- “የጦርነት መንገድ ለኢትዮጵያም ለግብፅም አይጠቅምም” – አቶ ሙሼ ሰሙ
- “ከገዢው ፓርቲ ያነሰ የአገር ፍቅር ያለን አይመስለኝም” – ዶ/ር መረራ ጉዲና
ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ መቀየሯንና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በግብጽና በሱዳን ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽእኖ እንዲያጠና የተቋቋመው የኤክስፐርቶች ቡድን ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ፤ የግብጽ ተቃዋሚዎች የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጐል ያቀረቡትን ሃሳብ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ተቃወሙት፡፡ የግብፁ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ከአገሪቱ ባለስልጣናት፣ ከተቃዋሚዎችና ከሃይማኖት ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፤ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማወጅና፣ የአገሪቱን ተቃዋሚዎች በመደገፍ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታስተጓጉል ማስገደድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተንፀባረቀውን ሃሳብ በተመለከተ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “በርግጥም ግብፃውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቀዳዳ አይጠቀሙም ብሎ መከራከር ያስቸግራል፡፡ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ለውጭ ሃይል መጠቀሚያ ለመሆን ይዘጋጃሉ የሚል ግምት የለኝም” ብለዋል፡፡ “በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቢያንስ ቢያንስ ከኢህአዴግ ያነሰ የአገር ስሜት አላቸው ብዬ አልገምትም” ያሉት ዶ/ር መረራ “ይሄም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ፈርጀ ብዙ ችግሮች ካልተፈቱ የውጭ ሃይሎች ባገኙት ክፍተት ተቅመው የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር አይሞክሩም ማለት አይቻልም” ብለዋል፡፡ “ከሰባት ዓመት በፊት በፓርላማ የሶማሌን ጉዳይ በሚመለከት ስንወያይ ዳር ድንበራችንን አገራችን ውስጥ ሆነን መከላከል ይሻላል፣ የሰው አገር መግባት አስቸጋሪ ነው፣ እና አሜሪካ እንኳን ያን ያህል ሃብትና ቴክኖሎጂ ይዘው በድል መውጣት አልቻሉም” ብለን ለቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሃሳብ አቅርበን ነበር፡፡ እሳቸው ግን “በእኔ ይሁንባችሁ ጥቂት ሳምንት ብቻ ነው በዚያ የምንቆየው” ሲሉን ነበር፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም እዚያው ነች፤ ያ ቀዳዳ አለ፤ የኦጋዴን፣ የኤርትራ፣ የሱዳን ቀዳዳዎች አሉ፡፡ የውጪ ሃይሎች እነዚህን ክፍተቶች ለመጠቀም አይሞከሩም ማለት አይቻልም፡፡ የአባይ ወንዝን በሚመለከት ከገዥው ፓርቲ ያነሰ የአገር ፍቅር አለን የሚል ግምት የለኝም ብለዋል ዶ/ር መረራ፡፡ አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ “የግብፅ መንግስት በአገር ውስጥ ያሉና በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን የፈለጋቸው፣ የራሱን አጀንዳ ለመሸጥ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር የፍትህ እጦት አሳስቦት አይደለም፣ የአባይ ግድብ እንዳይገደብ ተቃዋሚዎችን መሳሪያ አደርጋለሁ ብሎ መነሳቱ አግባብ አይመስለኝም፣ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አጀንዳ ስላልሆነ ትርጉም የለውም” ብለዋል፡፡
“መሐመድ ሙርሲ፤ የኢትዮጵያ መንግስትንና ህዝቡን አከብራለሁ የሚል አስተያየት ሲሰጡ በቅርብ ሰዎቻቸው ተሰምተዋል፡፡ በደጋፊዎቻቸውም ይሁን በህዝቡ ወይም በማንም ተባባሪ ሃይል ቢታገዝም፣ የጦርነት መንገዱ ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡ የጋራ ጥቅማችንን ለማስከበር በሩ ክፍት እስከ ሆነ ድረስ ተቀራርቦ መነጋገር እንጂ፣ በጦርነት መልኩ ማሰብ ዘመኑ የሚፈቅደው አይደለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዲያደርጉ በስምምነት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ያወጡትን ዝርዝር ሰነድ መመልከትና በምስራቅ አፍሪካ አገሮች የሚገኙ ህዝቦችን መጥቀም የሚችልበትን አቅጣጫ መከተል ነው የሚበጀው፡፡ የጦርነት መንገድ ለኢትዮጵያም ለግብፅም አይጠቅምም” ብለዋል፡፡
addisadmas
No comments:
Post a Comment