Thursday, April 18, 2013

ፈሪ ህዝብ አድርባይ እንጂ የልማት ሰራዊት መሆን አይችልም


(ሊሊ ክፍሌ - ዲሲ)
fear


የኢትዮጵያ እዝብ በተፈጥሮው ፈሪ ህዝብ ነው ብዬ አላምንም፡ ነገር ግን ለብዙ ዘመናት የተለዋወጡ ገዚዎች በፈጠሩበት ተጵህኖ በፍራቻ ድባብ ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል ብዬ አስባለው እስከ አሁን ድረስ። የአገሩን ዳር ድንበር ና ነጳነት በአጋጣሚ ሳይሆን በደሙ ጠብቆ የኖረን ህዝብ ፈሪ ነው ብሎ ማሰብ እብደት ነው። ነገር ግን በውስጥ ገዚዎች መካከል የተደረጉ ግጭቶች ያደረሱበት ጉዳት ፡ (የቅርቦቹን እንኳን ብንወስድ የቀይ ሽብርና 1997ቱ ምርጫ ግጭቶች) ፣ ኢፍታዊነት ፣ የፖለቲካ ፣ ፍትህ ና ሰብሃዊ መብት ግንዛቤ ችግር በፍራቻ ድባብ ና በግል እስካልነኩኝ አያገባኝም በሚል ጠባብ የአህምሮ እስር ቤት ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ ሲጣስ እሺ፣ ሲፈናቀል እሺ ፣ ንብረቱ ሲቀማ እሺ ፣ ፍትህ ሲዛባ እሺ ፡ሲታሰር እሺ ፣ ሰለ ፍትህ ፣ ፖለቲካ ና ሰብሃዊ መብት  ስትጠይቀው አርባ ክንድ የሚርቅ፣ ጭራሽ ምንም ወንጀል ሳይፈጵም ቢያስሩኝስ ብሎ የሚፈራ እዝብ እየሆነ ነው።
በአገራችን በጣም ሰለጠኑ በሚባሉ አገሮች ደረጃ የተቀመጠ ህገ መንግስት ና ህጎች አርቅቃለች፡ ነገር ግን አስፈጳሚዎቹ 180 ዲግሪ አዙረው ያነበቡት እስኪመስል  ድረስ ነው የሚተገብሩት ብዙ ግዜ ለህግና ለመመሪያ ደንታ የላቸውም ፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ። ምን ታመጣለህ እንደሚወደው የመንደር ወሮበላ ነው የሚተገብሩት።
እኔን የሚያሳስበኝ የአስፈጳሚዎቹ ድንቁርና ሳይሆን  ተሳስታችዋል  ተመለሱ ብሎ የሚጠይቅ ኢትዮጵያዊ ቁጥር በእጅጉ እየተዳከመ መምጣቱ ነው፣ እሺ፣ እሺ፣ እሺ  ብሎ ተቀብሎ ከማማረር ውጭ።  እንዲያውም አብዛኛው ኢትጵያዊ ህጉ ምን ይላይ በህጉ መሰረት የኔ መብትና ግዴታ ምንድነው ብሎም ለማወቅም አይፈልግም ። አያገባኝም  ኤሌትሪክና ፖለቲካ ከሩቁ እያለ እራሱን ያሸሻል ። እንዲህ አይነት ህዝብ ደግሞ አድርባይ እንጂ የልማት ሰራዊት መሆን አይችልም። የልማትና አስተዳደር  ፖሊሲዎች በሙሉ የፖለቲካ ጨዋታ ውጨት መሆናቸውን ይረሳል ፡ የመሬት ፖሊሲ፣ የሊዝ አዋጅ ፣ የግብርና ፖሊሲ ፣  የትምህርት ፖሊሲ ፣  የንግድ ህግ፣ የፕሬስ ህግ  ወዘተ ፖለቲካ መሆኑን መቀበል ይሳነዋል።
ነጋዴው፣ መንግስት ሰራተኛው፡ ምሁሩ ወዘተ  ያለቅሳል ያማርራል፡ 99.6% ድምጵ ሰጥተክ የመረጥከው እኮ አንተ ነህ ፣ አገራችን በልማት ላይ ነች ስትለው ፡ እኔ አልመረጥኩም ፣የለውጡ ዳቦ እኔን ዘሎኛል ይላል፤ ለውጡ ሚሊዮን ቢሊዮን የሚል የቁጥርና የህንጳ ጋጋታ እንጅ እኔን አልጠቀመኝም ይላል ።ፍራቻው ተስፋ ቢስ አድርጎታል። ፍራቻው አገር ለቆ በምን በኩል እንደሚያመልጥ የሚያስብ ዜጋ አድርጎታል። ኢትዮጵያዊ ዛሬ ተስፋውም ህልሙም ከአገር መሰደድን አድርጓል። እንዲህ አይነት ኢትዮጵያዊ ደግሞ የልማት ሰራዊት መሆን አይችልም።
ከፍራቻ እንዴት እንውጣ ?
ዶ/ር በየነ ጵጥሮስ በአንድ ወቅት ለተጠየቁት “ሕዝቡን ማታገል አልቻላቹም” ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ “ሕዝቡን አላታገላችሁም የሚለው ትክክል አይደለም ፡ ስብሰባ ስንጠራው እየተሸማቀቀ ፣ ሰው አየኝ አላየኝ እያለ ከሚመጣ ህዝብ ጋር ትግሉ ቀላይ አይደለም…” ያሉት በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያን ህዝብ በምን አይነት ሁኔታ እንዳለ ማሳያ ነው።
እንግዲህ አገራችንን ለማልማትና የዲሞክራሲ ስርሀት ለመገንባት የመጀመሪያው ትግል መሆን ያለበት የኢትዮጵያን ህዝብ እንዴት ከፍራቻ ማላቀቅ ይቻላል መሆን ይኖርበታል።
ከፍራቻ ለመላቀቅ ፡ ጫካ መግባት መፍትሄ ነው ብዬ አላምንም፡ በዛ አካሄድ ለውጥ ይመጣል ብዬም አልጠብቅም ፡ ከልምድና ከታሪክ እንደታየው የቀድሞውን ፈሪ ፡ አስፈራሪ አድርጎ ከመተካት ውጭ የፍርሀት ድባብን ከዜጎች ላይ ያጠፋል ብዬ አላምንም።
ጫካው መፍትሄ ካልሆነ ከፍራቻ እንዴት እንውጣ ?
በክፍል ሁለት እንመለሳለን

No comments:

Post a Comment