- አቡነ ሉቃስ ፓትርያሪኩን ከአቡነ ጳውሎስ “ከዚህ የበለጠ ምን አደረጉ?” በማለት ተናገሯቸው
- የኮሌጁን መዘጋት የተቃወሙ አባቶች እንደዚህ ቀደሙ ትደበደባላችሁ የሚል ማስፈራሪያ ደረሳቸው
- አሁንም ቤተክህነቱ በድህንነቶች እንደተከበበ ነው
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች በተቃውሞ ላይ
(ዘ-ሐበሻ) ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ለቀው እንዲወጡና ኮሌጁ ትምህርት ተቋርጦ እንዲዘጋ ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ ማዘዛቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች “አቡነ ማቲያስ ኮሌጁን የመዝጋት ሥልጣን የላቸውም፤ ውሳኔያቸውም ሕገ ወጥ ነው” በሚል ተቃወሙ።በኮሌጁ ላይ የሚሰጡ ማናቸውም ውሳኔዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መሆኑን በመጥቀስ የሲኖዶሱ ዋናፀሐፊ አቡነ ሉቃስ በይፋ መቃወማቸውን የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገልጸዋል።
አቡነ ሉቃስ ፓትርያርኩን በኮሌጁ መዘጋት ዙሪያ በማነጋገር “አቡነ ጳውሎስ ከዚህ የበለጠ ምን አደረጉ?” በሚል ከአቡነ ጳውሎስ በበለጠ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እንደጣሱ ወቅሰዋቸዋል ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች መንፈሳዊ ኮሌጁን በራሳቸው ፈቃድ ማዘጋታቸውና ተማሪዎቹንም እንዲወጡ ማደረጋቸው በሲኖዶሱ የሃሳብ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በአቡነ ገሪማ የተፈረመውና በአቡነ ማቲያስ ትዕዛዝ የተጻፈው ይኸው ተማሪዎቹን ከኮሌጁ እንዲወጡ የታዘዘበት ደብዳቤ የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት እና የቅድስት ሥላሴ ሥራ አመራር ቦርድ ደብዳቤው በግልባጭ እንዲደርሳቸው ሲደረግ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽህፈት ቤት ግን የደብዳቤው ግልባጭ ውስጥ አለመካተቱ የተፈጠረውን መከፋፈልና በተለይ በአንድ ብሄር ሥር የበላይነት የያዙት ወገኖች በማስፈራራት ቤተክርስቲያኗን የራሳቸው ለማድረግ የሚያደርጉትን ሩጫ የሚያሳይ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በሚገኘው ሲኖዶስ ስር ያሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ጳጳስ ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት “አሁን ጉዳዩን እያቀጣጠሉት ያሉት አቡነ ጢሞጢዎስ ናቸው። አቡነ ጢሞጢዎስ ማለት ፓትርያርኩ ውጭ ሃገር እያሉ በሃገር ቤቱ ሲኖዶስ ይከፈላቸው የነበረውን ደመወዝ ፈርመው በመውሰድ የሚጠቀሙበት ሰው ናቸው። እኚህ ሰው ከፓትርያርኩ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ስላላቸው እንዲመረጡም በአስመራጭነት ውስጥ ገብተው ትልቅ ሥራ ሰርተዋል። በዚህ በገንዘብ ላይ በተመሠረተ ስር የሰደደ ወዳጅነት የተነሳ የአቡነ ማቲያስን ት ዕዛዝ በማስፈጸም ሌሎች አባቶችን በማስፈራራትና በአባቶች መካከል ቡድን በመፍጠር በውስጣችን ውስጥ መከፋፈል እንዲኖር አድርገዋል” ሲሉ ይወቅሳሉ። ዘ-ሐበሻ አቡነ ጢሞጢዎስን አግኝታ ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት ባይሳካም ከቅርብ ምንጮች እንደሰማነው የአቡነ ጢሞጢዎስ ግሩም በዘር ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ የሌላ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባቶችን በመግፋት የስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መዘጋትንና የተማሪዎቹን ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀልን ከሕግ ውጭ አስፈጽመዋል በሚል እየተወቀሱ ነው።
በተለይም በሲኖዶሱ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው በሚባለው የዘር ሐረግ ውስጥ የሌሉት የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ ተብለው የተፈረጁት አባቶች ይህን ውሳኔ በመቃወማቸው ወይም ባለመደገፋቸው ሳቢያ እንደከዚህ በፊቱ ትደበደባላችሁ የሚል ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው እነዚሁ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አጋልጠዋል። ከዚህ በፊት አቡነ ጳውሎስ በሕይወት በነበሩበት ወቅት አባቶች ቤታቸው ተሰብሮ እንደተደበደቡ በተለያዩ ሚድያዎች ተዘግቦ እንደነበር የሚያስታውሱት እነዚሁ ምንጮች ይህን በማስታወስ አባቶች እንዲፈሩና አርፈው እንዲቀመጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአቡነ ጳውሎስ ሕልፈት በኋላ አዲሱ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ተስፋ የነበራቸው ወገኖች ተስፋ መቁረጥ ጀምረዋል። አሁንም ቤተክህነቱ በደህነንቶች የተከበበ ከመሆኑም በላይ ቤተክርስቲያኒቷን ከበላይ ሆነው የሚመሯት የሕወሓት ካድሬዎች እንጂ የ እምነት ሰዎች አይደሉም ሲሉ ትዝብታቸውን የሚገልጹት ምንጮቻችን አባቶች አሁንም በደህንነቶች በብሄራቸውና ባለመደገፋቸው ብቻ እንደሚገፉና እንደሚዋከቡ ተናግረዋል።
ዘ-ሐበሻ በቅድሥት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዙሪያና በቅዱስ ሲኖዶሱ መከፋፈል ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዳገኘች ትመለሳለች።
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=5345
No comments:
Post a Comment