Sunday, November 18, 2012

መሪውን ባጣበት ወቅት የሕዝቡን የልብ ትርታ ለማለዘብ የቤት ልማት አጀንዳ


ሰሎሞን ተሰማ
በዘመነ ትምክህተኞችና ጠባቦች አንድ ቁስለኛ ሰው ነበረ። ይህ፣ በአድኃሪነት የተወጠረ የመሬትና የቤት ከበርቴ ድንገት ጋሬጣ ወግቶት ቅልጥሙ ቆሰለ። ያንንም ቁስል ንቆት ኖሮ፣ እያደር እያመረቀዘ ሄደና ደህና የዝንብ መሰብሰቢያ ቤት ወጣው። መጀመሪያ ላይ ንፍፊቱ፣ ቀጥሎ ግን መገረኑ ሰውዬውን አላስኬድ አላራምድ አለው። በየት በኩል ይላወስ። እግር ተወርች አሳሰረው። እቤቱ ዋለ። ዝንቡን እሽሽ ሲል ለመዋልም ተገደደ። የኋላ ኋላ ግን፣ ዝንቦቹን እሽሽ ማለቱንም ተወው።
የሰውዬውን እቤቱ መዋል የሰማ አንድ የጥንት ወዳጁ ሊጠይቀው መጣ። የሰውዬውን ቁስል የወረሩትን ዝንቦችም አይቶ፣ የቁስላሙን ስምምነት ሳይጠይቅ ዝንቦቹን አባረራቸው። ቁስለኛው ተቆጣ። ግስላ ሆነ። በጠያቂው ሰው በጣም ተናደደበት። ጠያቂውም ሁኔታው ገርሞት፣ “ምነው ወዳጄ ሆይ፣ ዝንብህን ባባረርኩልህ እንዲህ ነደደህ!” ሲል በቅሬታ ጠየቀው። ቁስለኛውም ሰውዬ ቅሬታውን በሚያሳብቅ አኳኋን መለሰለት። “ሰማህ ወይ ወዳጄ! የምሬን እኮ ነው የተናደድኩብህ። ለምን መሰለህ” አለው። “ለምን መሰለህ፤ ዝንቦቹን ከማባረርህ በፊት እነዚህ የጠገቡት ሄደው የራባቸው/ያልጠገቡት ዝንቦች እንደሚመጡ መገመት ነበረብህ!” አለው።
ኦሮሚኛ፣ የማይጠግቡትን ጉዶች ሁሉ በአንድ ቃል ይገልጻቸዋል። “ኢንቁፍቱ”ዎች ይላቸዋል። በአማርኛም “የማይጠግብ፤ ከርሳም፤ ሆዳም፤ አጋብሴ፤ እንብርት የሌለውም” እንደማለት ነው። ኢንቁፍቱ – ቅጥየለሽ ስግብግብነትንና ዋጤነትንም ያካትታል። “ውጦ ሰልቅጦ ጭጭ!” የሆነውን ጉድ ሁሉ – ኢንቁፍቱ ነው ይለዋል – ኦሮሚኛ። ለዚህም ነው፣ የዛሬውን ጽሑፍም ርዕስ “ኢንቁፍቱ ዝንቦች” ያልነው። ያልጠገቡት ወይም የማይጠግቡት ዝንቦች ቁስለኛውን ምን ያህል ሊያሳምሙት እንደሚችሉ፣ ልብ ያለው ልብ ይለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ወቅትን አስታከው ግርር… የሚሉ በርካታ “ኢንቁፍቱ ዝንቦች” የቤት ልማቱ ሥራ ተገን አድርገው ሲሯሯጡ በሦስቱም ሥርዓቶች ታይተዋል። ለምን የቤት ልማትን ጉዳይ ከምርጫ ጋር እንደሚያያይዙትም ይህ ጽሑፍ በዋናነት ይጠይቃል። በተለይም ደግሞ ሦስቱን ሥርዓቶች የቤት ልማት ጉዳይ ለምን የምርጫ ወቅትን አስታከው እንደሚያራግቡት መረጃ ለመስጠት ይተጋል። አርእስተ ጉዳዩንም ለማብራራት የግማሽ ክፍለ ዘመን የናሙና ቅኝት ያደርጋል። እያወሳነው ያለነው ቢያንስ ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ስላለው የከተማ ነዋሪዎች ችግር ነው። የቤት ችግር! የከፋና የበረታ ችግር ነው። ሦስቱም ሥርዓቶች ያደረጓቸው ምርጫዎች ዋዜማ ላይ የቤት ልማት ጉዳይ እንዴት ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውል እንመለከታለን። ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችንም ለመጠቋቆም ጥረት እናደርጋለን።
ከላይ እንደጠቆምነው፣ የቤት ልማትን በተመለከተ ሦስቱንም ሥርዓቶች የሚያመሳስላቸው ሦስት ነጥቦች አሉ። አንደኛ፣ ሦስቱም የቤት ልማትን በምርጫ ዋዜማ ላይ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛና ለድጋፍ ማሰባሰቢያነት ነው የሚጠቀሙበት። ሁለተኛውም ነጥብ፣ ሦስቱም ሥርዓቶች ምርጫን የሚጠቀሙት የከፋ ተቃውሞዎች ከተማሪዎች፣ “ከወንበዴዎች”፣ እና “ከአክራሪዎች” በኩል ሲገጥማቸው ነው። በመጨረሻም፣ የቤትን ልማት ጉዳይ የሚያራግቡት በገዢው ቡድን/ አስተዳደር አካባቢ የመከፋፈል አደጋዎች ሲያጋጥሙ ነው። ሦስቱም ነጥቦች በጣም ጥቅልና አሻሚም ስለሆኑ እንደሚከተለው ለማብራራት እንጥራለን።
