Saturday, November 24, 2012

በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ እየጨመረ ነው ተባለ



ህዳር ፲፭ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መንግስት ሙስሊሙ ላነሳው ጥያቄ ተገቢውንና ሰላማዊ የሆነ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የሀይል አማራጭ መጠቀሙ፣ በሙስሊሙ ላይ የሚደርሰው በደል እየከፋ እንዲሄድ አድርጎታል።
የአካባቢው ነዋሪዋች እንደተናገሩት  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ከምሴ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቤት ለቤት በመግባት ከ60 በላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን በመያዝ አስረዋል።
በተያዙት ወጣቶች ላይ የሚደርሰው እንግልት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ቀያቸውን ለቀው ወደ ጂቡቲና ሱዳን ተሰደዋል።
ከደጋንና ከሀርቡ አካባቢዎች ተነስተው ሱዳን ድንበርን እያቋረጡ የነበሩ ሙስሊሞች ለኢሳት በመደወል “    እኛ በአገራችን በነጻነት መኖር ስላልቻልን በመንገድ ስንጓዝ ጅብ ይብላን ብለን ጥለን እየሄድን ነው። የሱዳንንና የኢትዮጵያን ድንበር እያቋረጥን ነው፣ እንግዲህ አገራችንን አደራ፣ ሱዳን በሰላም ከገባን ድምጻችንን ታሰሙልናላችሁ፣ ያለበለዚያ ግን መንገድ ላይ ከተያዝን እንደማስረጃ አድርገው ስለሚያቀርቡብን መልእክታችንን ብቻ አቅርቡልን ” በማለት ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በትናንትናው እለት  በኢሊባቦር ዞን በመቱ ከተማ ከ400 በላይ ሙስሊሞች  የተቃውሞ ድምጽ ማሰማታቸውን ተከትሎ እስከ ምሽቱ 10 ሰአት ታግተው ውለዋል።
የተወሰኑ ሙስሊሞችን ለማሰር ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ፣ ህዝቡ ባሰማው ተቃውሞ ወዲያውኑ ሊፈቱ ችለዋል።
የአሜሪካን መንግስት ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች መንግስት የሙስሊሞችን ጥያቄ ለመፍታት እየተከተለ ያለው መንገድ ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ይፈጥራል በማለት እያስጠነቀቀ ነው።

No comments:

Post a Comment