ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያና ኬንያ በግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሀይል ማመንጫ ግድብ ላይ ያላቸውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ሁለቱንም ሀገራት በማግባባት ላይ እንደሆኑ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ያለችው የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቅርብ የሚገኘውን የኬንያን ቱርካና ሀይቅ ይጎዳል በሚል የኬንያ መንግስት የአካባቢ ተቆርቋሪ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
የኦሞ ወንዝ ለቱርካና ሀይቅ ብቸኛ የውሃ ምንጭ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ሁለቱ ሀገራት በሀይቁ ዙሪያ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ በመጠበቅና በማስተዳደር ዙሪያ ላይ ስምምነት እንዲያደርጉ እያግባባ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ የውሃ ሀብት ሚኒስቴሮች በሚቀጥለው ወር ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የቱርካና ሀይቅ ይጎዳል ብለው ስጋታቸውን ሲገልጹ የቆዩ አካላት ስምምነቱ ሀይቁን ለመታደግ ይጠቅማል ብለው በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ከ80 በመቶ በላይ የቱርካና ሀይቅ ውሃን የሚያገኘው ከኦሞ ወንዝ በመሆኑ በኢትዮጵያ የሚገነባው የሀይል ማመንጫ ሀይቁን ያደርቀዋል ሲል የኬንያ መንግስት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ የመስኖ ልማትን የምታካሂድ ከሆነ ደግሞ የቱርካና ሀይቅ ትልቅ አደጋን ያጋጥመዋል ተብሎ ተፈርቷል፡፡
በርካታ ሰዎች በሀይቁ አሳን በማስረግ ህይወታቸውን እንደሚያስተዳድሩ ይነገራል፡፡
ኦክስፋም የተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት ለሀይል ማመንጫነት ታስቦ የነበረው ግድብ ለመስኖ ልማት እንዲውል በኢትዮጵያ በኩል መታቀዱ የቱርካናን ሀይቅ የውሃ ሀብት የሚጎዳ ከመሆኑ በላይ የበርካታ ሰዎች የአኗኗር ሁኔታ ይጎዳል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በቱርካና ሀይቅ ላይ ህይወታቸው በቀጥታ ተያይዞ ከሚገኘው 20 ሺ ኬንያውያን በተጨማሪ ከ200 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን በሚያጋጥም የውሃ እጥረት ተጎጂ ይሆናሉ ተብሎ ተፈርቷል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቶች በርካታ ሰዎችን ከኦሞ ወንዝ ዙሪያ በማፈናቀል 300 ሺ ሄክታር መሬትን ለስኳርና ጥጥ ልማት እርሻ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጎ ይገኛል በማለት ይገልጻሉ፡፡
ESAT
No comments:
Post a Comment