በመጀመሪያ፣ ሦስቱም የቤት ልማቱን በምርጫ ዋዜማ ላይ እንዴት ለፖለቲካ ትርፍ ሊያውሉት እንደሞከሩ ማስረጃችንን እናቀርባለን። በቅድሚያ ግን፣ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ፣ አራተኛውን “የሕግ መምሪያ ም/ቤት እንደራሴዎች ምርጫ”ና የቤት ልማት ጉዳይን እንመልከት። ምርጫው በ1961 ዓ.ም በሰኔ 16 ቀን ሲጀምር ሰኔ 25 ቀን 1661 ዓ.ም ነበር የተጠናቀቀው። በምርጫው ዋዜማ ታዲያ፣ በሥራ ሚኒስቴር (የአሁኑን የሥራና ከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን ሚ/ር እንደማለት ነው) “የሕዝብ የመኖሪያ ቤት ሥራ ድርጅት” አቋቁሞ ነበር። በሥራ ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ክቡር ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ ስለድርጅቱ እንዲህ የሚል መግለጫ በጥቅምት 3 ቀን 1961 ዓ.ም ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ሪፖርተር ሰጥተው ነበር።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዲህ አሉ፤ “የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ባደገ መጠን፣ ሕዝቡ በጥሩ ቤት ውስጥ መኖርን ይመርጣል። በአሁኑ ጊዜ (በ1961) ታዲያ በሀገራችን የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለ በግልጽ የታወቃል። ትክክለኛ ስታትስቲክስ አይኑረን እንጂ፣ በከተሞች ውስጥ በራሱ ቤት ከሚኖረው ሕዝብ ይልቅ በግለሰብ ኪራይ ቤት የሚኖረው ሕዝብ ብዛት እንዳለው አይካድም። ስለዚህም፣ በሀገራችን የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለማቃለል ሲል መንግሥት በሥራ ሚኒስቴር ሥር የሕዝብ መኖሪያ ቤቶችን ሥራ መሥሪያ ቤት እንዲቋም አድርጓል፤” ብለዋል። (ሚኒስትር ዴኤታው፣ “የሕዝብ መኖሪያ ቤቶችን ሥራ መሥሪያ ቤት” ያሉት ድርጅት አሁን የቤቶች ኤጀንሲ የሚለው ሞክሼ መኆኑን ልብ ይሏል።) ሚኒስትሩ ቀጥለው የተናገሩት ነው ፍሬ ነገሩ። “ድርጅቱ የተቋቋመው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነው። በዚህም አጭር ጊዜ ውስጥ “ያከናወነው ሥራ በጉልህ ባይታይም” ወደፊት ሊያከናውነው የሚገባውን የሥራ ዘመቻ/ንድፍ አዘጋጅቷል።” ይሄው ነው። ምርጫው ሰኔ 1961 ዓ.ም ሊካሄድ፣ በወርሃ ጥቅምት 1961 ላይ መጥቶ፣ አይንን በጨው ታጥቦ፣ “ያከናወነው ሥራ በጉልህ….” ችግር ፈቺ ነው፤ ማለት የተለመደ ነው። የሕዝቡን ኩርፊያና የሕዝቡን ሮሮ በሾኬ ለማንከረባበት የሚዘየድ ብልጠትም ይሏችኋል ይሄው ነው።
በዘመነ ደርግ የተደረገውን መራወጥማ ማንም አይስተካከለውም። ጓድ መንግስቱ በጠፍ ጨረቃ ተነስተው አስራ ሁለት አመት ሙሉ በስልጣን ያቆናጠጣቸውን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግንና ፒ.ሲ.አይ ያለበሳቸውን ኢሠፓን ለከርሞ ላይህም አልፈልግ አሉ። ወዲያውም የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽናቻን በጥቅምት አቋቁመው ሕዝቡን ናና ተወያይ አሉት። ሕዝቡም ለጥሪው ደንታ ዲስ መሆኑን የተገነዘቡት ጓድ ሊ/ር መንግሥቱ፣ ለከተሜው የቤት መስሪያ ቦታ በነፃ ማደል ጀመሩ (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 9 ቀን 1979 ዓ.ም)። የልማት ባንክም ለቤት ሰሪዎች 183,654,000 ብር አበደረ (አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 3 ቀን 1979 ዓ.ም፤ ገጽ 1)። የሚገርመው፣ ሕገ መንግሥቱ በሕዝቡ ተሳትፎ በየካቲት 1979 ዓ.ም ፀደቀ አሉንና በሚያዝያ 14 ቀን 979 ዓ. ምህረትም በዓዋጅ ቁጥር 314/1979 “ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን” የሚባል ድርጅት ተቋቋመ (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 15 ቀን 1979፤ ገጽ 1)። ለብሔራዊ ሸንጎም ዕጩዎች ከሚያዝያ 18-25 ቀን 1979 ዓ.ም ተመዘገቡ ተባለና፣ በግንቦት አንድ ቀን 1979 ዓ.ም የዕጩዎቹ የስም ዝርዝር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ወጣ። በግንቦት 23 ቀን 1979 ዓ. ምህረትም የዕጩዎቹን ዝርዝር ብሔራዊው የምርጫ ኮሚሽን አፀደቀ ተባለ። አስራ አምስት ቀን እንኳን ሳይሞላቸው ሰኔ 6 ቀን 1979 ዓ.ም እንዳሉ ተመርጠው፣ ጳግሜ 5 ቀን 1979 ዓ.ም ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የኢ.ሕ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሆኑ ተባልን (አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 6፣ ሰኔ 25 ቀንና ጳግሜ 6 ቀን 1979 እትም ይመልከቱ)።
“ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” ብሎ ሲፎክር የነበረው ወታደራዊ ጁንታ፣ ከመስከረም 1979 ዓ.ም ወርሃ ጥቅምት ጀምሮ መሬት ተመርተው ቤት ለሚሰሩ ከሁለት መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር እስከ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ድረስ በገፍ ሠጠ። እንደውነቱ ከሆነ፣ በበርካታ ከተሞች ውስጥ በተለምዶ “አዲስ ሠፈር” እና “ቦሌ” የሚባሉ መንደሮች በአዲስ አበባ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በግራዋ፣ በጂማ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በደሴና በሌሎችም ከተሞች እንደአሸን ፈሉ። ብዙዎቹ መንደሮች አሁንም ድረስ በዚሁ መጠሪያቸው ይገኛሉ።
በዘመነ ኢሕአዲግም ቢሆን የቤት ጉዳይ ምርጫን ተከትሎ የሚውለበለብ አጀንዳ ነው። አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 1997 ዓ.ም፣ (ያን ጊዜ-ከንቲባ) የአቶ አርከበ እቁባይን ፎቶ በፊት ለፊት ገጹ ይዞ ወጣ። የከንቲባው ንግግር በጥድፊያ የተሞላ ነበር። “በቤቶች ልማት ግንባታ ምክንያት ለሚነሱ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን አስተዳደራቸው እንደሚያደርግና፤ የአዲስ አበባን አስተዳደር ቤት የተከራዩ ነዋሪዎች ቤቶቹን ለመግዛት የሚያስችላች መመሪያ መውጣቱን” ገለጹ ይላል። የከንቲባው ሩጫ በዚህም አላቆመም። በሚያዝያ 13 ቀን 1979ዓ.ም በቦሌ ገርጂ አካባቢ የተሠሩትን 673 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ማስመረቅና ለባለቤቶቹ ለማስረከብ ተጣደፉ። ይሕም፣ አስተዳደራቸው ለመሥራትና ለማስረከብ ካቀደው 40ሺ ቤቶች ውስጥ 0.0168% (በመቶ) ያህል ብቻ ነበር የተሳካለት። ስለዚህም፣ ከሚያዝያ 15 ቀን 1997ዓ.ም ጀምሮ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ተደርጎ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 420ሺ ቤት ፈላጊዎች ተመዘገቡ (አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 25 ቀን 1997ዓ.ም)። ሁኔታው የኢሕአዴግን መሪዎችን ምን ያህል ግራ አጋብቷቸው እንደነበር በወቅቱ ኢቲቪን ያየ ሁሉ ያስታውሰዋል።
ወደሁለተኛው ነጥብ እንለፍ። ከ1959 መጋቢት ወር ጀምሮ የዩኒቨርሲቲና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አመጽ ተባብሶ በመቀጠሉ ሰበብ፣ መንግሥት በወላጆቻቸው አማካይነት ልጆቹን በተጽዕኖ ሥር ለማዋልም ከዘየዳቸው መላዎች አንዱ፣ “ወላጆችን የቤት ባለቤት አደርጋችኋለሁ፤” የሚል ነበር። ያም ሆኖ፣ ልጆቹ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን ከመደብደብ፣ የአንበሳ አውቶቡሶችን ከመሰባበርና ከማቃጠል፣ ከፖሊስ ጋር ከመጋጨትም አልፈው ተርፈው የሀገር ውስጥ በረራ የሚያደርጉ ሁለት አይሮፕላኖችን ጠልፈው ካርቱም ለማሳረፍ ቻሉ። መንግስትም፣ ወላጆችን መተለያዩ ዘዴዎች ልጆቻቸውን እንዲገስጹ ጫና ማሳደሩን ገፋበት። የወላጆች ቀንን አስመልክተውና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ሳይቀሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለው ለመሸለም፣ ንጉሠ ነገሥቱ በየትምህርት ቤቱ ለመሄድ ተገደዱ። ታዋቂ ግለሰቦችን፣ እነአበበ ቢቂላንና እነማሞ ወልዴን ትምህርት ቤቶች አካባቢ የስፖርት አምባሳደር አድርገው ታዳጊዎቹን እንዲያነቃቁም አዘዙ። ሆኖም፣ ውጤቱ አዎንታዊ መሆን አልቻለም (አዲስ ዘመን፣ ኅዳር 8 ቀን 1961ዓ.ም)።
ደርግም በዚህ የቤት ልማት ልግስናው ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ሞክሯል። “ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር” ብሎ፣ “በተገንጣይ ወንበዴዎች” ላይ ለከፈተው ቅስቀሳ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አድርጎ ተጠቀመበት። ከሁሉም በላይ፣ የሶቪየት ሕብረትና የሶሻሊስቱ ጎራ የእርዳታ እጁን ማሳጠር ጀምሮ ስለነበር፣ ከሀገር ውስጥ የመሬት ምሪትና የመሬት ገቢ ግብር በመሰብሰብ የአገዛዙን እድሜ ለማስረዘምም አቅዶ ነበር። በተለይም በኤርትራና በትግራይ እነዲሁም በወለጋና በሐረርጌ አካባቢዎች ተነሡብኝ ያላቸውን “ተገንጣዮችና ወንበዴዎች” በሕዝቡ ርብርብ ለመመከት፣ የቤት ልማት እቅዱን ነድፎ ይንቀሳቀስ ነበር። አራት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ “የነበረው ሁሉ እንዳልነበረ!” ሆነበት እንጂ።
በ1997 ዓ.ምህረትም ሆነ አሁን በ2004 ዓ.ም. የኢሕአዲግ መንግሥት “አክራሪ” ያላቸው የቅንጅት መሪዎችና የሙስሉም መሪዎች እንቅስቃሴ ሲፋፋምበት፣ ከቤት ልማት ጋር የተያያዘ አጀንዳ ቀርጾ መሯሯጥ ይዟል። ይኼውም በዋናነት፣ 40-60 (አርባ-ስልሳ) የተባለው የቤት ልማት ፕሮጀክት/ዕቅድ ነው። መጀመሪያ መናፈስ የጀመረው ከሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ሥርዓቱ፣ የቤት እንሰራለን ቅስቀሳውን፣ በስራና ከተማ ልማት ሚንስትሩ በኩል ለአራት ሳምንታት ያህል ቀጥሎት ነበር። በመሐል በሀዘኑ ምክንያት ጋብ ብሎ ሰነበተና እንደገና ከመስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮም ተጧጡፎ ቀጠለ። በሁለተኛም ደረጃ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና የክፍለ-ከተማዎቹ ተወካዮች ሰማኒያ አምስት ሺ (85,000) የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚንየም) ስራችንን በይፋ ጀመርን የሚል ዘገባ ለአምስት ሳምንታት ያህል አጡዘውት ነበር። በተለይም የመጅለሱ ምርጫ በመስኪዶች ካልሆነ “ዋ!” እያሉ ያስፈራሩትን “አክራሪዎች” (በመንግሥት ቋንቋ ነው) ጆሮ ለማሳጣት የቤት ልማት ጉዳይ ፍቱን መድኃነት ሆኖ ተገኝቷል።
ወደሦስተኛው ነጥብ እንለፍ። እንደሚታወቀው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ውስጥ በወጣቶቹ ቢሮክራቶችና በነባሮቹ የመሬት ከበርቴዎች መካከል ምናልባትም ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ መከፋፈል ተከስቶ ነበር። በተለይም፣ ክፍፍሉ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤትና በዘውድ አማካሪዎች ምክር ቤት መካከል ተከሰቷል። ንጉሠ ነገሥቱም በጠቅላይ ግዛቶች፣ በሚኒስትር መስሪያቤቶች፣ በክፍለ ጦሮችና በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሹም ሽር ጀምረው ነበር። ያንንም ውስጣዊ ሕመም በዋግምት ለማገም ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሉሉ ሀብተወልድ ጠ/ሚኒስትር ተብለው ካቢኔያቸውን ያዋቀሩት በታኅሳስ 1959 ዓ.ም. ነበር። እንደምንም ተብሎ የጥገና ለውጡ መሬት ሊያዝ ሞከረ። ብቻ ምን ያደርጋል …!
በደርግም ዘመን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ ኮሚሽነሮች፣ አርቲስቶችና እግርኳስ ተጫዋቾች አገር መክዳት የጀመሩት በ1978 መጨረሻ አንስቶ ነበር። ደርግ የጄራሎቹን ማዕረግ በመቀስ መቁረጥ፣ “ቂጣቸውንም” በሳንጃ መውጋት ጀምሮ ነበር። ተጠቃሽ የሆኑትን እናውሳ። ብ/ር ጄኔራል ታሪኩ ላይኔ በአደባባይ ማዕረጉን ተገፈፈ። የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዳዊት ወ/ጊዮርጊም ወጥተው ቀሩ። ከያኒዎቹ ተስፋዬ ለማና ኃይማኖት አለሙም ለሕዝብ ለሕዝብ ዝግጅት ሄደው ቀሩ። የእግር ኳስ ተጫዋቾቹም ቢሆኑ ግብጽና ቱኒዚያ ወይም አልጄሪያ ሄደው ከዱ። ጫናው በአመራር ላይ ላሉት ሰዎች ግልጽ ነው። ስለዚህም፣ ቤትን እንዲያለሙ ማድረግ ሰዎቹን ከክህደት ስሜት በመጠኑም ቢሆን ያስቀራቸዋል ተብሎ ታሰቦ ነበር የደርግ ቸርነት የታየው። ከደርግ የሦስት ብር ቤት ወራሽነት አንጻር ነው፣ “የደርግ ቸርነት ታየ” የምንለው።
በዘመነ ኢሕአዴግ ያለውን ሁኔታም እስቲ እናጢነው። ኢሕአዲግ በበርካታ ነውጦች ውስጥ ሳለ ነበር የ1997ቱ ምርጫም ሆነ የአሁኑ 40-60 የቤት ልማት ጉዳይ የመጣው። ከ1993 ሰኔ ወር ጀምሮ አንጋፋ አመራሮቹን “አንጃ” ናችሁ ብሎ አባረረ። ገሚሱንም በሙስና ወነጀሎ ሸቤ ከተታቸው። ያልታሰሩት ታዲያ እስከ 1997 ድረስ አድፍጠው ጠበቁት። በ97ም እልሀቸውን ሊወጡ የፓርቲነት ምዝገባ አደረጉ። ክፍፍሉ በርካቶችን በ1998 ዓ.ም. በድጋሚ በግምገማ አሰናበተ። አሁንም (በ2004 እና በ2005) ኢሕአዴግ በውስጣዊ ነውጥ ውስጥ እንዳለ ይነገራል። ኧረ እንዲያውም ሊሠነጠቅም ይችላል የሚሉ ወገኖች አጋጥመውናል። በዚህ እንደዐይኑ ብሌን የሚያየውን መሪውን ባጣበት ወቅት ደግሞ፣ የሕዝቡን የልብ ትርታ ለማለዘብ የቤት ልማት አጀንዳ ቀርጾ ቢንቀሳቀስ ምን ያስደንቃል? (የሳምንት ሰዎች ይበለን!)
 posted by Gheremew Araghaw

No comments:

Post a Comment