Thursday, January 30, 2014

“ኢትዮጵያውያን ለምንድን ነው የውጭ ገበሬዎች የሚያስፈልጓቸው? ምንድን ነው ይዘውልን የሚመጡት?” አቶ ግርማ

"አንድም ሰው ከቀዬው እንዲፈናቀል አልተደረገም" ሚኒስትር ዴኤታ

displaced anuaks


  • “ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች እንደታሰቡት ውጤታማ አልሆኑም” መንግሥት
  • መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን አይመለከትም አለ
የውጭ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው እያለሙ እንጂ፣ መሬት ለመቀራመት ብለው ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም ሲል ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
“መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም፤” ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ የመሥሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማው ማክሰኞ ዕለት ሲያቀርቡ፣ ሰፋፊ መሬቶች ወስደው በግብርና ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ስለሚገኙ የውጭ ባለሀብቶች ትክክለኛ ማብራሪያ እንዲሰጡ በተጠየቁበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት፡፡
በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሠይፉ ለሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ፣ የውጭ ኩባንያዎች ሰፋፊ መሬቶች አንዳንዶቹ እንደሚሉት ቤልጂየምን የሚያህል መሬት ተሰጥቶ እየተካሄደ ስላለው ኢንቨስትመንት በቂ ማብራሪያ በሪፖርቱ ስላልተካተተ እውነቱ ሊብራራ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሚካሄድ የግብር ኢንቨስትመንት ችግር የለውም ያሉት አቶ ግርማ፣ በመንግሥት ላይ እየቀረበ ያለው ክስ አርሶ አደሮች እንዲፈናቀሉ ማድረጉ አንዱ ነው ብለዋል፡፡
forced displacementየውጭ ኩባንያዎቹ ብድር የሚያገኙት ከኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ መሆኑን በማስታወስ፣ “በኢትዮጵያ ገንዘብና በኢትዮጵያ መሬት ለምንድን ነው የውጭ ኩባንያዎች መጥተው የሚያለሙት?” በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን ለምንድን ነው የውጭ ገበሬዎች የሚያስፈልጓቸው? ምንድን ነው ይዘውልን የሚመጡት?” በማለት አቶ ግርማ የሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረቡት ብቸኛው የግል ተመራጭና የምክር ቤት አባል ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ በሰፋፊ የግብርና መሬት ላይ በሚካሄደው ኢንቨስትመንት የምዕራባዊያን ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለምን የማስተዋወቅ ሥራ አይሠራም በማለት፣ የህንድና የቻይና (የምሥራቁ የዓለም አገሮች) ኩባንያዎች የጐላ ተሳትፎ ሚዛኑን መጠበቅ ይገባዋል የሚል መልዕክት ያለው ጥያቄያዊ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች በጋራ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በሰፋፊ መሬቶች ላይ ለሚካሄድ የግብርና ኢንቨስትመንት ሲባል አንድም ሰው ከቀዬው እንዲፈናቀል አልተደረገም ብለዋል፡፡
ሁለቱም ምስሎች በጋምቤላ አካባቢ ከሳተላይት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ቀያዮቹ ነጥቦች በሙሉ በመሬት ነጠቃ ከቀያቸው የተፈናቀሉና ቤታቸው የፈረሰ አባወራዎችን ሲሆን ቢጫዎቹ ደግሞ ተፈናቃዮቹ በግዳጅ የሰፈሩበትን ነው፡፡
ሁለቱም ምስሎች በጋምቤላ አካባቢ ከሳተላይት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ቀያዮቹ ነጥቦች በሙሉ በመሬት ነጠቃ ከቀያቸው የተፈናቀሉና ቤታቸው የፈረሰ አባወራዎችን ሲሆን ቢጫዎቹ ደግሞ ተፈናቃዮቹ በግዳጅ የሰፈሩበትን ነው፡፡
“የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆኑ ነፃ መሬቶችን ብቻ ነው ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የምንሰጠው፡፡ ማንም ከቀዬው አልተፈናቀለም፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሚደረግ የግብር ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንደሚጠይቅ የተናገሩት ማኒስትር ዴኤታው፣ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሆነ በባለሀብቶቹ ቀደም ብሎ ተይዞ የነበረው እምነት ኢንቨስትመንቱ ቀላል እንደነበር፣ ነገር ግን በተግባር ሲታይ ጊዜ የሚወስድና አቅም የሚጠይቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለባለሀብቶቹ የሚሰጠውን የመሬት መጠን እየቀነሰ እንደሚገኝ፣ በአጠቃላይ ግን ትልቅ አቅም የሚፈጥር ዘርፍ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ በፌዴራል መንግሥት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች 43 መሆናቸውን አስረድተው፣ ከእነዚህ ውስጥ 15 የሚሆኑት ብቻ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ በአብዛኛው እየተሳተፉ የሚገኙት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በበኩላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት መቀራመት የለም ብለዋል፡፡
አሁን ባለው የዓለም የዕድገት ሁኔታ የገንዘብ አቅም ያለው በምሥራቃውያን አካባቢ መሆኑን፣ ምዕራባውያኑ በዘርፉ ያልተሳተፉት የአቅም ችግር ስላለባቸው እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
“የመሬት መቀራመት ጉዳይ እየተነሳ ያለው ከዚሁ የዓለም ጂኦ ፖለቲካ አካባቢ ነው፡፡ ከምሥራቅ የዓለም አገሮች ወደ አፍሪካ እየመጣ ያለ ኢንቨስትመንት ስለማይወደድ ነው፤” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩም ሆነ የሥራ ባልደረቦቻቸው የውጭ ኩባንያዎቹ እያገኙ ስላለው ከፍተኛ ብድር ግን ማብራሪያ ሳይሰጡበት ታልፏል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እንደሚያስረዳው፣ በ2006 ዓ.ም. የመኸር ወቅት 253 ሚሊዮን 805 ሺሕ 340 ኩንታል ምርት ሊገኝ እንደሚችል፣ ይህም ካለፈው ዓመት ዘጠኝ በመቶ መጨመሩን ነው፡፡ (ሪፖርተር)
http://www.goolgule.com/why-ethiopia-needs-foreign-farmers/

No comments:

Post a Comment