Thursday, June 20, 2013

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ውይይት አደረገ

ሰኔ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ዶናልድ ያማማቶ፣ በአፍሪካ የዩሴ አይ ዲ ዳይሬክተር ኤሪል ጋስት፣ በአፍሪካ  ጉዳዮች ተመራማሪ  ዶ/ር ፒተር ፓሀም፣ የግንቦት7 ሊቀመንበር ዶ.ር ብርሀኑ ነጋ ፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር  አቶ ኦባንግ ሜቶና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአሜሪካ ተወካይ  ሚስተር አዶቲ አኪዌ እና ሌሎችም ታዋቂ ምሁራን ፖለቲከኞች የተሳተፉበት ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ አምባሳደር ያማማቶ እና ዶ/ር ጋስት ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድምትገኝ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱን የገለጹት አምባሳደር ያማማቶና ሚስተር ጋስ፣  በሌላ በኩል ግን መንግስት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በመፈጸሙ የአገሪቱን መጻኢ እድል አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል።
ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ እና ሚ/ር አክዌ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ ዶ/ር ብርሀኑ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በመለስ ጊዜ እንደነበረው ምናልባትም ከዚያ በበሳ ሁኔታ አስከፊ እየሆነ መሄዱን ገልጸዋል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፍተኛ ገንዘብ የዘረፉ እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ በመሆናቸው እንጠየቃለን በሚል ፍርሀት ስልጣን በቀላሉ ለመልቀቅ እንደማይፈልጉ ዶ/ር ብርሀኑ አክለዋል።
ዶ/ር ብርሀኑ መንግስትን በሀይል ለማውረድ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እየተጠናከሩ መሄዳቸውን፣ አገሪቱ ወደ አልተፈለገ ግጭት ከማምራቷ በፊት የአሜሪካ መንግስት አሁን የሚከተለውን ፖሊስ ቆም ብሎ እንዲፈትሽ አሳስበዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ነጻ ታወጣናለች ብለው እንደማይጠብቁ፣ የራሳቸውን መብት በራሳቸው ለማስከበር እንደሚችሉ ገልጸው፣ አሜሪካ ከአምባገነኑና ዘረኛው የህወሀት መንግስት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት እንደገና እንድትፈትሽ ጠይቀዋል።
የውይይቱ ሊቀመንበር የተከበሩ ሚስተር ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በዝርዝር ለተሰብሳቢው አቅርበዋል።

No comments:

Post a Comment