በ “ፍትህ” ጋዜጣ “የሁለተኛ ዜግነት ህይወት እስከመቼ”፣ “የፈራ ይመለስ” እና “መጅሊሱና ሲኖዲሱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቂያ” በሚሉ ርዕሶች በተለያዩ እትሞች ባሰፈረው ዘገባ ተከስሶ ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ምስክሮችን ለመስማት ለሃምሌ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ ከትላንትና በስቲያ በከፍተኛው ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት የጋዜጠኛው ምስክሮች ሊደመጡ ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የተከሳሽን የመከላከያ ቃል ሲያዳምጥና ስለምስክሮቹ ከጠበቆች መግለጫ ሲሰማ ሰዓት ያለቀ በመሆኑ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ “የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ” ፣ “ህዝብን በህገ መንግስቱ ላይ ማነሳሳትና” “የመንግስትን ስም ማጥፋት” በሚሉ ሶስት ጉዳዮች ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ የመከላከያ ምስክሮቹ ምስክርነታቸውን ለመስጠት ሀሙስ ዕለት በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ሆኖም በጊዜ እጥረት ሳይመሰክሩ ቀርተዋል፡፡
ከጋዜጠኛ ተመስገን ምስክሮች ውስጥ 1ኛ ምስክር ዶ/ር ያሬድ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ ሁለተኛ ምስክር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም እና 3ኛ ምስክር ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ሀ/ሚካኤል ከህግ፣ ከጋዜጠኝነትና ከመናገር ነፃነት እና መሰል ጉዳዮች አንፃር ምስክርነታቸውን በቀጣዩ ቀጠሮ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የፌደራል አቃቤ ህጎች በ1ኛ ምስክር ዶ/ር ያሬድና በሁለተኛ ምስክር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ላይ እንዳይመሰክሩ ተቃውሞ ያቀረቡ ሲሆን የተቃውሞው ምክንያት ዶ/ር ያሬድ የህግ ባለሙያ ቢሆኑም ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን እንደሌላቸው በመግለፅ ሲሆን 2ኛ ምስክር የሆኑት ፕ/ር መስፍን ደግሞ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሊቀመንበር የነበሩ ቢሆንም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በነበራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገለልተኛ ሆነው ይመሰክራሉ የሚል እምነት እንደሌለ በመግለፅ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱም በኋላ 1ኛ ምስክር ህገ-መንግስቱን የመተርጎም መብት ባይኖራቸውም ተከሳሽ የተከሰሱባቸው ፅሁፎች ከህግ አንፃር እና ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ አኳያ አግባብ ናቸው አይደሉም ያስከስሳሉ አያስከስሱም፣ በሚለው ላይ ብቻ እስከተናገሩ ድረስ ችግር እንደሌለው ጠቁሞ፤ ፕ/ር መስፍንም የኢሰመጉ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ ድርጅቱ ስላወጣቸው ሪፖርቶችና ተያያዥ ነገሮች ብቻ ከተናገሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ከምስክርነት ያግዳቸዋል የሚል ህግ እንደሌለ በመግለፅ የተከሳሹን ምስክሮች ቃል ለመስማት ፍ/ቤቱ ለሃምሌ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
addis admas
No comments:
Post a Comment