Friday, April 26, 2013

አዋሽ ወንዝ በጥቂት ወራት ውስጥ የሚሊዮኖችን ህይወት ለአደጋ አጋልጦ ከጥቅም ውጭ ሊሆን ይችላል ተባለ



ኢሳት ዜና:-ብሉበርግ ትናንት ይዞት በወጣው አስደንጋጭ ዘገባ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የበሰቃ ሀይቅ በመስኖ ስራዎች እና በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ምክንያት ጨዋማነቱ በ15 እጥፍ በመጨመሩ በሰኔ ወር ዝናብ ከዘነበና  ሀይቁ ወደ አዋሽ ወንዝ መፍሰስ ከጀመረ ፣ ወንዙን ለመጨረሻ ጊዜ ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል ሲል ጠቅሷል።.
ስራ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የአፈር መሸርሸርና በመሬት የውስጥ እንቅስቃሴ ምክንያት ጨዋማነቱ ከመጠን በላይ እየጨመረ በመሄዱ የሚሊዮኖችን ህይወት ለአደጋ አጋልጧል።
በውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከርሰ ምድር ውሀዎች ዋና ሀላፊ የሆኑት አቶ ተስፋ ታደሰ ፣ “ሀይቁ በራሱ ጊዜ ወደ አዋሽ መፍሰስ ከጀመረ የአዋሽ ወንዝ ለዘላለሙ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።” ብለዋል።
የላይሻው አዋሽ ወንዝ የውሀ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ  እንደሻው ታደሰ  ደግሞ የሰኔ ዝናብ ከመዝነቡ በፊት ሀይቁ ወደ አዋሽ ወንዝ እንዳይፈስ ወሳኝ ጥረት መደረግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ባለሙያው እንደሚሉት ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ የሚገኘው ሀይቅ ወደ ወንዙ ከፈሰሰ ከተሞችን ከማጥለቅለቅ አልፎ የአካባቢውን አርብቶ አደሮች ሊያፈናቅላቸው ይችላል።
ብሉበርግ እንደሚለው መንግስት ላለፉት 14 አመታት የውሀ ፓምፖችን በመጠቀምና ቦዮችን በመስራት በሰቃን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም አልተሰካላትም።
በአለማያ ዩኒቨርስቲ የሲቪል ኢንጂነርግ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መገርሳ  ዲንቃ እንደተናገሩት በአካባቢው የሚደረገው የመስኖ ስራ  ችግሩን አባብሶታል። ፕሮፌሰሩ የመሬት እንቅስቃሴው ለሀይቁ መስፋፋት ተጨማሪ አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በላይኛው አዋሽ ላይ ሲካሄድ የነበረው የመስኖ እንቅስቃሴ ችግሩን እንዳባባሰው ለማመን ተገደዋል።
በመተሀራ አካባቢ ያለውን የላይኛው የአዋሽ አግሮ እንዱስተሪ ኢንተርፕራይዝ፣ የሼክ ሙሀመድ አላሙዲ ንብረት የሆነው ሆራይዞን ፕላንቴሽን በቅርቡ መግዛቱ ይታወሳል። የሆራይዞን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ እንዳሉት በላይኛው አዋሽ ላይ የሚካሄደው የመስኖ ስራ ምንም አይነት የአካባቢ ተጽኖ አላመጣም፤ ይሁን እንጅ ድርጅታቸው ችግሩን ለማጥናት ከመንግስት ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነው ብለዋል።
የበሰቃ ሀይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ ከፈሰሰ 23 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የሼክ ሙሀመድ አላሙዲ ድርጅት፣ ከህንድ አገር በተገኘ የ640 ሚሊዮን ዶላር ብድር የማስፋፍያ ስራ የሚሰራለት የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ 30 ሺ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው  መተሀራ እና አዲስ ከተማ እንዲሁም የመተሀራና የተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ።ው በመካከለኛው አዋሽ አካባቢ ያለው የአምቢባራ ቢዝነዝ ግሩፕ ንብረት የሆነው የጥጥ እርሻ እና በአጣቃላይ ድምራቸው 5 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያላቸው ፕሮጀክቶች በሙሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ።
“ሰኔ ላይ ዝናብ ከዘነበ ሁሉም ነገር ተፈጸመ” ሲሉ የውሀ ባለሙያው  አቶ እንዳሻው አስጠንቅቀዋል።
የበሰቃ ሀይቅ ጨዋማነት እየተፋጠነ የመጣው የክልሉ መንግስት በ467 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመስኖ ስራ የሚያገለግለውን የፈንታሌ ቦይ መገንባት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች፣ ዲዛይን እና ሱፐር ቪይዢን ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እንግዳ ዘመድኩን ተናግረዋል።
ውሀ በፓምፕ ለማስወጣት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፣ የሚሉት የመንግስቱ ባለስልጣን አቶ ተስፋየ ደግሞ አዋሽ ወንዝ በራሱ 4 በመቶ ጨውነት ያለው በመሆኑ ከዚህ መጠን ካለፈ ውሀውን ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል ብለዋል።
ፕሮፌሰር መገርሳ ደግሞ ” የሀይቁ ጨውነት በምንም ይጨምር በምንም፣  በሰቃ ሀይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ መፍሰሱ እና የመተሀራ ስኳር ፋብሪካን በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ ማውደሙ አይቀሬ ነው።  ተንዳሆን ጨምሮ በታችኛው የውሀ ክፍል የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችም በሙሉ በሙሉ ይወድማሉ” ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ረዳት ፕሮፌሰር መገርሳ የአዋሽን ውሀ ለመጠጥነት በሚጠቀሙት የአፋር ተወላጆች ላይ የከፋ አደጋ እንደሚከሰትም ገልጸዋል።
ምንም እንኳ የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሙያዎች በጋራ የበሰቃን ሀይቅ እያጠኑ ቢሆንም ፣ አቶ ተስፋየ እንደሚሉት ለጊዜው መንግስት ስለሚወስደው እርምጃ አቅጣጫው ጠፍቶበታል።
በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ መረጃዎችን በማሰባሰብ ችግሩን ለማሳወቅ ጥረት ሲያደረግ የነበረው የፎቶ ጋዜጠኛው ቢኒያም መንገሻ ፣ ሀይቁ የፈጠረውን አደጋ ለመንግስት ለማቅረብ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደርግም በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ችግሩን እንዳባባሰው ተናግሯል
3 ኪሎ ሜትር ስፋት ብቻ የነበረው የበሰቃ ሀይቅ በአለፉት አርባ አመታት ውስጥ ወደ 45 ኪሎሜትር ከፍ ማለቱን በዘገባው ተመልክቷል። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ መለስ ዜናዊ አፍረካ የአካባቢ ጠበቃ እየተባሉ ሲወደሱ እንደነበር ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment