Tuesday, July 9, 2013

አሜሪካና አውሮፓን ያፋጠጠው የስለላ ሚስጥር


አሜሪካና አውሮፓን ያፋጠጠው የስለላ ሚስጥር
የአሜሪካን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል አሜሪካውያኑ ባለሥልጣናት ጦር ከተው በሌሎች አገሮች የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት የተለመደ ነው፡፡
አልተሳካም እንጂ በሶማሊያ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት ታሪክ የሚያወሳው ነው፡፡ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ዛሬም ድረስ ያሉዋቸው ወታደራዊ የጦር ሠፈሮች አሜሪካውያኑን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እያነጋገረ ነው፡፡
አሜሪካ ግን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቷ ለደኅንነቷ ስትል መሆኑን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ስታቀርብ ኖራለች፡፡ ከሰሞኑ የተሰማውና ለአሜሪካ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ጠንካራውን ሥፍራ የሚይዘውን የአውሮፓ ኅብረትን ጭምር ያስቆጣው ደግሞ ጦር አዝምቶ ከመውጋትም ባለፈ በስውር የሚደረገው ስለላ ነው፡፡ አሜሪካ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ ስትል ከአገሯም አልፋ ሌሎች አገሮችን አትሰልልም ማለት ሞኝነት ቢሆንም፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ግን ይህን አልጠበቁትም፡፡ አሜሪካ ሁሌም ለአውሮፓ ወዳጅና አማካሪ ናትና፡፡
አሜሪካ የምታካሂደው ሙሉ የኢንተርኔትና የስልክ ጥሪዎች ጠለፋና ስለላ ያልተዋጠለት የቀድሞው የአሜሪካ ስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሠራተኛ ሚስጥሩን በማውጣቱ፣ አባል አገሮቹ ከአሜሪካ ጋር ለሚኖራቸው የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት እንኳ ጉዳዩ እስካልተጣራ ድረስ አንፈርምም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲሻክር ያደረገው ደግሞ የ30 ዓመቱ አሜሪካዊ ኤድዋርድ ስኖውደን የዘከዘከው ሚስጥር ነው፡፡
በአሜሪካ የስለላ ድርጅት የሚደረገውን የስልክና የኢንተርኔት ጠለፋ ሚስጥር አባክኖ ወደ ሆንግ ኮንክ በግንቦት ወር የተሰደደው ስኖውደን የእንግሊዙ ጋርድያን ጋዜጣ ማንነቱን እስካጋለጠበት ጊዜ ድረስ ያለበት አልታወቀም ነበር፡፡
መረጃው ይፋ ከወጣ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት በቀድሞው የደኅንነት ሠራተኛ ላይ ክስ መክፈቱንና የሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናትም አሳልፈው እንዲሰጡት ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ስኖውደን በሰኔ ወር ሞስኮ ገብቷል፡፡
በሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያ እንደተጠለለ የሚነገርለት ስኖውደን፣ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ተቋማትና ዜጎች ሳይቀሩ የሚፈጸምባቸውን የኢንተርኔትና የስልክ ስለላ ሚስጥር ለምን ማባከን እንደፈለገ ሲጠየቅ፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነቱን የስለላ ሥራ በሚሠራ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር አልፈልግም፡፡ የምናገረውና የምሠራው ሁሉ በሚቀረፅበትና በሚሰማበት ዓለም መኖር አልፈልግም፤›› ነበር ያለው፡፡
ስኖውደን የመብት ጥያቄ ቢያነሳም አሜሪካ የመንግሥት ንብረትን በመስረቅና ያልተፈቀደ የብሔራዊ መከላከያ መረጃን ይፋ በማውጣት አሜሪካ ክስ መሥርታበታለች፡፡ ሞስኮ ሆኖ ለ21 አገሮች ጥገኝነት የጠየቀው ስኖውደን ተላልፎ እንዲሰጣትም ለሩሲያ ጥያቄ አቅርባለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካና ታንዛኒያን የጎበኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተፈላጊ ሰዎችን አሳልፈው ለመስጠት ከሩሲያ ጋር ውል ባይኖራቸውም፣ ሩሲያ ስኖውደንን አሳልፋ እንደምትሰጣቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ስኖውደን እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ባሉበት ወቅት ግን ከአውሮፓ ኅብረት ሌላ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ስኖውደን ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠት ትልቁ አጀንዳው አይደለም፡፡ አጀንዳው ያነጣጠረው አሜሪካ ወዳጅ መስላ በአባል አገሮች ኤምባሲዎች ላይ ሙሉ የኢንተርኔትና የስልክ ጠለፋ ማካሄዷና የየአገሮቹን ሉዓላዊነት መድፈሯ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአውሮፓ ኅብረትና በአሜካ መካከል ያሉ የንግድ ግንኙነቶች ጐርበጥባጣ መንገድ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡
አንዳንድ የአውሮፓ ፖለቲከኞችም አሜሪካ የተጋለጠባት የስለላ ወንጀል በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል ያሉ አጠቃላይ ስምምነቶችን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ናቸው ብለዋል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንደ፣ ‹‹አሜሪካ የአውሮፓ ኅብረትን ላለመሰለል ዋስትና እስካልሰጠች ድረስ ምንም ዓይነት ስምምነቶች አይኖሩም፤›› ሲሉ፣ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሕግ ባለሥልጣን ደግሞ፣ ‹‹ከእኛ ጋር የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች የስለላ ሥራ እንደሚሠሩ ትንሽ ፍንጭ ከተገኘ በትራንስ አትላንቲክ ገበያ ላይ ስምምነት አናደርግም፤›› ብለዋል፡፡
የፈረንሳይ የግራ ክንፍ ፓርላማ አባል የሆኑት ዲን ሚሊንኮን ፈረንሳይ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ሁሉንም የንግድ ስምምነቶች እንድታግድ ጥሪ በማቅረብ፣ የአሜሪካ ዋና ሚስጥራዊ የስለላ ሰነዶችን ይፋ ላደረገው አማሪካዊ ኤድዋርድ ስኖውደን የአውሮፓ ኅብረት የፖለቲካ ጥገኝነት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡
ለሁለት አገሮች ግንኙነት ፖለቲካ ትልቁን ሚና ቢጫወትም አንዳንድ ፈረንሳውያን ከአሜሪካውያን ጋር የንግድ ውል ለመፈጸም እየሰጉ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በአብዛኞቹ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችም፣ ‹‹እንዴት ጓደኛን ትሰልላለህ?›› በሚል ብስጭታቸውን ገልጸዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ፣ ‹‹የስለላ ድርጅቶች መረጃ ለማግኘት ሲሉ ጠላቶቻቸውን እንደሚሰልሉ ሁሉ የወዳጆቻቸውንም መረጃ ይሰበስባሉ፤›› በማለት በአሜሪካ የኢንተርኔትና የስልክ ጠለፋ አልተደነቁም፡፡
አሜሪካ በወዳጆቿ ጭምር ሳይቀር ስታደርግ ስለነበረው ስለላ መረጃ ከወጣ ወዲህ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል አለመተማመን ሰፍኗል፡፡ የአባል አገሮቹ አንዳንድ መሪዎችና ፖለቲከኞችም ለስኖውደን የፖለቲካ ጥገኝነት መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
ዊኪሊክስ እንደዘገበው ስኖውደን ቻይናን፣ ፈረንሳይን፣ አየርላንድንና ቬኒዙዌላን ጨምሮ ለ21 አገሮች የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቀ ሲሆን፣ ሰባት የአውሮፓ አገሮች ጥያቄውን ውድቅ አድርገውበታል፡፡ ለዚህም በአገሮቹ ላይ የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር እየፈጠረ ያለው ጫና ምክንያት መሆኑን ስኖውደን ተናግሯል፡፡ ቦሊቪያና ቬኑዜላ ለስለላ ሠራተኛው ጥገኝነት ለመስጠት ፍላጎት ማሳየታቸው ተሰምቷል፡፡ አሜሪካ ከወዳጆቿ ጋር የገባችበት አሳዛኝ አጋጣሚ ግን አንገቷን ሰበር እንዳደረገባት እየተነገረ ነው፡፡
source: ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment