Tuesday, July 2, 2013
የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አዋጅ ጸደቀ
ኢሳት ዜና :-በሚኒስትር ማእረግ ደረጃ እንዲቋቋም የታሰበው የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት መ/ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ከአንድ ሳምንት ዕይታ በኋላ ዛሬ ለፓርላማው ቀርቦ እምብዛም ውይይት ሳይደረግበት መጽደቁ ታውቋል፡፡
የኣመቱ ሥራውን ሰኔ 30 የሚያጠናቅቀውና ለዕረፍት የሚዘጋው ኢህአዴግ መራሹ ፓርላማ በተጣደፈ አሰራር ያጸደቀው በዚሁ አዋጅ መሰረት የሚቋቋመው መ/ቤት መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የመተንተንና የማቅረብ እና የደህንነት አገልግሎት የመስጠት እንዲሁም በአገር ውስጥ የጸረ ሸብርተኝነት እና የበረራ ደህንነትን የማስጠበቅ ሥራዎችን በኃላፊነት
ይሰራል።
መ/ቤቱም ካለበት ህገመንግስታዊና አገራዊ ሃላፊነት እንዲሁም ካለው ስልጣንና ተግባር በመነሳት በሚኒስቴር መ/ቤት ፕሮቶኮል ደረጃ እንደሚሰራ በአገሪቱም የተለያዩ ቅርንጫፍ መ/ቤቶችን ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስ አዋጁ ያስረዳል፡፡
ማንኛውም ሰው በመ/ቤቱ መረጃ ሲጠየቅ የመተባበር፣ የሠጠውንም መረጃ በሚስጢር የመያዝ ግዴታ የተጣለበት ሲሆን ይህንን የተላለፈም በወንጀል እንደሚጠየቅ ደንግጓል፡፡
አገሪቱ በተለይም በኤደን ባህረሰላጤ አካባቢ የሚስተዋለውን ተለዋዋጭ የስጋት ምንጭ ለመከላከልና ለመቋቋም የሚቻለው ብቃት ያለው የመረጃና ደህንነት ተቋም ሲገነባ ነው በማለት አዋጁ የወጣበትን ምክንያት አስቀምጧል።
የአዋጁን መጽደቅ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ተቃውመውታል። አዋጁ አዎንታዊ ጎኖች እንዳሉት የገለጹት አቶ ግርማ ለትርጉም አሻሚ የሆኑ አሻሚ ድንጋጌዎች መካተታቸው ለተቃውሞአቸው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ እንዲሁም ኢህአዴግ የተለያዩ ደህንነት መስመሮች እንዳሉዋቸው አስታወሱት አቶ ግርማ ምናልባትም አዲሱ ጠ/ሚ የደህንነት መስመሩ አንድ ወጥ በሆነ እና እርሳቸው በሚያዉቁት መንግድ ብቻ እንዲህ በመፈለጋቸው የተደነገገ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ተናግረዋል
በአዲሱ አዋጅ አንድ የደህንነት ሰራተኛ አስቸጋሪ ሁኔታ ካልገጠመው በስተቀር በዜጎች ላይ አንድ ጥፋት ቢፈጽም ሊጠየቅ እንደሚችል በአዋጁ መደንገጉን የገለጹት አቶ ግርማ ፣ ይሁን እንጅ “አስቸጋሪ ሁኔታ” የሚለው ሀረግ ለትረጉም አሻሚ ነው በማለት ገልጸዋል ። መረጃን በመቀበልና ይፋ በማድረግ በኩልም አዋጁ ችግሮች እንዳሉበት አቶ ግርማ ተናግረዋል
“ብሄራዊ የደህንነት መስሪያ ቤት ተቃዋሚዎችን እንዳይሰልል፣ ወይም በተቃዋሚዎች ላይ እንግልት እንዳይፈጽም የሚያስገድድ ድንጋጌ አለ ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አዋጁ” ምንም ” እንደማይል ገልጸዋል።
መንግስት በእስራኤል አገር የሰለጠኑ የደህንነቶች ሀይሎችን በተለያዩ የሀይማኖት እና የመንግስት ተቋማት ማሰማራቱን፣ ሌሎች አዳዲስ የደህንነት ሰራተኞችም በስልጠና ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment