Wednesday, March 26, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር 5 ነገረ- ኢትዮጵያ ጋዜጣ ርእስ አንቀጽ – ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል!

ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል! እንዲህም ተብሏል ለውጥን ማዘግየት ይቻል እንደሆን እንጂ ገድቦ ማስቀረት እንደማይቻል ከትርክት አልፎ በተግባር የታየ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴን አፍኖ መዝለቅ የማያዛልቅ ሙከራ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሀገራት ታይቷል፡፡ በዓለም ላይ የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ ራሱ ለውጥ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ‹‹እነዚያ ሰላማዊ ለውጥን የማይቻል ለማድረግ የሚሞክሩ ሁሉ ሀይል ያመዘነበት አብዮትን የማይቀር ያደርጉታል›› እንዲሉ ለውጥን ለመገደብ መሞከር በራሱ ከዚያም በላይ የሆነ ታላቅ አብዮትን ይጠራል፡፡
በሀገራችን ለበርካታ ጊዜያት ይህ ሀቅ በእውን ተከስቷል፡፡ 40 አመታትን ወደኋላ ብንጓዝ እንኳ የ1966ቱ አብዮት ያለበቂ ዝግጁነት የተካሄደ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በወቅቱ የኑሮ ውድነት፣ ብዝበዛ እንዲሁም ቅጥ ያጣ በስልጣን መባለግ የነበረ ቢሆንም፣ የአጼው ስርዓት የህዝብን ሰቆቃና ቅያሜ፤ የዓለምንና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከምንም ባለመቁጠሩ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አብዮት፣ በአግባቡ መርቶ ፍሬያማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ባለመሰራቱ አሁን ድረስ ለዘለቀው የፖለቲካችን ብልሹነትም ሆነ ለስርዓቱ አሳዛኝ መጨረሻ ጉልህ አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ህዝባዊ አብዮት መቼ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በእርግጠኝነት ለማወቅ ቢከብድም በአንዲት ሀገር ያለው ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ግን የለውጡን ነጋሪት ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ሀገራት የተነሱትን አብዮቶች ስናይ፣ ማናቸውም በአምባገነን የአገዛዝ ስርዓት ስር የሚገኝ ህዝብ ነጻነቱን በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለማወጅ ወደ ኋላ እንደማይል ነው፡፡ በቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና በሌሎችም ሀገራት የተስተናገደውን ህዝባዊ አብዮት ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ መሰል አብዮት ከወደ ዩክሬን ተስተናግዷል፡፡ የዚህ ሁሉ አብዮት መንስኤ በየሀገራቱ ሰፍኖ የቆየው አምባገንነት ነው፡፡ ወደ ሐገራችን ሁኔታ ስንመለስም ከ1966ቱ ጊዜ በባሰ የኑሮ ውድነት፣ የሐይማኖት ጣልቃገብነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የመሰረታዊ አገልግሎት መጓደልና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበው የህዝብን ጫንቃ አጉብጠውት ይገኛሉ፡፡
ይህን በሀገራችን የተንሰራፋውን ጭቆናና የኑሮ ውድነት ስናይ የህዝባዊ አብዮትን መምጣት እንድንገምት ያደርገናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሲጠራቀም በቆየ የህዝብ ብሶት ምክንያት ሊነሳ የሚችልን የህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ ማስቀረት አይቻልም፡፡
ትንታጉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ደጋግሞ ይለው እንደነበረው ዳግም አብዮቱ በኢትዮጵያ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ይህን ለውጥም የሚያስቀረው ኃይል አይኖርም፤ ያለው ብቸኛ አማራጭ (በተለይ በመንግስት በኩል) የሚመጣውን ለውጥ በአግባቡ ማስተናገድ ወይም ‹ማኔጅ› ማድረግ ነው፡፡
በእርግጥም ለውጡ ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አኳያ ሲታይ መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ ለሚመጣው ህዝባዊ እንቅስቃሴና ለሚከተለው ለውጥ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የተከሰተውን ህዝባዊ አብዮት በአግባቡ አለመምራትና አለማስተናገዳችን ያስከተለብንን አሉታዊ ተጽዕኖ የዛሬ 40 ዓመት አይተናል፡፡ አሁን ከዚያ ድክመታችን ትምህርት ቀስመን የቀረበ የሚመስለውን የለውጥ ትግል መምራትና ማስተናገድ እንዳለብን እሙን ነው፡፡
በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ሁለት ዋና ዋና አካላት ይበልጡን ከፊት የሚገኙ ይሆናል፡፡ አንደኛው መንግስት ሲሆን ሌላኛው በተቃውሞ ጎራ ያለውና የትግል አቀጣጣዩን ክንፍ (ነጻ ማህበራት ሊሆኑ ይችላሉ) የሚያካትተው አካል ነው፡፡ መንግስት ቢችል ለውጡን የማደናቀፍ ስራን ለመስራት መሞከሩ አይቀርም፡፡ ከዚህም አልፎ ጭራሹን የህዝብን እንቅስቃሴ ለመጨፍለቅ ሊሞክር ይችላል፡፡ ይህም እርምጃ እጅጉን አደገኛና ክቡር ህይወትን ሊቀጥፍ የሚችል እስከመሆን ይደርስ ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ እርምጃ የሚመጣው ለለውጡ ካለመዘጋጀት ስለሚሆን በመንግስት በኩል ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ነገረ-ኢትዮጵያ ማሳሰብ ትወዳለች፡፡
ይህን በማድረግም መንግስት ቢያንስ ለውጡን ‹ማኔጅ› በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይቻለዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የለውጡን እንቅስቃሴ በአግባቡ መርቶ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ለማስቻል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድና በነጻ ማህበራት በኩል በቂ ዝግጅት ማድረግን እንደሚጠይቃቸው ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ምንም ያህል ከስርዓቱ ወገን ለውጥን ለማስተናገድ ያለመፈለግና ያለመዘጋጀት ቢታይም እንኳ ህዝብ የተነሳለትን ዓላማ ማስቀረት እንደማይቻል ተገንዝበው፣ ለውጡን በተደራጀና በአንድነት መንፈስ ለመምራት የፓርቲዎችና የማህበራት ሚና የጎላ መሆኑ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም እነዚህ አካላት ጥቃቅን ልዩነቶች ሊኖራቸው ቢችል እንኳ በእንዲህ አይነት ወቅት ትብብራቸውን ማጠናከርና ለጋራ የህዝብ ጥቅም መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ እውን ከሆነ ማግስት ሌላ ችግር እንዳይከሰት ህዝብ አመኔታ የሚጥልበትና በቀጣይ የመሪነት ሚናን ለመወጣት ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ መውጣት ግድ ይላል! ለዚህም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል!
negere_ethiopia_032614
ሙሉዉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !

No comments:

Post a Comment