Wednesday, September 4, 2013

የፀረ-ሽብር አዋጁ ለምን ይሰረዝ? ~ ስለሺ ሐጎስ


ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአገራችን አገልግሎት ላይ ባለው የፀረ-ሽብር አዋጅ ዙሪያ አንዳንድ የመወያያ ነጥቦችን ለማንሳት ሞክረን ነበር “የፀረ-ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል..” በሚል አብይ ርዕስ ለመዳሰስ የተሞከረው የተለያዩ አካላት በፀረ-ሽብር አዋጁ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን በራሱ መኮነን የዕውነትም የእውቀትም መሰረት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ የጥያቄዎቹን መነሻ ሰበቦች መመርመር ወደ እውነት የሚያደርሰን ብቸኛ መንገድ ነው ተባብለናል፡፡ የዛሬው ቀጠሮአችን የተመሰረተው የፀረ-ሽብር አዋጁን በጥንቃቄ አንድንመረምር በሚያስገድዱን ሶስት ነጥቦች ላይ ነው፡፡ ለመስታወስ እንዲረዳን ሳምንት ያነሳናቸውን እነዚህን ሶስት የመጠየቂያ ነጥቦች አስቀድመን ወደ ዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን እናልፋለን፡፡ ስለ አዋጁ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ስለ እንከን የለሽነቱ የሚሰብኩት መንግስትና ደጋፊዎቹ ብቻ መሆናቸውና የአዋጁን እንከኖች ከመንቀስ ጀምሮ ይሰረዝ እስከሚል ጠንካራ ውግዘት የሚያቀርቡት ደግሞ አሁን ያለውን መንግስት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚቃወሙ አካላት ብቻ ለምን ሆኑ? አዋጁ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ አስራ ሰባት ጋዜጠኞችና በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ፖለቲከኞችና የፓርቲ አመራሮች የዚህ አዋጅ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የመንግስት ተቃዋሚዎችና ተቺዎች ከዚህ አዋጅ ኢላማ ውጪ ናቸው ማለት ያስችላልን? መንግስት፣ በአሸባሪነት ተከሰው ስለታሰሩ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ሲጠየቅ የሚመልሰው የንጹሀን ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለደህንነታቸው የታሰበላቸው ንጹኃን ዜጎች መንግስት አሸባሪ ያላቸውን እስረኞች እንዲፈታ የታሳሪዎቹን ፎቶ በመያዝ አደባባይ ወጥተው ሲጠይቁ ስለምን ተስተዋሉ? ከነዚህ የማጠየቂያ ነጥቦች ተነስተን አዋጁን ስንበረብረው የዐዋጁ ዋነኛ ዓለማ ምን እንደሆነና አዋጁ ግንባር ቀደም ኢላማ ያደረገው እነማንን እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን፡፡ የአዋጁን ትክክለኛ አላማና ኢላማውን መለየት ደግሞ ለምን ይሰረዝ? ለምንስ አይሰረዝ? ለሚሉ ጥያቄዎች ልብ የሚሞላ ምክኒያታዊ ምላሽ ለማግኘት ያስችላል፡፡ አላማና ኢላማው ገዥው ፓርቲ ይህንን አዋጅ ለምን እንዳፈቀረው፣ለምንስ ከሌሎች ህግጋት ሁሉ የበለጠ እንዳሚሳሳለት፣ በእርሱ የመጣ ባይኔ መጣ ያሰኘው ምን እንደሆን ከራሱ አንደበት የተደመጠ ነገር የለም፡፡ ተቃዋሚዎች ግን አዋጁን ለምን እንደጠረጠርኩት ባለፈው ስምንት ኢቲቪ ባሰተላለፈው የፓርቲዎች ክርክር ላይ አፍረጥርጠውታል፡፡ ይኸውም “የአዋጁ አላማ ኢህአዴግን የሚቃወሙና የሚተቹ ዜገችን ስጥ ለጥ እንዲሉ ማድረግ ሲሆን ዋነኛ ኢላማዎቹ ደግሞ እኛ ነን” የሚል ነው፡፡ ይህ ጥርጥሬ ብቻ አይደለም፡፡ ፓርቲዎቹ ለድምዳሚያቸው መነሻ የሆኗቸውን በርካታ ማሳያዎች አቅርበዋል፡፡ የፓርቲዎቹንና የኢሀአዴግን ጉዳይ እዚሁ ጋር እንተወውና ወደ ራሳችን የፍተኝ ነጥቦች እናምራ አዋጁ ለምን አላማ ወጣ? እነማንን ኢላማ ያደረገ አዋጅ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በአዋጁ የተካተቱን አንቀጾች ቴክኒካዊ የህግ ትርጓሜ አንድምታ በመነሳት መተንበይ ይቻል ይሆናል፡፡ እኔ ግን ይሄን መንገድ አልመረጥኩትም፡፡ ያልመረጥኩት ደግሞ በሌላ ምክኒያት ሳይሆን ስለማላውቅ ነው፡፡ ይልቁንም እኔ በአዋጁ ላይ ያለኝ ዕውቀት የሚነሳው መሬት ላይ ካለው እውነት ነው፡፡ ዐዋጁ የተለጠጠ ትርጓሜ ያላቸውን ድንጋጌዎች መያዝ አለመያዙን አንቀጽ እያጣቀስኩ ቃል እየመነዘርኩ ላስረዳችሁ የሚያስችል ምንም የህግ እውቀት የለኝም፡፡ የእኔ እውቀት “መለስ በቃ” የሚል መፈክርን ፎቶ ማንሳት ብቻ ህገ መንግስቱዊ ድንጋጌዎችን በሃይል ለመናድ፣.በአሸባሪ ድርጅት ውሥጥ በአመራርነትና በውሳኔ ሰጭነት በመሳተፍ፣ ለአሸባሪ ድርጅቶች አባል በመመልመል፣ በማሰልጠንና በማደራጀት ወ.ዘ.ተ በሚሉ ክሶች ወንጅሎ 14 ዓመት ለማስፈረድ የሚያስችል አዋጅ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን የአዋጁ ድንጋጌዎች ያለቅጥ የተለጠጡ በመሆናቸው ብቻ ነው ለማለት አልችልም፡፡ የከሳሹ ፍላጎት ያለቅጥ በመለጠጡም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህ አዋጅ ተከሰው በእስር የሚገኙ ፓለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ስብዕና ቀድም ብሎ የሚያወቅና አደረጉ የተባሉትን ተግባራት የሚያውቅ ሰው “ታዲያ አሸባሪ ያልሆነ ማነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ነው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን እንደ ምሳሌ ማየት ይችላል፡፡ ርዕዮትን በምሳሌነት የማነሳው በደምብ ስለማውቃትና የፍርድ ሂደቷንም በቅርብ የተከታተልኩት ሰለሆነ ብቻ ነው፡፡ ርዕዮት ዛሬ በእስር ላይ የምትገኝ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ሁለት ሰዎች ተጫጩኸው ሲነጋገሩ ቆማ ማድመጥ የማትችል ፍፁም ሰላማዊ ሰው ነበረች፡፡ ቤተሰብ የማስተዳደር ሃላፊነት የተኸከመች ሆና ሳለ ከአነስተኛው የመምህርነት ደሞዟ ላይ ቀንሳ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ ተማሪዎቿን ለመርዳት ወደ መስሪያ ቤቷ በእግሯ ስትመላለስ አውቃለሁ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን መንግስት እንዳበደ ሰው አስሯት ሲያበቃ በአሸባሪነት አስፈርዶ ይኸው ሀገሯ በቃሊቲ ከሆነ ዛሬ 807ኛ ቀኗ ነው፡፡ የመንግስት ባለ ስልጣናት ስለ ርዕዮት አሸባሪነት ሲያወሩ ብቻ ሰይሆን አጠፋች ሰለተለባለው ነገር ማስብ ስጀምር ልቤ ስራ ይፈታብኛል፡፡ የፌድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በርዕዮት ላይ ፍርድ ያልተላለፈ ዕለት ያነበበው የሚከተለውን ነበር፡፡ “በአዲስ አበባ አንዳንድ የአደባባይ ቦታዎች ላይ በቀይ ቀለም “መለስ በቃ” የሚል ዓመፅ የሚያነሳሳ ፅኁፍ ሲፃፍ ቦታው የት እንደሆነ ተከታትላ ፎቶ በማንሳት መረጃ አስተላልፋለች፡፡ ታዛቢዎች ባሉበት ከርሷ ኢሜይል ፕሪንት ተደርጎ የወጣ “ሶሊዳሪቲ ሙቨመንት ፎር ኒው ኢትዮጵያ” የሚል ፅኁፍ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ከህግ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ሀይል የሚራምደው አቋም ስለሆነ በመረጃ ማስተላለፍ ላይ ይህ ሲታከልበት ይግባኝ ባይ የፈፀመችው የጋዜጠኝነት ስራ ነው የሚል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ የቀረቡ ማስረጃዎች ይገባኝ ባይ የሽብርተኛ ድርጅት አባል ናት ለማለት የሚያስችል ባይሆንም ለሽብርተኛ ድርጅት የሚደርሉ መረጃዎችን በማቀበል በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ የተሳተፈች ስለመሆኑ የሚያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በሁለተኛው ክስ ላይ የተጠቀሰው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ አዋጅ ቁጥር 652/2002 አንቀጽ 7/1/ በሽብርተኛ ድርጀት ውስጥ በማንኛውም መልኩ የተሳተፈ…. የሚለውም ይህንን የሚያካት ነው፡፡” ይሄን የፍርድ ቤት ውሳኔ ለቁጥር ለሚታከቱ ጊዜዎች አንብቤዋለሁ፡፡ ርዕዮት የፈፀመቸውን ወንጀል ፈልጌ ማገኘት ግን አልቻልኩም፡፡ ለአመፅ የሚያነሳሳ ወንጀል ሆኖ የቀረበው “መለስ በቃ” የሚለው ፅሁፍ ነው፡፡ ርዕዮት ግን ይህን አልፃፈችም፡፡ ስህተቷ ሆነ የቀረበው “ለሽብርተኛ ድርጅቶች የሚደርሱ መረጃዎችን በማቀበል” የሚለው ነው፡፡ በድረ ገጽ የሚለቀቅን ዜና ለአሸባሪ ድርጅቶች እንዳይደርስ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል ግን የሚያወቀው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ በርዕዮት የተፈፀመ አንዳችም የወንጀል ድርጊት ሳይኖር በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፏን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል፡፡ በየትኛው የሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ? የሚል ጥያቄ ካነሳችሁ ግን መልሱ አይታወቅም፡፡ በአልቃይዳ ውስጥ ይሁን በአልሸባብ ውስጥ አሁንም ከሰይጣን በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለ18 ዓመታት እስር ከዳረጉት ሰበቦች አንዱ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ነው፡፡ የህወሃት አንጋፋ ታጋይና የሀሳብ አባት ተደገርው የሚወሰዱት አቶ ሰብሃት ነጋ የዚሁ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘውትር ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የፀረ-ሽብር ዐዋጅ አቶ ሰብሃትን ገልመጥ እንኳ ለማድረግ ጉልበት አላገኝም፡፡ “ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ የበለጠ እኩል ናቸው፡፡ እንዲል፤ ጆርጅ ኦርዌል፡፡ እነዚህ የፈጠጡ እውነቶች የሚነግሩን የፀረ-ሽብር ዐዋጁ የፀደቀበትን አላማ ቅርጥፍ አድርገው የሚበሉ ተግባራትን በመከወን ላይ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የፀረ-ሽብር አዋጁ ይሰረዝ የምንልበት አንድ አብይ ምክኒያት ይህ አዋጅ አሸባሪነትን በበቂ ሁኔታ መመከት የሚያስችል አቅም የሌለው መሆኑ ነው፡፡ “Trigger factors of terrorism” የተባለ አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ የሽብርተኝነት መቀፍቀፊያ የሆኑ አምስት ምንጮችን አስቀምጧል ከነዚህም አንዱ “የዴሞክራሲ ዕጦት፤ አፈናና የህግ የበላይነት አለመኖር ሀገር በቀል ሽብርተኞች እንዲቀፈቀፉ ያደርጋል፡፡” የሚል ነው፡፡ ይህ አዋጅ ሀሳብን በመቅጣት፣ተቃውሞን በማፈንና ዜጎችን በፍርሃት በመሸበብ የሚፈጥረው ስርዓት ሽብርተኝነትን በማባባስ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ማጠቃለያ በተለያዩ ክፍላተ አለማትና በተለያዩ አዝማናት የተነሱ አምባገነን ነግስታት ዜጎቻቸውን እንደሰም አቅልጠው ለመግዛት ያስቻሏቸው ሁለት መሰሪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ጠብ-መንጃ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ህግ ነው፡፡ በእኛም ሀገር የሆነው ይህ ነው፡፡ የሩቁን ትተን ደርግ፣ ሀገር ምድሩን በክላሽ እየቆላ 17 የግፍ ዓመታትን አስግፎን አልፏል፡፡ አሁን ኢህአዴግ ደግሞ ህግ የክላሽን ቦታ ተክቶ እንዲሰራ በማድረግ አገር ምድሩን በህግ እየቆላው ነው፡፡ ህግ የክላሽን ቦታ ተክቶ በሚሰራባት በዚያች ሀገር፣ ህጋዊነት ይሞታል፡፡ ህጋዊነት በሞተባት በዚያች ሀገር ደግሞ ማንም አይድንም፡፡ ህጋዊነት በሞተባት ሀገር፣ ጋዳፊ እደሆነው መሆን የሁሉም እጣ ፈንታ ይሆናል፡፡ ቀን ሲጥል እንደ ፍየል ታርዶ መጣል እንጂ፣ እንደሙባረክ ፍርድ ቤት የመቆም እድል አይገኝም፡፡ እናም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አንተም ለራሰህ ስትል ሰይፍህን ከፍትህ አንገት ላይ አንሳ፡፡

No comments:

Post a Comment