አባትነት በተግባር - የዓመቱ ምርጥ አባት!
አካለ ስንኩል የሆነውን ልጁን በትከሻው በመሸከም በየቀኑ 14.4ኪሜ (9ማይል) በእግሩ በመጓዝ ለሚያመላልሰው አባት መንግሥት በአቅራቢያው ቤት እንደሚሰጠው ተነገረ፡፡
በደቡብ ምዕራብ የቻይና ግዛት የሚኖረው የአርባ አመቱ አባት አካለ ስንኩል የሆነውን የ12ዓመት ልጁን ት/ቤት ለማስገባት ካለው የጸና እምነት የተነሳ ልጁ ራሱን ችሎ መራመድ የማይችል በመሆኑ ለመጓጓዣ ባዘጋጀው ለየት ያለ ቅርጫት በመሸከም ከመስከረም ወር ጀምሮ እያመላለሰው መሆኑን የቻይናን ዜና ምንጮችን ጠቅሶ ዴይሊ ሜል ዘግቧል፡፡
ልጁ የሦስት ዓመት ህጻን በነበረበት ወቅት ከወላጅ እናቱ ጋር የተለያየው አባት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ልጁን ብቻውን ያሳደገው ሲሆን እናቱ ብትለይም ልጁን ብቻውን ለማሳደግ በመወሰን መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል የዚያኑ ጊዜ መወሰኑን ተናግሯል፡፡ ልጁ እያደገ ሲመጣ ት/ቤት ለማስገባት በአካባቢው ያሉትን ሲጠይቅ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ከአካባቢው ርቆ ወደሚገኝ ት/ቤት ለማስገባት ይወስናል፡፡ ሆኖም ት/ቤቱ ከሚኖርበት ገጠር 7.2ኪሜ (4.5ማይል) የሚርቅ በመሆኑ ልጁን ራሱ ተሸክሞ ለማመላለስ በመወሰን ከመስከረም ወር ጀምሮ እያመላለሰው እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
በሚያደርገው ደስተኛ እንደሆነ የተናገው አባት ልጁ በት/ቤት ውጤቱ ከክፍሉ አንደኛ መሆኑ እንደሚያኮራው ይናገራል፡፡ “ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ አውቃለሁ፤ ሕልሜ ኮሌጅ እንዲገባ ነው” በማለት በልጁ ያለውን ተስፋ ይናገራል፡፡
በአካባቢው የሚገኝ የዜና ዘጋቢ ጉዳዩን ይፋ ካደረገው በኋላ የአካባቢው የመንግሥት መስተዳድር በልጁ ት/ቤት አቅራቢያ ቤት እንደሚከራይለት ለአባትየውና ለልጁ ቃል ገብቷል፡፡ ት/ቤቱም ወደፊት ለእንደነዚህ ዓይነት ልጆች የሚሆን የማደሪያ ቦታ ለማመቻቸት ማሰቡን ገልጾዋል፡፡
http://www.goolgule.com/father-of-the-year/
No comments:
Post a Comment