Wednesday, September 4, 2013

ውብሸት ታዬና የፖለቲካ አመራሩ ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ


በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በጽኑ እስራትና በገንዘብ የተቀጡት የአውራ አምባ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አንድነት ፓርቲ (መኢዴአፖ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔርና ሒሩት ክፍሌ፣ መንግሥት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ከዓመት በፊት ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፡፡ 

ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ሕግ ለማፈራረስ፣ በዜጎችና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚልና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ክሶችን በማቅረብ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት በ14 ዓመታት ጽኑ እስራትና በ33 ሺሕ ብር፣ አቶ ዘሪሁን በ18 ዓመታት ጽኑ እስራትና በ50 ሺሕ ብር፣ ሒሩት ክፍሌ ደግሞ ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ተቀጥታ በይቅርታ መውጣቷን በመጥቀስ በ19 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ የወንጀል ችሎት ከሁለት ዓመታት በፊት መወሰኑ ይታወሳል፡፡ 
ከቅጣት ውሳኔው በኋላ ሦስቱም ፍርደኞች በሠሩት ድርጊት መፀፀታቸውን በመግለጽ፣ ለፌዴራል የይቅርታ ቦርድ የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ደብዳቤው ከዓመት በላይ የቆየ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት ‹‹ይቅርታችሁ ተቀባይነት አላገኘም›› የሚል ምላሽ ፍርደኞቹ ባሉበት ማረሚያ ቤት ደርሷቸዋል፡፡ 
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ተዛውረዋል፡፡ ሒሩት ክፍሌ ግን በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ትገኛለች፡፡ 
እነ ጋዜጠኛ ውብሸት በተከሰሱበት ጉዳይ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና መምህርትና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙም ተከሰው በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ33 ሺሕ ብር መቀጣታቸው ይታወሳል፡፡ 
ጋዜጠኛ እስክንድርና ርዕዮት ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን፣ ርዕዮት የገንዘብ ቅጣቱ ባለበት ሲፀናባት የእስር ጊዜዋ ወደ አምስት ዓመት ዝቅ ተደርጐ ተወስኖባት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትገኛለች፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ግን ይግባኝ ያለ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤት ቅጣት ፀንቶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ይገኛል፡፡ እነ ውብሸት ይግባኝ ከማለት ይቅርታ መጠየቁ እንደሚያዋጣ በማመን ቢጠይቁም ከዓመት በኋላ ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡  
source: ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment