ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት የህዝባዊ ንቅናቄ የትግል ስልቱ የመጀመሪያውን የአደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ሰኔ 30/10/2005 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚያደርግ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ሁልጊዜም ህግ ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲያችን የአገሪቱ ህገ መንግስት በሚደነግገው መሰረት የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለሰሜን ጎንደር ዞን ማወቅ ለሚገባቸው የመንግስት አካልና ለከተማ መስተዳድሩ አሳውቆ ወደ ቅስቀሳ ከገባ ጥቂት ቀናት አልፈዋል፡፡
ይህ ተግባር ህጉን ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ፓርቲያችን ላይ አሁንም በገዥው ፓርቲ ህግ ጥሶ ሰላማዊ ሰልፉን የማደናቀፍ ተግባር እየተፈፀመ ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡ ይህና ሌሎች የገዢው ፓርቲ እኩይ ድርጊቶች አንድነትን በፍፁም ወደኋላ ሊመልሱት እንደማይችሉ ማሳወቅ እንወዳለን ፡፡ ይህን በድፍረት እንድንናገር ያስቻለን ከዓላማ ቁርጠኝነታችን በተጨማሪ ህግ አክባሪነታችን ነው፡፡ ስለዚህ በቅስቀሳ ቡድኑ ላይ ከሚካሄደው ዛቻና ማስፈራሪያ ውጭ በተለያዩ ወረዳዎች የፓርቲያቸውን ተልዕኮ ለማሳካት በፍፁም ሰላማዊነት እየሰሩ ያሉ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትግላችንን ሊቀለብሰው እንደማይችል ተገንዝቦ መንግስት ከህገ ወጥ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
እነዚህ አባሎቻችንም በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቅን ምንም አይነት ህገ ወጥ እርምጃ መብታችንን ከመጠየቅ እንደማይገድበን በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና የፀጥታ ሀይሎች በአንድነት አባላት ላይ እየወሰዱ የሚገኙትን እስርና ማስፈራሪያ ፊትለ ፊት በመቃወም ቁርጠኝነቱንና አጋርነቱን በማሳየቱ አንድነት ፓርቲ ለጎንደር ህዝብ የአክብሮት ምስጋናውን ያስተላልፋል፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment