Sunday, October 27, 2013

የትርፍ ሰዓት ትግል


ኢዮብ ይስኃቅ
ከዕለታት አንድ ቀን ባልተለመደ ድፍረት የሙስና ኮሚሽን ሰይፉን ትላልቅ የወያኔ ባለሥልጣናት ላይ አሳረፈ። እንደመድኃኒት ብልቃጥ እዚህም እዚያም ተወሽቆ የነበረ ብርና ንብረት እያስቆጠረ ወንጀለኞቹን ዋስ እየከለከለ ወደ ወህኒ ወረወረ። ሚኒስትሮች ከቦታቸው ተፈናቀሉ፤ የሙስና እናት የሚለውን ሜዳሊያ ያጠለቀችው ወ/ሮ አዜብ ከኤፈርት ተባረረች። ያዲሳባ ከንቲባነትም ሱሚ ነው ተባለች። ከሁለት ብቻ ሳይሆን ከብዙ ያጣች ሆነች። ህዝቡ እልል ለማለት ቢፈልግም ወያኔን ስላላመነ መጨረሻውን ለማየት መጠባበቅ ያዘ።
 የተፈራው አልቀረም ጉዱ ቀስ በቀስ ይወጣ ጀመር። በትሩ አንደኛው ጠንካራ ሙሰኛ ሌላኛውን ደካማ ሙሰኛ የሚያስገብርበት ሂደት ነበር። ህወሓትን ሊጋፋ ይችላል ተብሎ የተጠበቀው በረከት ስምኦን ጉዋደኞቹን ካስበላ በኋላ ተደራድሮ ለሌላ ሥልጣን ታጨ። ምናልባት ትግርኛ መናገሩ ከአደገኛው ሰይፍ ሳይታደገው አልቀረም – ለዛሬ።
ሰሞኑን የተስፋዬ ገብረአብ እና የተመስገን ደሳለኝ ከቅርብ ምንጮች ተገኘ ተብሎ የተጻፈውን የኢህአዴግን መበላላት የሚያሳይ ጽሑፍ ሳነብ፤ በተጨማሪ የተገነዘብኩት ነገር እስሩና መጠላለፉ ለሀገሪቱ ጥቅም ሳይሆን የወያኔን የሥልጣን ግዜ ማራዘሚያ መሆኑን ነበር። በተለይ ተመስገን አቶ ስብሃት ነጋ “በውራይና” ጋዜጣ ላይ የፃፉትን ሲያስነብበን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በፍፁም ሥልጣኑን የማስረከብና ለኢትዮጵያም ምንም አይነት የሚጠቅም ራዕይ እንደሌለው ያረጋገጠ ነበር። ምናልባት ራዕይ እንኳን ቢኖራቸው፤ በሥልጣን ላይ እስከነድዳቸው የመቆየት ሊሆን ይችላል። መቆየታቸው ባልከፋ! ነገር ግን ለዚች ድሃ ሀገርና ህዝብ የሚጠቅም አንድም ፖሊሲ የመቅረፅ ሃሳብ የላቸውም። እያንዳንዱ ልማት ተብዬ ከጀርባ ለነሱ ሙስና የተጋለጠ ካልሆነ በስተቀር ለሀገር ተብሎ የሚወጣ ዕቅድ የለም። ለሰው ልጅ ምን ያህል ሀብት ይበቃዋል ብለን እስክንገረም ድረስ በአጥንቱ የቀረውን ህዝብ እየጋጡት ይገኛሉ።
የመገናኛ ብዙኀኖቻችን
ባለፉት ሃያ ዓመታት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ስንመለከት በአዲስ ዘመንና አጋር የመንግሥት ሚዲያዎች እንደሚነገረን የጥጋብ ሀገር አልሆነችም። ወይንም በዘመናዊው አዲስ ዘመን “ሪፖርተር” ጋዜጣም እንደሚቀርብልን የኢትዮጵያ ችግር የጠንካራ ተቃዋሚ መጥፋት ብቻ አይደለም። ስታትስቲክ ብቻውን ዜና አይደለም ብሎ በአሉ ግርማ እንዳለን፤ የተመደበውን በጀት ድምር፣ የሚሠሩ ልማቶች ወጪና የተገኘውን ብድር በደማቅ ርዕሶች መፃፍ ብቻውን ጥሩ ጋዜጣ አያሰኝም። በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ድህነት፣ በየትምህርት ቤቱ ለሁለትና ለሦስት ቀናት እህል ባፋቸው ሳያልፍ በየክፍላቸው የሚወድቁትን ህፃናትና በየቀኑ በልማት ስም የሚፈናቀሉትን ቤተሰቦች ዜና እንደግል ጋዜጣነቱ ሲያስነብበን አናይም። አልፎ አልፎ ተኝቶ ቤቱ ድረስ የሚቀርቡለትን ትኩስ መረጃዎች ለማጀብ ቀላል ትችቶችን በርዕሰ አንቀፁ ያቀርብልናል።
እንደአለመታደል ሆኖ በሌሎችም የግል ጋዜጦች የምናገኘው ዜና ጽንፈኝነትን የተሸከመ ከመሆኑም ሌላ መንግሥትን ከመሳደብ ውጪ በተቃዋሚ ጎራ ያለውን ችግር ግልፅልፅ አድርገው አያቀርቡም። እየተሳደደም ቢሆን ሁሉንም በአንድ ሚዛን የሚያስቀምጠው አንድ ለናቱ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ ብቻ ነው።
በሀገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ
በርግጥም ወደ ተቃዋሚ ጎራ ስንመጣ ቀላል የማይባል ችግር አለ። በመጀመሪያ ባገር ውስጥ ያሉትን ስንመለከት አብይ ችግር ሆኖ የምናገኘው ሥልጣንን ሙጭጭ የማለት ጉዳይ ነው። የሊቀመንበርነቱን ቦታ አስረከቡ ሲባል አረፍ ብለው ይመለሱበታል። በዚህ ሃያ ዓመት ውስጥ የትኛውም አንጋፋ ፓርቲ በአዲስ ወጣት መሪ ተተክቶ አላየንም። ተተካካን ያሉትም በአጋፋሪነት ከኋላ በምክትልነት ያስከተሉዋቸውን ሰዎች ነው። እነዚህ ሰዎች እንደአስፈላጊነቱ ቦታውን ሊለቁ የሚችሉ ታማኝ ሰዎች ናቸው። በተቃዋሚነት ዘመኑ ዲሞክራሲን ያላለማመደን መሪ በአጋጣሚ የመንግሥት ሥልጣን ቢረከብ እንዴት አይነት አምባገነን እንደሚሆን ለመገመት ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም። ለጠንቋዩ የታሰበውን እራሳችን እየበላን እራሳችን እንገምታለን።
 ስደተኛው ተቃዋሚ
ወደውጪው ተቃዋሚ ስንመጣ ሰሞኑን “ሰላቢ ፀሐፊዎች” በሚል በተስፋዬ ገብረአብ የቀረበውን ጽሑፍ በማስታወስ ነው። ተስፋዬ ይህን ያለው በብዕር ስም ጎርፍ የሚለቁትን ፀሐፊዎች ለመንካት ነው። እኛ ደግሞ ሰላቢ ፖለቲከኞች እንላለን – ቁርጠኝነት ጎሎዋቸው የሌላውን የትግል ስሜት ይሰልባሉና። በትክክል የምንስማማበት አንድ ነጥብ አለ። ይኸውም ኢትዮጵያ ፋታ በማይሰጥ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች። ይህ ማለት ማቄን ጨርቄን ሳንል የምናምንበትን ወይም የምንሰብከውን ትግል መከተል ይሆናል። ወድድንም ጠላንም የዛሬዎቹ መሪዎች በረሃ በገቡበት ወቅት ወጣትነታቸውን ጨምሮ ብዙ ጥቅሞቻቸውን መስዋዕት አድርገው ነው።
ለምሳሌ መለስን እና ኢሳያስ አፈወርቂን ብንወስድ፤ አንዳቸው የተከበረ ዶክተር፣ ሌላኛቸው ደግሞ ኢንጅነር የመሆን ተስፋ የነበራቸው ወጣቶች ነበሩ። በሀብትም ቢሆን ደጃዝማች አባቶቻቸው መሶባቸው ሙሉ፣ ጎተራቸው ካመት ዓመት የማይጎድል ባላባቶች ነበሩ። ጥሩ ኑሯቸውንና የነገ ትልቅ ሰው የመሆን ዕድላቸውን በሳጥን ቆልፈውበት ነው ወደ በረሃ የገቡት። አይ! አሸንፈው መሪ ለመሆን ነው የሚል የዋህ ያለ አይመስለኝም። ኃይለሥላሴም ሆኑ ደርግ ይወድቃሉ ብሎ እንኳን ሰዉ እግዜሩም እርግጠኛ የነበረ አይመስለኝም። የራሱን ጀግኖች እየበላ መንገዱን ጠርጎ ያስገባቸው ወደድንም ጠላንም ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ነው።
ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ የዛሬዎቹ ተቃዋሚዎች በተለይ ደግሞ ብቸኛው አማራጭ የትጥቅ ትግል ነው የሚሉት፣ እንኳን ሕይወታቸውን፣ ደሞዛቸውን ሲሰዉ አናይም። ኢትዮጵያ ያለችበት ችግር አጣዳፊና ግዜ እንደማይሰጥ ከተስማማን ፈጣን እርምጃ መወሰድ ነበረበት። ከዚህ ይልቅ መግለጫዎችን በመስጠቱ ላይና ገቢ ማሰባሰቡ ላይ በርትተው ሲንቀሳቀሱ እያየን ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በድል ማግስት አዲስ አበባ የሚያስገባ ካርድ በገንዘብ የሚታደልበት ዝግጅት ተደርጎ ነበር – በግንቦት ሰባት። በዚህ አጭር ጊዜ ወያኔ ወድቆ አዲስ አበባ ይያዛል የሚል የየዋህ ግምት ባይኖረኝም በኢትዮጵያ ተራሮችና ጫካዎች ውስጥ እየተሽሎከለከ ወያኔን የሚያሸብር ታጋይ መጠበቄ አልቀረም። በኢንተርኔት መስኮቶች ወዛቸው ግጥም ያለ ባለስካርፍ ታጋዮችን ተመልክተናል። ግን የዋሉበትን የትግል አውድማ በስህተት እንኳን ሰምተን ወይንም አይተን አናውቅም።
አንድ እየተሠራ ያለ ነገር ቢኖር ይሔ እንደጉድ ድህነትንና ግፍን እየሸሸ በረሃና ባህር የሚበላው ወጣትና ወደ ዐረብ ሀገር የሚሰደዱ እህቶች ምርጫቸው ሽሽት ሳይሆን የችግሮቻቸው ምንጭ የሆነውን መንግሥት ለመጣል ትግሉን መቀላቀል ነበር። ይህ መሆኑ ቀርቶ ግን በኢትዮጵያ ጫካዎች ልናያቸው የሚገቡ ወታደራዊ ልብሶች እንደእንቁጣጣሽ ቀሚስ እነታማኝ በየነን በፈንድሻ ለመቀበል በየስደቱ መድረክ ላይ ሲጌጥባቸው እናያለን።
 ኢትዮጵያን ከህወሓት ጥፋት ለማዳን ያለን ምርጫ
ሀገራችን በህወሓት መራሹ መንግሥት እጅ ከቆየች ያለማጋነን በሚቀጥሉት ዓመታት ዛሬ ያለችበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እንደማይኖራት ማወቅ አለብን። ህዝቡም በዘርና በኃይማኖት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚበላላባት ምድር ትሆናለች። ስለዚህም የትርፍ ጊዜ (part time) ትግል ለዚች ሀገር እንደማይመጥን አውቀን የመረጥነውን የትግል መስመር በቁርጠኝነት መቀጠል አለብን። በሰላማዊ ከሆነ በሰላማዊ፣ በትጥቅ ትግል ከሆነ በቦታው እታች ወርዶ መታገል ያስፈልጋል። ይህ ካለሆነ ግን የቁርጠኛ ልጆችን መንገድ በመሪነት ስም በመዝጋት በእጅ አዙር የወያኔ መንግሥት ዕድሜ እንዲራዘም ማገዝ አይገባም።

ትንሽ መልዕክት ለተስፍሽ (ተስፋዬ) ገብረአብ
በመጨረሻ ከላይ ስሙን ለጠቀስኩት ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ የምለው አንድ ወንድማዊ ምክር አለ። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አሁን በቅርብ ደግሞ ለላይፍ መጽሔት በሰጠው ቃለመጠይቅ ስለኤርትራ ለምን እንደማይፅፍ ተጠይቆ “ሰዎች የማላውቀውን እንድጽፍ ለምን ይጠብቃሉ” የሚል መልስ ሰጥቷል። ወይንም በሚቀጥለው መጽሐፉ በአንዲት ምዕራፍ እንደሚያወጋን ተናግሯል። እኔ ግን የቡርቃ ዝምታን የሚያክል መጽሐፍ ለመጻፍ አርባጉጉ ወይ በደኖ ካሳለፈው ጊዜ የበለጠ በኤርትራ ቆይቶዋል የሚል ግምት አለኝ። በእናቱ ኤርትራዊ ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ የኤርትራዊያንን ሕይወትና ኑሮ ከሌላው ሰው በተሻለ የማወቅ ዕድሉ አለው። ለአንድ አይደለም ለዕድሜ ልኩ የሚበቃ መጽሐፍ የሚወጣው ግፍ በኤርትራ ምድር እየተፈጸመ ነው። ተስፍሽ ደራሲ ድንበር እንደማይወስነው ላንተ መንገር የለብኝ። ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለህ ማመንህም ቢሆን ስለጎረቤት ሀገር ህዝብ መበደል ስለመጻፍ ሊገታህ አይገባም። ብዕርህ ስለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ስለመላው አፍሪካ ህዝብ መዘመር ይገባታል።
ይህቺን ትንሽ ጽሑፍ ከጫርኩ በኋላ በኢንተርኔት የተለቀቀውን “የስደተኛው ማስታወሻ” አነበብኩ። ሌላ ጊዜ በሰፊው ብመለስበትም አሁን ተስፋዬን አንድ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ። አሁን ማን ይሙት ከአስመራ ተነስተህ እስከ ናቅፋ ተራራ በደራሲ ዓይን የታዘብከው አስፋልት የሚያቁዋርጡ የደረቁ ወንዞችን ብቻ ነው? አለምክንያት በየድንጋዩ ስር ውሃ እንዳጣ ዛፍ የጠወለጉ ወጣቶችን አላየህም? ወይንስ ያንተን መምጣት አስመለክቶ እንዳታያቸው ደብቀዋቸው ነው? ብዕርህ ደፋርና ግልፅ ናት ብዬ አስብ ነበር፤ ግን የዘር ልጉዋም ሳያደናቅፋት አልቀርም።
እኔ ጨርሼአለሁ።
ነፃነትና ሰላም ለመላው አፍሪካ ህዝብ!

ኢዮብ ይስኃቅ
eyobisack@yahoo.it  

ወ/ሮ አዜብ መስፍን Azeb Mesfin

No comments:

Post a Comment