መሓሙድ ይባላል፤ ተወልዶ ያደገው ሐረር ነው። እድሜው 52 ሲሆን አሜሪካ መኖር ከጀመረ 30 አመት እንደሞላው ይናገራል። የ27 እና 23 አመት ወጣት ልጆች አሉት። የራሳቸውን ኑሮ ነው የሚኖሩት። በዲሲ ጎዳና አንድ ጥግ ስር ኩርምት እንዳለ ያገኘሁት መሓሙድ፣ ሁኔታውን በማየት አሳዛኝ ሕይወት ውስጥ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ከአንደበቱ የሚወጡት ቃላት አፍ ከማስከፈታቸው በተጨማሪ ጠለቅ ያለ መልክት ያዘሉ ናቸው። መሓሙድ ስለገጠመው ችግር እንዲህ አለኝ፤ «..ከወጣትነቴ ጀምሮ ከማውቃት፣ የቀዬ (ሐረር) ፍቅረኛዬ ጋር ነበር ወደ አሜሪካ የመጣነው። ከእርሷ በቀር ሌላ ሴት በጭራሽ አላውቅም። በፍቅር የአብሮነት ትዳር ዘመን ለሰላሳ አመታት ኖረናል። የነበረን ፍቅር በቃላት አይገለፅም!!» …አንገቱን አቀርቅሮ ለደቂቃዎች ዝም አለ፤ በሃዘን ስሜት ተውጦ ቀጠለ፥ «.. ከስድስት ወር በፊት ድንገት ታመመችና ሆስፒታል ገባች። በተኛች በሶስተኛው ቀን ጠዋት ሆስፒታል ስደርስ ዶክተሩ በጣም አዝኖ መሞትዋን ነገረኝ። የምናገረው ጠፋኝ፤ “ዶ/ር ልቋቋመው የማልችለውን ነገር ነው እየነገርከኝ ያለኸው፤ እባክህ ውሸት ነው በለኝ?..” ብዬ እግሩ ስር ወድቄ እየተንሰቀሰቅኩ ለመንኩት። …ግን የሚለውጥ ነገር አልነበረም። የ30 አመት ፍቅሬ በዛ መልኩ ጥላኝ ሄደች። አላህ የጀነት ሰው ይበላት።…» አለኝ። መሓሙድ ከዛ በኋላ ሕይወቱ እንደተቃወሰ ይናገራል። እንዲህም ይላል፥ « የምትወደውን ማጣት እጅግ ከባድ ነው። ዛሬ ብወድቅም እነሳለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ!! …የምትሞት እንኳ ከሆነ ከንፈርህን ጥረግ፤ ..ወደታች እንዳትወድቅ የምትሄድበትን መንገድ እወቅ።..» ..መሓሙድን ተሰናብቼው መንገዴን ስቀጥል.. “ውስጠ ወይራ” ቃላቱን እያሰላሰልኩ ነበር።
( መሓሙድ ይኸውላችሁ…)
( መሓሙድ ይኸውላችሁ…)
No comments:
Post a Comment