Monday, July 22, 2013

ኢህአዴግ አንድነት ፓርቲ የጠራው ሰልፍ እንዳይሳካ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው

ሐምሌ ፲፭(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት በማለት የጠራው ህዝባዊ ንቅናቄ ገዢውን ፓርቲ በማስደንገጡን አዲስ ከጀመራቸው ግምገማዎችና የህብዕ እንቅስቃሴዎች ለመረዳት ተችሎአል።
በደሴ እና በጎንደር የተካሄደውን ስላማዊ ሰልፍ ተከትሎ  የፖሊስ እና የቀበሌ የፖለቲካ አመራሮች በጠንካራ ግምገማ ተይዘው መሰንበታቸውን ከኢህአዴግ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ስማችን እና ድምጻችን አይተላለፍ ያሉት ምንጮች እንደገለጹት በ1ለ5  አደራጃጀት መሰረት ህዝቡ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ መመሪያ ለሚመለከታቸው ወገኖች ተላልፏል።  የፖሊስ አባላት ሰልፎችን በመበተን የድርሻቸውን እንዲወጡ የተሰጣቸው መመሪያ በመካከላቸው ክፍፍል እንዲፈጠር እንዳደረገ  ምንጮች ገልጸዋል፡፡  ፖሊሶቹ በስራ አጥነት እና በኑሮ ውድነት የተማረረውን ህዝብ ለማቆም አንችልም በማለት ሲናገሩ ተስምተዋል።
ነሀሴ 26 በደብረማርቆስ ከተማ የሚካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ ለመገደብ እና በ1 ለ 5 አደረጃጀት የተቀየሰውን የማገቻ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን እና ምክትላቸው አቶ ገዱ አንደርጋቸው የስልጠናና የማሳሰቢያ ስራዎችን ለመስራት ወደ ደብረማርቆስ  እየተመላለሱ ነው።
ሐምሌ 28 በባህርዳር የተጠራውን ህዝባዊ ሰልፍ ለማስቆም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሁሉንም መንገዶች እንዲከተሉ፣ የብአዴን ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊዎች እና ሁሉም የመንግስት አመራሮች በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ  ተወስኖ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌና የአዳማ ተመሳሳይ ስራዎችን እንዲያከናውኑ በሚኒስትር ደረጃ የተወከሉ አመራሮች ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡
ከኢህአዴግ ዜና ሳንወጣ  ለመለስ ፋውንዴሺን እርዳታ ከህዝቡ የገንዘብ ልመና ጥያቄ መቅረቡን ለማወቅ ተችሎአል።
የመለስ ፋውንዴሺን አመራሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነሐሴ 14 በደመቀ ሁኔታ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሙት አመት በሻማ ማብራት ስነ ስርዓት እንዲከበር መታቀዱን ተናግራዋል፡፡
በእለቱም ለፋውንዴሺኑ የተቋም ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ይጣላል ተብሎአል፡፡
በቀጣይም ለፋውንዴሺኑ እርዳታ  የሚሆን ገንዘብ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ለመሰብሰብ ታስቦ የባንክ አካውንት ለባለሃብቶች ፤
ለድሃው ደግም በሞባይል ቁጥር በቴሌ በሚቆረጥ  ከ2 ብር ጀምሮ 100 ብር የሚደርስ የገንዘብ መክፈያ መዘጋጀቱን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment