Sunday, September 15, 2013

የዓመቱ አወዛጋቢ፣ አነጋጋሪና ትኩረት ሳቢ አጀንዳዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)
የዓመቱ አወዛጋቢ፣  አነጋጋሪና ትኩረት ሳቢ አጀንዳዎች
የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አዲሱ አስተዳደር
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም መገባደጃ ላይ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የአገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ብዙዎችን ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ የዳያስፖራ ፖለቲከኞችና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢህአዴግ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ እንደሚፈጠር ስጋታቸውን ገልፀው ነበር፡፡ በአገር ውስጥም ተመሳሳይ ስጋት የነበሯቸው ወገኖች አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ስጋት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ በመስከረም 2005 ዓ.ም በጠ/ሚኒስትርነት ከተሾሙም በኋላ ለተወሰነ ጊዜ የቀጠለ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎችና የፖለቲካ ተንታኞች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ክፍተቱን ለመሙላት ለጊዜው ተቀመጡ እንጂ የጠ/ሚኒስትርነቱ ቦታ ከህወሐት እጅ እንደማይወጣ ተንብየው ነበር፡፡ ቢያንስ እስካሁን ግን ትንበያቸው የሰራ አይመስልም፡፡ በአዲሱ ህግ መሰረት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ለአስር ዓመት (ሁለት ተርም) በሥልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ ይጠበቃል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ተፎካካሪያቸውን (ብአዴን ያቀረባቸውን) አቶ ደመቀ መኮንንን በማሸነፍ ነው የጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣኑን የያዙት፡፡ በድምፅ ብልጫ የተሸነፉት አቶ ደመቀ መኮንንም ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው በተጨማሪ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለማግኘት ችለዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ሃላፊነታቸውን በቅጡ እንዲወጡ በሚል ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው ተነስተዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም በአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው በርካታ ሹም ሽሮችን አድርገዋል፡፡ ከሁሉም የሚቀድመው ግን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሚጠሩ ሁለት ተጨማሪ ባለስልጣናትን መሾማቸው ነው፡፡ ከኦህዴድ አቶ ሙክታር ከድር፣ ከህወኃት ደግሞ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሚኒስትርነት ከሚመሯቸው መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ሹመት አግኝተዋል፡፡ ይሄ ያልተለመደ አሿሿም ህገመንግስቱን የጣሰ ነው በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃወሙት ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በህይወት ሳሉ የታሰበበት ጉዳይ እንደነበርና ሥራን በጥራትና በብቃት ለማከናወን ታልሞ የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአቶ ኃይለማርያም አስተዳደር ትልቁ “ራስ ምታት”
ለአዲሱ የአቶ ኃይለማርያም መንግስት ከምንም በላይ ትልቅ ራስ ምታት የሆነበት “የሃይማኖት አክራሪነት” ጉዳይ ነው፡፡ ከእስልምና ምክር ቤት ምርጫ እና ከአወሊያ ት/ቤት ጋር ተያይዞ የተነሳው ውዝግብ “የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት መታሰርን ተከትሎ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን “ድምፃችን ይሰማ” እና “የታሰሩት ይፈቱ” የሚሉ ተቃውሞዎች በየጊዜው ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ አጀንዳቸው መሆኑ ደግሞ መንግስትን ክፉኛ አስቆጥቶታል፡፡ በአመቱ መገባደጃ ግድም በደሴ ከተማ ግድያ የተፈፀመባቸው የሼክ ኑሩ ይማም ጉዳይም ነገሩን የበለጠ አባብሶታል፡፡ መንግስት ሼኩን አክራሪዎች ስለመግደላቸው በቂ ማስረጃ አለኝ ሲል፤ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ጉዳዩን “የመንግስት ድራማ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ የአክራሪነት አጀንዳ በዚህ መልኩ አሁንም ድረስ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡ በ2006 መቋጫ ይበጅለት ይሆን?
ከ8 ዓመት በኋላ የተነሳው የሰላማዊ ሰልፍ እገዳ
ከ97 ምርጫ በኋላ ላለፉት 8 አመታት ታግዶ የቆየው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የተፈቀደው ባሳለፍነው አመት ነበር፡፡ በግንቦት ወር በሠማያዊ ፓርቲ የተጀመረው የተቃውሞ ሠልፍ፤ በአንድነት ፓርቲ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲም የጠየቃቸው አራት ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው በድጋሚ ሠላማዊ ሠልፍ መጥራቱ ይታወሳል፡፡ አንድነት ፓርቲ የ3 ወር የህዝባዊ ንቅናቄ መርሃ ግብር ዘርግቶ በ16 ያህል ከተሞች ሠላማዊ ሠልፎችና ህዝባዊ ስብሠባዎችን አድርጓል፡፡ “የሚሊየኖችን ድምፅ” በሚል ስያሜም አወዛጋቢ የሆነውን የፀረ ሽብር ህግ ለማሠረዝ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ይሄንን ተከትሎም አዋጁ ከወጣ ከአራት አመት ገደማ በኋላ በኢቴቪ አዘጋጅነት ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ትኩረትን የሳበ ጠንካራ ክርክር አድርገዋል – በዓመቱ መገባደጃ ላይ፡፡
“ፓርላማው ጥርስ አወጣ?” ወይስ ድሮም ነበረው?
ሌላው ዘንድሮ የታየ ጉልህ ለውጥ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱ ነው፡፡ ባለፉት 21 አመታት ባልታየ መልኩ ፓርላማው የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን የስራ ውጤት አጥብቆ ሲሞግትና ሲገመግም ተስተውሏል፡፡ ይሄን ያስተዋሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች “ፓርላማው ዘንድሮ ጥርስ አወጣ” ሲሉ አፈጉባኤውን ጨምሮ አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት በዚህ አይስማሙም፡፡ “ፓርላማው ድሮም ጥርስ ነበረው” የሚሉት አባላቱ እስካሁን ያልታየው ሚዲያው ትኩረት ሰጥቶ ስለማይዘግብ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ከህወሐት የመጀመርያ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ የምክር ቤቱን መነቃቃት ማጤናቸውን ጠቁመው “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን በመጀመሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ ያለው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ አሁን ብዙዎችን የሚያሳስባቸው ጥርስ አወጣ አላወጣም የሚለው ክርክር ሳይሆን የተጀመረው መነቃቃት ተጠናክሮ ይቀጥላል ወይስ እንደ ወረት ታይቶ ይጠፋል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ለጊዜው ይሄን የሚያውቀው ደግሞ መንግስት ብቻ ነው ይላሉ – አስተያየት ሰጪዎች፡፡
“መንግስት ይከሰሳል” የተባለበት ዓመት
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ ተወላጆች መፈናቀልም በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ክስተቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ በወቅቱ የተፈናቀሉት ቁጥራቸው ከ3ሺህ የሚልቅ ሠዎች፤ በአማራ ክልል ፍኖተ ሠላም ከተማ በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ ከተደረገ በኋላ፣ የክልሉ መንግስት አመራሮች “እኛ ሣናውቅ ነው የተፈናቀሉት” በማለት ወደነበሩበት እንዲመለሡ ተደርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በይፋ ድርጊቱን በማውገዝ በድርጊቱ የተሣተፉ ወንጀለኞች ለፍርድ እንደሚቀርቡ በፓርላማ ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ መንግስትን ለመክሠስ የሚያስችለንን ዝግጅት እያደረግን ነው ሲሉ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ተቃዋሚዎች ጉዳዩን ለፖለቲካዊ ጥቅማቸው እያዋሉት ነው ሲል ተችቷል፡፡ መንግስት ጥፋት ሲፈፅም ይከሰሳል ወይ የሚለውን በተመለከተ ግን ቁርጥ ያለ መልስ የምናገኘው ምናልባት ወደፊት ሊሆን ይችላል፡፡
ሶስቱ አነጋጋሪ የዓመቱ ምርጫዎች
በ2005 ዓ.ም ከተከናወኑ አበይት ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤት ምርጫ ይጠቀሳል፡፡ በሚያዚያ ወር በተካሄደው ምርጫ ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች “ምርጫ ቦርድ ለጥያቄያችን ምላሽ አልሰጠንም” በሚል ራሣቸውን ያገለሉ ሲሆን በዚህም አጋጣሚ “33 ፓርቲዎች” በሚል የጋራ መሠባሠቢያ መድረክ ለመፍጠር ችለዋል፡፡ ኢህአዴግ በምርጫው በተወዳደረባቸው አካባቢዎች ሁሉ ማሸነፉን ምርጫ ቦርድ የገለፀ ቢሆንም ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ኢህአዴግ ለብቻው ተወዳድሮ ለብቻው አሸንፏል በማለት ምርጫው “ፍትሃዊ” አልነበረም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ለአምስት አመት ያስተዳደሯትን ከንቲባ ኩማ ደመቅሳን አሰናብታ አዲሱን አቶ ድሪባ ከማልን የተቀበለችውም ባሳለፍነው ዓመት ነበር፡፡
የተጠናቀቀው አመት ከፖለቲካዊ ምርጫ ባሻገርም የሃገሪቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች መሪዎች ምርጫም አስተናግዷል፡፡ በጥቅምት ወር ላይ በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት አመራሮች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን በየካቲት ወር ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በእስልምና ምክር ቤት ምርጫ ሼህ ኪያር መሃመድ አማን በፕሬዚዳንትነት ሲመረጡ በፓትርያርክ ምርጫው አቡነ ማትያስ ተመርጠዋል፡፡
መንግስት ሙስና ላይ ያመረረበት ዓመት
ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው 21 ዓመታት እንደ ዘንድሮ በሙስና ላይ አምርሮ አያውቅም ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ነገሩ እውነት ይመስላል፡፡ በግንቦት ወር መጀመርያ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ሠራተኞች፣ ደላላዎችና ባለሃብቶች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፋንታ፣ የህግ ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እንዲሁም የአቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እሸቱ ወልደሠማያትን ጨምሮ ሌሎች የቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ትላልቅ ባለሃብቶች በአጠቃላይ ከ60 በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረው ጉዳያቸውን በፍ/ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ከታዋቂ ባለሃብቶች መካከልም የኬኬ ኃ.የተ.የግ.ማህ. ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎችም ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ ይገኙበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ዘጠኝ የስራ አመራሮችም በሙስና ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው በዚሁ ዓመት ነው፡፡ ከሙስና ጋር በተያያዘ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ከሃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃነ ሃይሉ እንዲሁም የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ዳሬክተርና ሁለት ምክትሎቻቸው ይገኙባቸዋል፡፡
መንግስት ከአቅሙ በላይ አቅዶ ይሆን? (የቤቶች ፕሮግራም)
ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ ትኩረት ሠጥቶ ከተንቀሳቀሰባቸው ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አዲሱ የቤት ፕሮግራም ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ሠዎች ይመዘገባሉ በተባለለት የቤት ፕሮግራም፣ 10/90፣ 20/80፣ 40/60 እና የማህበራት በሚል አራት ቦታ ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡ የቤት ፕሮግራሙ ውጤታማ ይሆናል አይሆንም የሚለው ጉዳይ ሲያወዛግብ የከረመ ሲሆን መንግስት በቁርጠኝነት አሣካዋለሁ ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ ስኬቱ ያጠራጥረናል ብለዋል፡፡ ከዚሁ የቤት ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ተመዝጋቢዎች የቁጠባ ሂሳብ በመንግስት ባንክ ብቻ እንዲከፈቱ መደረጉ ለግል ባንኮች ስጋት እንደሆነ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን የግል ባንኮች ብዙ ደንበኞቻቸውን እንዳጡም መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡
2005 ዓ.ም እነዚህን ዋና ዋና አነጋጋሪና አወዛጋቢ ጉዳዮችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ አዲሱ ዓመትስ? አብረን የምናየው ይሆናል፡

No comments:

Post a Comment