በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ወያኔ-ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ሥራ በጣም ቢያመዝንም የሚመሰገንበት ሥራ የጽሑፍ ቁጥጥርን ማስቀረቱ ብቻ ነው፤ ሁልጊዜም አንድ ጥሩ ነገር የሚያስከትለው አብዛኛውን ጊዜ የማይጠበቅ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ለምሳሌ አጠቃላይ ነጻነት ሲመጣ ወንጀለኛነት ይጨምራል፤ እንዲሁም የጽሑፍ ቁጥጥር ሲነሣ ጸሐፊዎች ይበዛሉ፤ ትምህርት በተስፋፈበትና ማንም እንደፈለገ ለመጻፍና ለማሳተም ችሎታውም ዕድሉም በማይገኝበት፣ ሳያበጥርና ሳይሰልቅ አሰር-ገሰሩን ጽፎ በአደባባይ የሚወጣውን ጥምብ-እርኩሱን አውጥተው ሁለተኛ እንዳይለምደው የሚያደርጉ የታወቁና የሰላ አእምሮና ብዕር ያላቸው አርታእያንና ሐያስያን (ገምጋሚዎች) ባሉበት ብዕሩን የሚያባልግ ጸሐፊ አይወጣም፤ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ብዕርን ማባለግ እንደመብት ወይም እንደነጻነት እየታየ ነው፡፡
በአደባባይ የሚጽፉ ሰዎች ሁለት ነገሮችን ለይተው መገንዘብና ለሌሎችም ሲየያስተላልፉ ለይተው ማስተላለፍ አለባቸው፤ አንዱ የሆነና የተረጋገጠ ሁነት ነው፤ይህንን ሳይበርዙና ሳይከልሱ እንዳለና እንደተገኘ ማስተላለፍ ግዴታ ነው፤ ሁለተኛው የራስ አስተያየት ነው፤ የጠራውንና የነጣውን አውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብቶ ማቅረብ ወይ አለማወቅ ነው፤ አውቀው ከሆነም ለማታለል ከመሞከር የሚቆጠር ነው፤ በአለንበት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ የምናየው ፊደሎቹን ማወቅ እንደሙሉ እውቀት ይቆጠራል፤ ወይም በሌላ አነጋገር ፊደልን ማወቅ የመጻፍ ችሎታን ይሆናል፤ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፤ ፊደሎችን ማወቅ ትልቅና መሠረታዊ የእውቀት ጎዳና ላይ መግባት ነው፤ ጎዳናው ግን በጣም ረጅም ነው፤ በእውቀት ጎዳና ላይ መግባት የእውቀት ባለቤት ከመሆን ጋር እንዳይደባለቅ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአገራችን ፊደልን ማወቅ ሌላም አደጋ አለው፤ ፊደልን ማወቅ ከሥልጣን ጋር ሲጋባ የሚያስከትለውን ውድቀት ከአንዴም ሁለቴ አይተናል፤ እያየንም ነው፤ ስለዚህም ፊደል ኃላፊነትን ያመጣል፤ አለዚያ በአለፉት ሠላሳ ዓመታት ያየነው ውድቀት እየተከበረ ይቀጥላል፡፡
መጻፍ እንደመናገር ሊቆጠር ይቻላል፤ሆኖም በመጻፍና በመናገር መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ በንግግር ላይ ከሰዎች በሚቀርበው ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ እንዲህ ማለቴ ነው ብሎ የተናገሩትን እዚያው ለማረምና ለማስተካከል ይቻላል፤ በተጻፈ ነገር ላይ እንዲህ ዓይነቱ ወዲያው የመታረም ዕድል የለም፤ ስለዚህም ለመጻፍ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት ነው፤ ከላይ እንደተገለጸው ፊደልና ሥልጣን ሲጋቡ ሰንደቅ ዓላማው ጨርቅ ነው ከማለትም ሊያልፍ ይችላል፤ ለምሳሌ የደርግን የትርፍ ቤቶች አዋጅ ብንመለከተው ‹‹ትርፍ ቤት›› ሲል ትርፍን እንተወውና ‹‹ቤት›› ለሚለው ትክክለኛ ትርጉም አልሰጠም፤ ስለዚህም በጭራሮ የተያያዘ ምንም ‹‹ቤት›› የሚያሰኘው (መኝታ ቤት፣ ወጥ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት፣ … የሌለው) በሃምሳ ሳንቲም የሚከራይ ነገር ‹‹ቤት›› ተብሎ በሺህ ብር ከሚከራይ ቤት ጋር ተወረሰ! ያፈረ የለም እንጂ አሳፋሪ ነው!
እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከየት የሚመጣ ነው? አንድ አጠቃላይ የአስተሳሰብ ችግር አለ፤ ለየት ያለውን ከጅምላው፣ ግዙፉን ከረቂቁ፣ አንዱን ከብዙው ያለጥንቃቄ ማደባለቅ በአማርኛ በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ የአስተሳሰብ ችግር ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ (አበሻና ሆድ የሚለው ጽሑፍ ባሕር ተሻግሮ የአበሻን ነገር-ዓለም ትቶ የተጠበሰ ውሻ (ሆት ዶግ) የሚበላውንም አስቀየመውና ሌሎች ስለአበሻ የጻፍኋቸውን ተውኩት እንጂ አበሻና መናገር የሚለው በተለይ ለባሕር ማዶው ዘሎ-ጥልቅ ተስማሚው ነበር፤) በማናቸውም ነገር ላይ ለመቀባጠር በጣም ኃይለኛ ምኞት አለው፤ አንዱ ያስተሳሰብ ችግር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሳያስቡና ሳይጨነቁ አፍ እንዳመጣ ከመናገር ልማድ ጋር የተያያዘ ነው፤ አሁን ደግሞ የጎሠኛነት ሥርዓት ካመጣብን ጣጣ ዋኖቹ የአስተሳሰብ ችግሮች እነዚህ ናቸው፤ የቡድን መብትን መሠረታዊ አድርጎ የግለሰብን መብት ጨፍልቆ የተነሣው የወያኔ የጎሣ ሥርዓት ከሃያ ዓመታት በኋላ በስንት ጥረት የደረሰበት አሁንም የተዛባ ድምዳሜ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ጎን ለጎን አቁሞ እኩል ናቸው ማለትን ነው፤ ለውጡ የተጣራ ባይሆንም ሃያ ዓመታት መፍጀቱ የወያኔን የመማር ፍጥነት የሚያመለክት ነው፤ የሥልጣን ጉልበትና የሥልጣን ምኞት ተጽእኖ እንደአንድነት ያለውንም የፖሊቲካ ፓርቲ ፐሮግራሙን እንዲለውጥና የግለሰቦችንና የቡድን መብቶች በአንድ ደረጃ ላይ እንዲያስቀምጥ ተደርጎአል፤ ከቡድን ውስጥ ግለሰቦች ሁሉ ሙልጭ ብለው ሲወጡ ስለቡድን መብት የሚያወራ ምን እንደሚባል እንጃ! ከቀኝ ወደግራ የዞረ? ወይስ ከግራ ወደቀኝ? ወይስ … ቀኝ ፖሊቲካ ባዶ ከረጢት ይዞ ይቀራል።
በተደጋጋሚ እንዳየሁት ለግለሰብ መብቶች የቆመ ቀኝ-ዘመም፣ ለቡድን መብቶች የቆመ ግራ-ዘመም የሚባል ይመስላል ይህ ስሕተት ነው።
ቀደም ሲል የታወቀው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እኔን ቀኝ-ዘመም እያለ ጽፎ ሳይ ይህ ሰው በአውነት አንድ መዝገበ ቃላት ማየት አቅቶት ነው? ወይስ እኔን በተለየ ዓይን ለማየት ከመፈለግ የተነሣ ነው? ወይስ የሲአይኤውን መልክተኛ ፖል ሄንዜን ሰምቶ ነው? የሱ ጎሣ አባል መሆንንና አለመሆንን እኔ የምመርጠውና የምወስነው አይደለም፤ ታምራት በኢትዮጵያዊነት ወይም በዜግነት ዓይን ሊመለከተኝ አለመቻሉም የእኔ ጥፋት አይደለም፤ ሁሉም ቢቀር በሰውነት ደረጃ ሊያየኝ ይችል ነበር፤ ይህንንም አልቻለም፤ እንግዲህ ወይ እኔ ሰው አልሆንኩለትም፤ ወይ እሱ ወደሰውነት ደረጃ አልደረሰም፤ በታምራት ነገራ ቀኝ-ግራ መጋባት እንደኔው ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ የነበረው ክፍሉ ሁሴን ወደጥናት ተመልሶ የታምራትን ስሕተት አረጋገጠ፤ እኔም እንዲሁ አደረግሁና የታምራት ነገራን ግራ መጋባት አረጋገጥሁ፤ ታምራት ነገራ የጎሣ ቀኝ ገብቶት ግራ ፖሊቲካ ቀኝ ሆኖበታል! ቀኝ-ግራ ፖሊቲካ በጎሣ አባልነት የሚገኝ ወይም የሚታጣ ይመስለዋል፤ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሀብትና ሌላ ማናቸውንም ነገር ከቁም-ነገር ሳይቆጥሩ ለማንም ሰው በሰውነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን መብት እንዲያገኝ ቆሞ መከራከር ለታምራት እንግዳ ነገር ይመስለኛል፤ ገና እሱ ሳይወለድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር በተደረገ ስብሰባ ላይ ለምን የኢትዮጵያ ራድዮ በኦሮምኛ አይናገርም? በማለት ጌታቸው ኃይሌ ጋር ሆነን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎችን ሞግተን ነበር፤ ይህ ለታምራት የቀኝ ፖሊቲካ ነው፤ የሱ ጎሣ-ዘመም ፖሊቲካ ግራ መሆኑ ነው! ጎሠኛነት ምን ጊዜም የትም ቦታ እንደግራ ፖሊቲካ ተፈርጆ አያውቅም።
አሁን ደግሞ ሰሎሞን አብርሃም ይህንኑ የታምራት ነገራን ስሕተት ለመድገም የዳዳው ስለመሰለኝ በዝምታ ለማለፍ አልፈለግሁም፤ ሰሎሞን (liberalism) የሚለውን የአንግሊዝኛ ቃል በባሕርዩ የሌለበትን ትርጉም ሊሰጠው ይዳዳዋል፤ ሰሎሞን አብርሃም ሊጽፍበት የተነሣው ጉዳይ በእኔ ግምት በጣም ወቅታዊና አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የግል ስሜትን ከሁነት ጋር፣ ያልተጣራ የተውሶ ሀሳብን (‹‹ፊዩዳሊዝም፣ ሊበራሊዝም››…) ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስተሳሰቡን ያጎደፈው ይመስለኛል፤ ያነሣው ጉዳይ በተለይም እንደሱ ላለ ፖሊቲከኛ ከስሜተኛነትና ከወገንተኛነት የጸዳ ቢያደርገው (‹‹ወግ አጥባቂ፣ቀኝ አክራሪ›› ..)፣ወይም ደግሞ ያልተጣራ (‹‹የሊበራል ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ይመስላሉ፤›› እያለ በጎን ከሚጎሽም የጸዳውን እውነት ፊት ለፊት እያቀረበ ድካማቸውን ቢተነትን የሚጠቅም ይሆን ነበር።
ግራና ቀኝ ፖሊቲካ የሚባለውን ከጎሣ ፖሊቲካ ጋር ለማገናኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወጣቶችን ወደአስከፊ ስሕተት እንዳይመሩ መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል፤ የጎሣ ሥርዓትን የሚቃወሙትን ወገኖች በሌላ መንገድ ለመቋቋም ቢሞክሩ የተሻለ ነው፤ በጎሣ ክፍፍል ማመን ሌላው ቀርቶ በሰውነት ደረጃ ለመሰለፍም ያስቸግራል፤ ለማናቸውም የጎሣ ፖሊቲካን ከግራ ፖሊቲካ ማዛመዱ እሳትና ውሀ ነው።
No comments:
Post a Comment