Sunday, April 21, 2013

**የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች**


በአባይ ስም ከዲያስፖራዎች ገንዘብ ለመለመን እየሞከረ ያለው ወያኔ አሳፋሪ ውርደት መከናነቡን ቀጥሎአል። ቴዎድሮስ አድሃኖምን ከደቡብ አፍሪካ እያሯሯጡ ያባረሩት ዲያስፖራዎች በአሜሪካ ግርማ ብሩን አፉን ያስያዙት ሲሆን በኖርዌይ በትላንትናው እለት በተካሄደ ስብሰባ የወያኔዋን ተወካይ መብራት በየነን ከስብሰባው አባረዋታል። ኢትዮጲያውያኑ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ሳይገድባቸው በህብረት ኢህአዴግን ማዋረድ የቀጠሉ ሲሆን እዚህ ሃገር ቤት ውስጥ ያሉ የመብት ጥሰቶች መፍትሄ ሳያገኙ አባይ አባይ ብሎ መጮህ ዋጋ የለውም ብለዋል።
———
በቤንሻንጉል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ሁኔታ አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ሲሆን ወደ ቦታቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች የአካባቢው ህዝብ አብሮአቸው እንዳይሰራ እና ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ በወያኔ እየተገፋፋ ነው። ንብረታቸው እና እርሻቸው የወደመባቸው ተፈናቃዮች የሚሰጣቸው የምግብ እርዳታ በሽታ እያመጣባቸው ሲሆን የአካባቢው ህዝብ የአማራ ተወላጆችን ስራ እንዳይቀጥር፣ አገልግሎት እንዳይሰጥ እና እርሻ ቦታም እንዳይተባበራቸው ዘመቻ ተከፍቶአል። መኢአድ መረጃዎች በማጣራት በቦታው ከ2000 በላይ የትግራይ እንዲሁም ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች እና ከ60 በላይ የህውሃት ታጋዮች ሰፋፊ የግል እርሻ በአካባቢው ያለ ሲሆን ጥቃቱ ሆን ተብሎ የአማራ ተወላጆች ላይ መነጣጠሩ አለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፍ ፍርድቤት ለመውሰድ ማሰቡን ተናግሮአል። የሰማያዊ ፓርቲ አመራርም ሁኔታውን ለማጣራት በቦታው በተገኙበት ወቅት ሳታስፈቅዱ ወደ ክልሉ ገብታችኋል በሚል ከታሰሩ ከሰአታት በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል።
———
ባለፈው ሳምንት የነበረው ምርጫ ላይ ባዶ የተመለሱ ወረቀቶች እና ስድቦች እጅግ መብዛት ያስደነገጠው ኢህአዴግ ህዝቡ ውስጥ ያለውን ሰፊ ተስፋ መቁረጥ ተቃዋሚዎች በቀላሉ ለአመጽ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ የፖሊስ እና ደህንነት ሃይሉ ነቅቶ ካልጠበቀ ኢህአዴግ ሊያበቃለት እንደሚችል እያስጠነቀቀ ነው። አባላቶቹን ‘ኢህአዴግ ከወደቀ ህዝቡ እናንተን ነው የሚበላው’ እያለ በማስፈራራት ሰፊ የስለላ ስራ እንዲሰሩ እየጠየቀ ሲሆን በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች ሁኔታዎች ጠንከር ተደርገው እንዲታዩ አሳስቦአል።
በመረጃ የዳበረ ህዝብ አምባገነኖችን ቀባሪ ነው!!
#ፀረአምባገነን

No comments:

Post a Comment