Tuesday, January 28, 2014

ከቀይ ወደ ሰማያዊ ጉዞ

ቹቸቤ

ከቀለማት ሁሉ ‘ቀይ’ አገራችንን አቅልሞ መዶሻው ቁልቁል ሲወቅረን ማጭዱ ከታች ሲያጭደን ኖረን ያለቀው አልቆ የተረፍነው ፈዘንና ደክመን ባለንበት ሰዐት ማጭዱንና መዶሻውን በብጫ ቀለም  ሸፍነው በትግራይ ስም አጨዳውን የቀጠሉበትና ቀን የሰጣቸው ጎጠኞች አገርም ሕዝብም ሊያጠፉ እንደገና በወገን ደም እያጨቀዩን ይገኛሉ። ቢሆንም ተስፋችን አላሟጠጠም። ብርቱዎች ቆርጠውና ቀልጥፈው ለነጻነት የሚደረገውን ትግል በሁሉም መስክ አፋፍመዋል። አዲስ የሆነው ነገር ከቀይና ነጭ ሽብር በሁዋላ ሰማያዊ ሰላማዊ ትግል የሚል መፈጠሩ ነው። ታሪክ ያልዘገባቸው ግን ከቀይ ሽብር ወደ ብጫ ስካር በሚል ጠጅ ቤት የቀሩ የአብዮት ትራፊ ወጣቶችን ህይወት ነው።Ethiopia’s Blue party (Semayawi party) leaders in police control
ርዕሱን በቀለም ጀምረነዋልና ሰማያዊ ፓርቲ በአውሮፓና በአሜሪካ ሃዋርያውን ልኮ ዓላማውን ሲያሳውቅ የሰነበተው በልደትና  በጥምቀት ሰሞን ነበርና ፓርቲው በመወለዱ ደስ ያላቸውና በመጠመቁና በማጥመቁም የጨፈሩ በርካቶች ናቸው። ወጣቱ ትውልድ ያገባኛል ይገባኛልም  ሲል ደስ ይላል። ደስታ ብቻም ሳይሆን ተስፋም ይሰጣል። ይልቃል ሰማያዊን ፓርቲዬ ብሎ ያላወቀውን ሲያሳውቅ ያወቀውንም  ሲያጠምቅ ሰንብቶ ወደ አገር ቤት የመልስ ጉዞ ከማድረጉ በፊት ለምታደርጉልን ድጋፍ አድናቆት አለኝ በማለት የኢትዮጵያ የወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክን እድምተኞች አመስግኖ እንደጋገፍ እንበርታ በማለት ተሰናብቷል። ሌላኛው አጋሩ ብርሃኑም ደከመኝ ሳይል የተጠየቀውን ሁሉ ሲመልስ አርፍዷል። የልብ የልቡን ጥያቄ ያቀረበው እንደልቡም ጥሩ ውይይት መርቷል። ይቺን ማስታወሻ ስጽፍ ውይይቱ በሰፊው ቢሰራጭስ የሚል ማመልከቻ ላስገባ ነበር ግን የልቤን ልባሙ ሰው አውቆ ኖሮ ያሰብኩትን ሆኖ አገኘሁት።
ሰማያዊ ፓርቲ በወጣቶች የተገነባ ድርጅት ነው። እድሜ ጠገብ አዛውንቶችና እውቀት ጠገብ ምሁራኖችም ከጀርባው ይኖራሉ ብለን እናምናለን። እንዳለፈው ትውልድ የሀገር ፍቅር ስሜታቸውን ለሀገር ጥፋት የቆሙ መሰሪዎች እንዳይጫወቱበት ካለፈው በሚገባ ይማራሉ የሚል ተስፋም ይኖራል። ከምንም ነገር በላይ ግን አበቃለት የተባለው ወጣት የበቃለት ቁርጠኛ የነጻነት ታጋይ ሆኖ ሲነሳ ማየትን ያህል የሚያስደስት ነገር የለም። ወጣቱ ታሪክንና ትናንትን መማርያው አድርጎ እውቀትን ግን መመርያው ካደረገ ነገን ያሰበበት መድረሱ እርግጥ ነው። የዛሬዎች ጎልማሶች ትናንት በስሜትና በሀገር ፍቅር ተነስተው ዛሬ አገራቸውን ለሚያምሱ ጎጠኞች መሳርያ መሆናቸውን ሲያስቡ ልባቸው መድማቱ አይቀርም። የዚያኑ ያህል ዛሬን ድረስ የተሰራባቸውን ግፍ መለየት የማይቸሉ ወይም ያንን ቢለዩና ቢናገሩ ታሪካቸውና ህይወታቸው ወና ስለሚሆንባቸው በ’ተከድኖ ይብሰል’ የሚኖሩ ብዙ አሉ ይህንን ለቀጣዩ ትውልድ አልመኝም።
የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ካለፈው ሊማሩ የሚገባው ይህ ነው። ከምንም ነገር በላይ ዛሬ የማሰብና ያሰቡትን የመናገር መብት ያለበት ድርጅትን አጠናክሮ መንቀሳቅስና በተግባር ደግሞ መፈተንን ማስመስከር ይገባቸዋል። የስልጣንና የስራ ክፍፍልን ለሁሉም ማዳረስና ድርጅት አንጂ ግለሰብ ብቻ የሚገንበት እንዳይሆን ተግቶ መስራትም ይጠበቅባቸዋል። የዘመናችንን ጎጠኛና ሁዋላ ቀር ገዢ ማንነት በሚገባ እንዲታይ ዱላውንና ጥቃቱን ተቀብለው በቁርጠኛነት መነሳታቸው ደግሞ  ያኮራል። ከዘረኞቹ ገዢዎች ጋር ከሚደረገው ትግል ባሻገር ደግሞ የተኙትን የሚያነቃ የሰነፉትን የሚያበረታ ስራ መስራታቸውም ግሩም ነው። ተባብሮ ከመተኛት ከፊት ቀድሞ ሌሎቹንም ማነሳሳትም  ቸል የሚባል አይደለም። አንዳንዴ ከትብብርና ከውህደት በፊት መሆን ያለባቸው ነገሮችን በመዘንጋት የትብበር ጥሪ ማብዛቱም ደግ አይደለም። ስኳር ቡናው ውስጥ ስለገባ አያጣፍጠውም  ከስር ሄዶ ይተኛል እንጂ፣ እንዲጣፍጥ መማሰል አለበት። ቡናው እስኪፈላ መቆላት መፈጨት መንተክተክ አለበት ስኳሩም  እንዲሁ ብዙ ጉዞ አለው። እንዲያም ሆኖ መጥፎ ቡናን በስኳር ብዛት ማጣፈጥ አይቻልም። ድርጅቶችንም  ተባበሩ ስላልናቸው  ጠንካራ ና ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም።
በመጨረሻም ምሰጋናና ማበረታቻችን ሁሉ እያደረግን ከቀይ ወደ ሰማያዊ የምናደርገው ጉዞ የተሳካ እንዲሆን  ድጋፋችን አይለያቸው። “ግባችን እሩቅ መንገዱ ጠመዝማዛ ነው” ከሚለወ ተስፋ አስቆራጭ መፈክር “መንገዱ በስኬት የተሞላ ከግብ  መዳረሻችንም ቅርብ ነው” በሚል አዲሰ መፈክር  ልሰናበት።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10824/

No comments:

Post a Comment