ በማንሳት ቁጫ እና ጋሞ
በቋንቋና ባህል የተለየ በመሆኑ በልዩ ወረዳ ይተዳደር፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ የተሰራው ትምህርት ቤት ስራ ይጀምር፣
ንፁህ ውሃና መብራት እንዲሁም የፍትህና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ይመለሱ የሚሉ ይገኙባቸዋል።
በወረዳው ሕዝብ ተወክለዋል የተባሉትና በአሁኑ ወቅት በአርባ ምንጭ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት የሀገር ሽማግሌዎች
መካከል አባባ ጫንቃሎ አያና የ94 ዓመት አዛውንት፣ አቶ በቀለ ካሳ፣ አቶ ማቲዎስ ዱማ፣ አቶ ኤልያስ አራሰ፣ አቶ
ባርሲሳ ባሣ፣ አቶ ታደሰ ሻራ፣ አቶ ዮሴፍ ዲቻ፣ መምህር ሚልኪያስ ባሳ እና አቶ አዳነ ካሳ መሆናቸውን የነዋሪዎቹ
ጥቆማ ያስረዳል።
የቁጫ ወረዳ አስተዳደር አቶ የስጋት ሰንታ ስለጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው ሲመልሱ የተጠቀሱት ሰዎች መታሰራቸውን
አምነዋል። አቶ የስጋት ግን ጉዳዩን በተመለከተ ጋዜጣው የግል ወይም የመንግስት መሆኑን ከጠየቁን በኋላ የሚከተለውን
ምላሽ ሰጥተዋል።
“ማንም ሰው የሕግ የበላይነት ስላለ ይጠየቃል። ስለዚህ ማንንም ጋዜጠኛ አምጥተው ባስቀረፁ ወይም ባስጠየቁ አይደለም
ምላሽ የሚያገኙት። ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች የተጠየቁት ወይም የታሰሩት ትምህርት ቤትን ከመዝጋት ጋር በተያያዘ ነው።
ሕገወጥ ስብሰባዎችና ሰልፎችን ሰዎችን ሲቀሰቅሱ ትምህርት ቤቱን ሲዘጉ ነው። ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የዞኑ
ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለሆነም ፍርድ ቤቱን ይበልጥ መጠየቅ ትችላላችሁ” ካሉ በኋላ “ሰዎቹ ተጠርጥረው ተይዘዋል።
ጉዳያቸው በሕግ ተጣርቶ ጥፋተኛ ካልሆኑ ይለቀቃሉ ጥፋተኛ ከሆኑ ደግሞ በሕግ ይጠየቃሉ” ሲሉ መልሰዋል።
በተጨማሪም አቶ የስጋት ሰዎቹ የመንግስት አካላትን መጠየቅ ሲገባቸው ጋዜጠኛ ያስፈታናል ብለው መጠየቃቸው
እንዳስገረማቸው ገልፀዋል። ነገር ግን ጉዳያቸውን ሕዝብ እንዲያውቅላቸው አስበው ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ተገቢ
መሆኑን ብንገልፅላቸውም “ጠቅላላ የ32 የቁጫ ቀበሌ ሕዝብ ያውቃቸዋል” ሲሉ መልሰዋል።
የታሰሩት ሰዎች የግብርና ስራ በተለይም የተፋሰስ ስራ እንዲቆም አድርገዋል የሚሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ 36 ሺህ
በላይ የቀበሌ ሕዝብ ግብር እንዳይከፍል በማድረጋቸው ወረዳው አምስት ሳንቲም አላገኘም፣ በሕጋዊ ስብሰባዎች ላይ
ሰዎች እንዳይሳተፉ አድርገዋል። ሕጋዊ ስብሰባን ለመምራት የሄዱ አመራሮችን አባረዋል ብለዋል።
የታሰሩት የሀገር ሽማግሌዎች ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል የመብራት ይግባልን ጉዳይ እየተጠና መሆኑን መንገድም
እስከ ቀበሌአቸው እየተሰራ መሆኑን ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት ተሰርቷል ያሉት አስተዳዳሪው የሀገር ሽማግሌዎቹ
በአመፅ የሚገኝ ምንም ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል ብለዋል። አሁን በተፈጠረው የነዋሪዎቹና የአስተዳደሩ ውጥረት
ሳቢያም በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 600 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውንም የወረዳው አስተዳዳሪ አምነዋል።
በጉዳዩ ላይ የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ ቱማ አየለን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ነገር ግን ለዞኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ከዚህ ቀደም የዞኑ አስተዳዳሪ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናትን በመያዝ
ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ቢያደርጉም ባለመግባባት መቋጨቱን ገልፀውልናል።
በ2002ቱ ምርጫ መድረክን በመወከል በወረዳው ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በወረዳው መሠረታዊ የመልካም
አስተዳደር ችግር መኖሩን፣ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ዲክላሬሽን ልጆች በአፍ መፍቻ
ቋንቋቸው እንዲማሩ ቢደነግግም የቁጫ ተወላጆች በጎሞ ቋንቋ እንዲማሩ መገደዳቸውን እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር
ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው እንዲፈቱ ሲሉ አሳስበዋል።
የቁጫ ወረዳ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን የምትገኝ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ በ420 ኪሎ
ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ ነች።
ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment