Tuesday, January 28, 2014

በቂ ጥበቃ ያልተደረገለት ሰርግ በሰው ደም ተጨማልቆ ተጠናቀቀ

በዳዊት ሰለሞን
በአዲስ አበባ ሐምሌ 19 መናፈሻ ትናንት 18/05/2006 እሁድ 10፡00 ገደማ በሰርግ ታዳሚዎችና በአካባቢው በሚገኙ ወጣቶች መካከል በተነሳ ግጥት ብዙዎች ክፉኛ ተጎድተው ወደ የካቲትና ምኒልክ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን በሰርጉ የታደሙ ሰዎች ለፍኖተ ነጻነት ተናግረዋል፡፡
ፈረንሳዊ ዜግነት ያለው ሙሽራ ኢትዩጵያዊቷን በሚያገባበት ሰርግ ላይ ለመታደም ከ300 የሚልቁ ሰዎች በአዳራሹ በመገኘት የሙሽሮቹን ደስታ ሲካፈሉ ቆይተዋል፡፡የጥሪ ካርድ በመመልከት ወደ አዳራሹ እድምተኛውን ሲያስገቡ የነበሩ አስተናባሪዎች ያለ ጥሪ ወረቀት ወደ አዳራሹ ለመግባት ከፈለጉ ወጣቶች ጋር ሲጨቃጨቁ መቆየታቸውን የሚናገሩት የሐምሳ አለቃ ሹምዬ ያለው ሾልኮ ወደ አዳራሹ መግባት የቻለ ወጣት ከአንዲት እድምተኛ የእጅ ስልክ ሰርቆ ሊወጣ ሲል በመያዙ ጭቅጭቁ ወደ ለየለት ድብድብ ማምራቱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ድንጋይ፣ ብረትና ዱላ ማንነት ሳይለዩ በሰው አካል ላይ ማረፍ በመጀመራቸው እጃቸው የተሰበረ፣ የተፈነከቱና የተረጋገጡ ሰዎች ብዛት ቁጥር አልነበረውም፡፡ከውጪ የነበሩ ወጣቶች ጓደኛቸው ሰርቆ ተይዟል መባሉን እንደውሸት በመቁጠር ድንጋይ መወራወር በመጀመራቸው መልስ ለመስጠት የሰርጉ ታዳሚዎች ያገኙትን ይዘው ድንጋይ ወርዋሪዎቹን መፋለም ይጀምራሉ፡፡በዚህ መሐል ከሁለቱም ወገን ለጉዳት በመዳረጋቸው ሆስፒታል መመላለስ የሰርጉ አዘጋጆች አጣ ፈንታ በመሆን ሰርጉ ተጠናቅቋል ››ብለዋል፡፡
ሰርጉን ለማጀብ የተገኙ ሁለት መኪኖችም በድንጋይ የፊትና የኋላ መስታወቶቻቸው ረግፎባቸዋል፡፡ሰርጉ እንዲከናወንበት አዳራሹን ያከራየው የሐምሌ 19 መናፈሻ አስተዳደር በቂ ጥበቃ ባለማዘጋጀቱና በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶችም ለራሳቸው ደህንነት በመስጋት መሰወራቸው ለሰው አካልና ለንብረት መጎዳት ከፍተኛ አስተዋእጾ ማበርከቱን ሐምሳ አለቃ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment