Monday, July 1, 2013

የግብፅ ጦር ፕሬዚዳንት ሙርሲ ለተቃዋሚዎች ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ 48 ሰዓታት ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2005 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብፅ  ጦር በአገሪቱ  ለተከሰተው ቀውስና  ለተቃዋሚዎች ጥያቄ ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ምላሽ እንዲሰጡ 48 ሰዓት  ሰጠ ።
ጦሩ የፕሬዚዳንቱ  መንግስት አሁን ለተፈጠረው  ቀውስ  ፈጥኖ ምላሽ  መስጠት ካልቻለ ለሰላም ሲል የራሱን  ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ  እንደሚተገብር አስታውቋል ።
ይህ  የጦሩ መግለጫ  የወጣው  ተቃዋሚዎቹ  ከሰዓት በኋላ  በካይሮ  የሚገኘውን የፕሬዚዳንት ሙርሲ ፓርቲ የሆነውን ሙስሊም ወንድማማቾች ዋና መስሪያ ቤት  ከወረሩ በኋላ ነው ።
የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት በእሳት የተቀጣጠለ ሲሆን ፥  በውስጡ  የሚገኙ  ንብረቶችም ተዘርፈዋል ።
በዋና ፅህፈት ቤቱ  አከባቢ  በነበረው  ግጭትም  ስምንት  ያህል  ሰዎች ተገድለዋል ።

ሚኒስትሮች ስልጣናቸውን  እየለቀቁ ነው
በፕሬዚዳንቱ ላይ  የተቀሰቀሰው  ተቃውሞ  በመላው  የግብፅ  ከተሞች የተቀጣጠለ ሲሆን ፥ እስካሁንም  አምስት ሚኒስትሮች ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል ።
የቱሪዝም ፣የውሃ ፣ የአከባቢ ፣  የመገናኛና የመረጃ ቴክኖሎጂ እንዲሁም  የህግና  ፓርላማ  ጉዳዮች ሚኒስትሮች የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጠቅላይ  ሚኒስትር ሂሻም ቃንዲል  አቅርበዋል ።
የግብፅ  የአገር  ውስጥ  ሚኒስቴር  እንዳስታወቀው በትናንቱ  የተቃውሞ ሰልፍ ላይ  ብቻ  ከ14 እስከ 17 ሚሊዮን  የሚጠጉ  ሰዎች  ለተቃውሞ  አደባባይ ወጥተዋል ።
በአንፃሩም  ትናንት  ሙርሲን ደግፈው አደባባይ  የወጡ  ሰዎች ነበሩ ።
በሁለቱ  ጎራ  በተቀሰቀሰም  ግጭት እስካሁን 14  ሰው   መገደሉንና  በ100  የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው  ተነግሯል ።
ተቃዋሚዎቹ  ፕሬዚዳንት  ሙርሲ እስከ  ነገ ስልጣን  እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ  ሰጥተዋል ።
ይህንን  ማድረግ ከተሳናቸው  ግን  በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን  እንደሚቀጥሉ  ነው የገለፁት ።

ምንጭ: ቢቢሲ

No comments:

Post a Comment