በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሲገኝ መንግስት በ1997 ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንዲከፍል የሚጠይቀው ክስ እንደሚከፈት ስዊድናዊው የህግ ባለሙያ አስታወቁ
ነሃሴ ፳፱(ሃያዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም :-በ1997 ምርጫ ወቅት ለ200 ሰዎች ሞት እና በመቶዎች ለሚቀጠሩት ቁስለኞች ተጠያቂ በሆኑ 13 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ወታደራዊ አዛዦች ላይ ለፖሊስ የክስ አቤቱታ አስገቡት በስዊድን ታዋቂ የሆኑት ጠበቃ ስቴላ ጋርደ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በቅርቡ ለፖሊስ ከገባው አቤቱታ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በግፍ ለተገደሉት፣ ለቆሰሉት ፣ ለታሰሩት፣ ከስራ ለተፈናቀሉት አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍል ለማስገደድ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። አብዛኛውን የምርመራ ስራ የሚሰራውና ወጪውን የሚሸፍነው የስዊድን ፖሊስ ቢሆንም፣ ምስክሮችን ለማስመጣትና ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ገንዘብ የሚያስፈልገው ክሱን ለሚመሰርቱት የህግ ባለሙያዎች አይደለም የሚሉት ስቴላ፣ በክርከሩ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ቢያሸንፍ፣ መንግስት ለሚያቆመው ጠበቃ ወጪ መከፈል ስላለበትና ወጪውን የሚሸፍነውም የተረታው አካል በመሆኑ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በክሱ ከተረታ ግን በውጭ ያለው ሃብቱ ታግዶ ለተጎጂዎች እንዲሰጠጥ ይደረጋል ብለዋል። በ13 የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የክስ አቤቱታ ቢቀርብም በመንግስት ላይ እስካሁን አልቀረበም ያሉት ስቴላ፣ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን መዋጪ ማድረግ ከቻሉና በቂ ገንዘብ እንዳለ ሲታወቅ የካሳ መጠየቂያ ክሱ ወዲያው ይከፈታል ብለዋል። ማንኛውም ገንዘብ አለማቀፍ ደረጃ ባላቸው የሂሳብ ሰራተኞች እንደሚታይና የተዋጣው ገንዘብ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል። ሰሞኑን ለፖሊስ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ስቴላ፣ ፖሊስ ማመልከቻውን ተቀብሎ ምርመራ መጀመሩንና በሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት ውስጥ ለስዊድን አለማቀፍ ወንጀል አቃቢህግ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። አቃቢ ህግ የቀረቡትን መረጃዎች አይቶ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድ እንደሚወስን የገለጹት ስቴላ፣ የቀረቡት ማስረጃዎች ክሱ በአጭር ይቋጫል ብለው ለመናገር እንደማያስድፈራቸው ገልጸዋል። ከአለፉት አስር አመታት ወዲህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች በየትኛውም አገር መታየት መጀመራቸው ክሱን ለመመስረት እንዳነሳሳቸው ጠበቃው ገልጸዋል። አቃቢ ህግ ክስ ለመመስረት ከወሰነ ስዊድን ውስጥ ያሉ ተጠያቂዎች በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ፣ ሌሎች ከስዊድን ውጭ የሚኖሩ ባለስልጣናት ደግሞ በኢንተርፖል በኩል ስማቸው ተላልፎ ተይዘው ክሳቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግ አክለው ገልጸዋል። ከጠበቃ ስቴላ ጋርደ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ በነገው ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን።
http://abbaymedia.com/amharic/2014/09/04/%E1%89%A0%E1%89%82-%E1%8B%A8%E1%8C%88%E1%8A%95%E1%8B%98%E1%89%A5-%E1%8B%B5%E1%8C%8B%E1%8D%8D-%E1%88%B2%E1%8C%88%E1%8A%9D-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%89%A01997-%E1%8C%89%E1%8B%B3/
No comments:
Post a Comment