Saturday, March 29, 2014

ኑ! እንዋቀስ፤ ኢህአዴግንም እናፍርሰው! (ተመስገን ደሳለኝ)


(ይህ “ኑ! እንዋቀስ” የሚለው ስር ነቀል የለውጥ ጥሪ ቀጥታ የሚያነጣጥረው በኢህአዴግ አባላት ላይ ብቻ ነው፤ አመራሩን በፍፁም አይመለከትም)
ኢህአዴግ ራሱ በይፋ ሲናገር እንደተደመጠው፣ በአሁኑ ጊዜ የአባላቱ ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ደርሷል፡፡ ይህም የአገሪቱ ቁጥር አንድ ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲ ያደርገዋል፡፡ በርግጥ ግዙፍ እንጂ ጠንካራ እንዳላልኩ ልብ ይሏል፡፡ ምክንያቱም ጥንካሬ የሚለካው በአባላት ቁጥር ሳይሆን በድርጅት ፍቅር፣ በዓላማ ፅናትና በሚሰጡት ልባዊ አበርክቶ ነው፡፡Journalist Temasegan Dasaleg
እንዲህ ያለ አቋመ-ብርቱነት ደግሞ ድሮ በያ ትውልድ ጊዜ ቀርቷል፡፡ በዘመነ-ኢህአዴግ የተንሰራፋው ጥቅመኝነት (በእነርሱ ቋንቋ ኪራይ ሰብሳቢነት) ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በደቡባዊቷ አዋሳ ከተማ ስድስተኛው የድርጅቱ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት፣ አቶ በረከት ስምኦን በብስጭት እየተትከነከነ በደፈናው ለጥቅም ድርጅቱን የተቀላቀሉ አባላት በርካታ መሆናቸውን አምኖ በአደባባይ መናገሩ አስረጂ ሊሆነን ይችላል፡፡ ይህን ንግግሩንም አፍታተን ስናብራራው እንደሚከተለው ሆኖ እናገኘዋለን፡- የግንባሩ አባላት ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ገደማ የደረሰው በጥቅም በመደለል፣ በአንድ ለአምስት የጥርነፋ መዋቅር በፍርሃት ተጠፍንጎ በመያዙና በመሳሰሉት ነው (መቼስ አቶ በረከት ከድርጅቱ ጉምቱ መሪዎቹ አንዱ ነውና ዘርዝሮ እንዲያስረዳን አይጠበቅበትም)
የሆነው ሆኖ አባላቱ እንዲህ የመብዛታቸው ምስጢር የድርጅቱ አምባ-ገነንነት ባህሪይ መገለጫ እንጂ አመላይ አጀንዳ አሊያም ምትሀታዊ ችሎታ እንዳለው የሚያሳይ አይደለም፡፡ ይህ የትኛውም መሰል ሥርዓት ከተጠናወተው ሁሉንም ከመቆጣጠርና መጠቅለል (Totalitarianism) አስተሳሰብ የሚሰርፅ ማኪያቬሊያዊ አስተምህሮ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ‹‹አምባገነኖች የአንድ እናት መንትያ ልጆች ናቸው›› እንዲሉ፤ በ‹‹ቆራጡ መሪ›› ዘመነ-መንግስትም በጊዜው ከነበረው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አኳያ መሳ-ለመሳ ሊባል በሚያስደፍር ሁኔታ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሰማያዊ ካኪ ለባሽ የኢሠፓ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ግና፣ ያ ካኪ ለባሽ ሕዝብ፣ የልቡን በልቡ ይዞ ‹‹ቪቫ መንጌ!›› እያለ አሳስቆ በስተመጨረሻ ጉድ እንደሰራው ሁሉ፤ ‹‹ይህ የህዝብ ማዕበል…›› ተብሎ በአቶ መለስ ዜናዊ የተሞካሸው የ97ቱ የቅዳሜው መሬት አንቀጥቅጥ የሰልፍ ትዕይንትም፣ በድጋፍ ሳይሆን በግዳጅ የሰመረ መሆኑን ለማየት፤ አይቶም ለመመስከር ከሃያ አራት ሰአት ጊዜ በላይ አልወሰደብንም፡፡ እንዴት? ቢሉ በማግስቱ (ሚያዚያ 30) ለተቃውሞ ከወጣው ሕዝብ የቅዳሜዎቹም በብዛት መሳተፋቸውን በራሳቸው አንደበት ‹‹ትላንት ለቲሸርት፤ ዛሬ ለነፃነት!›› በሚል ሕብረ-ዝማሬ ከአደባባዩም አልፎ ከተማዋን በሚያናውፅ የለውጥ ጩኸት የመሰከሩበት ‹‹ፖለቲካ›› መቼም ቢሆን አይዘነጋምና፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ ታሪካዊ ሀቅ የሚገልፅልን አንድ ታላቅ እውነት-በጥቅም እየደለሉ አባልን ማብዛት በክፉ ቀን የማይታደግ መሆኑን ነው፡፡ ጥቅመኝነት ግፋ ቢል የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹‹ፀበል›› ያስጠምቅ፣ ‹ኢህአዴግ ጌታ ነው!›ን ያስፎክር ያሸልል ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያን ትንሳኤ መሻትን አያስቀይርም፡፡ ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይለውጠው ሁሉ የኢህአዴግ አባላትም ምንም ቢሆን ምን፣ እንደሌላው ሕዝብ የሀገር አንድነት የሚያሳስባቸው፣ ብሔራዊ ውርደት (ረሀብተኝነት) በቁጭት የሚያንገበግባቸው፣ ከዘውግ ልዩነት የሕዝብ ለሕዝብ መተማመንና አንድነታዊ ጥንካሬው የሚበልጥባቸው፣ የኃይማኖት ነፃነት የሚያስተቃቅፋቸው… ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጥቅመኝነት የእጦትን ክፍተት ለመሙላት ለጊዜው ያሰግዳል እንጂ ክብርንና ማንነትን አስሽጦ በባርነት ቀንበር አያሳድርም-በተለይም ዥንጉርጉርነቱን ጠንቅቆ ለሚያውቀው ኩሩ-ሀበሻ!
ደግሞስ ምን ያህሉ አባል ነው፣ የድርጅቱን መታወቂያ በመያዙ ብቻ የረባ ጥቅም ያገኘው? በግላጭ እንደሚታየው በግል ጥቅምም ሆነ በተጭበረበረው የዘውግ ፖለቲካ ሳቢያ ኢህአዴግን የተቀላቀሉ የአብዛኞቹ አባላት የኑሮ ደረጃ ዛሬም እንደ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከችግር የመቆራመድ አስከፊ ሕይወት አልተላቀቀም፡፡ ፓርቲውን መታከካቸውም በማይጨበጥና በማይታይ እንቅልፍ የለሽ ሕልም አናውዞ ይበልጥ ደቁሷቸዋል እንጂ በቀን ሶስቴ መመገብ እንኳ አላስቻላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የድርጅት አባልነታቸው እንደተርታው ሕዝብ በአድሎአዊ አሰራር መማረርን እንዳላስቀረላቸው በርግጠኝነት መመስከር ይቻላል፡፡
ይህ አይነቱም እርግጠኝነት ነው ‹ኑ! እንወቃቀስ (እንነጋገር)፤ እንተማመንምና ሀገርና ትውልድ እየገደለ ያለውን ፓርቲያችሁን አብረን ተጋግዘን እናፍርሰው› የሚል የማንቂያ ደውል ላሰማችሁ ገፊ-ምክንያት የሆነኝ፡፡ እናም ድርጅታችሁን ትመረምሩ ዘንድ ወደድኩ፡-
ድርጅታችሁ ሥልጣን ላይ ተፈናጥጦ ባሳለፋቸው ሁለት አስርታት የተጓዘበትን መንገድ በአስተውሎት ብትመረምሩ፤ በእርግጠኝነት እንደ ግዙፍ ዐለት ካገጠጡ ሀገራዊ ውድመቶች እና ከበባድ ኪሳራዎች ጋር መፋጠጣችሁ አይቀሬ ነው፡፡
ይህም ሆኖ በቅድሚያ በተልካሻ ፕሮፓጋንዳ ያሰለቸንን የብሔር ጉዳይ (የተወሰኑ ሰዎችን አማልሎ አባል ለማድረግ አስተዋፆ እንዳለው ባይካድም) ወደጎን ብለን፤ የትኛውም ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶቹን ማክበር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጠቀም… የፖለቲካ ፓርቲ በችሮታ የሚሰጠው ሳይሆን፣ የማንም ተፈጥሮአዊ መብት መሆኑን ማስረገጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይህ ማለት ግን የድርጅታችሁ ሀቲት፡- ‹አንዱ በሌላው እድሜውን ሙሉ ሲጨቆን እንደኖረ፤ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ እንደሆነ፤ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ይልቅ የክልሉን እንዲያስቀድም መቀስቀስና መስበክን የብሔር ብሔረሰብ መብትን ማክበር ነው› የሚለውን አምኖ መቀበል አይደለም፡፡ በግልባጩ ስርዓቱ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን ሰማይ ጥግ አጉኖ፣ ሕዝብን ከፋፍሎና በጥርጣሬ (በጎሪጥ) ወደሚተያይበት ጠርዝ ገፍቶ፣ የሥልጣን ዕድሜውን ያራዘመበት ሁለት አስርታትን ያሳለፈ ስልቱ መሆኑን መረዳት አይሳናችሁም ብዬ አስባለሁ፡፡
ሌላ ሌላውን ትተን እንኳ የኢህአዴግን አመሰራረት ብንመለከት ግንባሩን ከፈጠሩት አራቱ ድርጅቶች መካከል ከሞላ ጎደል ህወሓት እና ኢህዴን/ብአዴንን እንደ ፖለቲካ ድርጅት መውሰድ ይቻል ይሆናል እንጂ፤ ኦህዴድና ደኢህዴን፣ በህወሓት ‹‹አባ መላ››ዎች እንደ የፋብሪካ ሳሙና በሚፈለጉበት መጠንና ቅርፅ ተጠፍጥፈው ከተሰሩ በኋላ በኦሮሞና በደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች ላይ እንደ አለቅት የተጣበቁ የመሆናቸውን ምስጢር እነርሱም ራሳቸው የሚክዱት አይመስለኝም (ምናልባት በሽግግሩ የመጀመሪያ ዓመት ላይ እንደአስተዋልነው ከኦህዴድ ይልቅ፣ ኦነግ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎችን ወክሎ ቢቀጥል ኖሮ ይህ ጉዳይ በዚህ አውድ ላይነሳ ይችል ነበር፡፡ የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፤ የራሱ የፖለቲካ ቁመናና ራዕይ የነበረው በኃይል ተገፍቶ፤ በምትኩ በሌሎች እስትንፋስ ህልው ሆኖ
‹‹የሚያስተዳድረው››ን ሕዝብና ራሱንም ጭምር ቀን ከሌት ‹‹ከብሔር ጭቆና ነፃ አወጣናችሁ›› ስለሚሉት ሞግዚቶቹ ገድል መተረክን ‹‹ፖለቲከኛነት›› አድርጎ የወሰደው ኦህዴድን ያነገሰ ነውና)
በነገራችን ላይ የፖለቲካ ፓርቲን እንደ ፋብሪካ ምርት ጣጣ-ፈንጣጣው ተጠናቅቆለት ሲያበቃ የመጫኑ አሰራር በሁለቱ ክልሎች ብቻ ተገድቦ የቀረ አይደለም፤ አጋር ፓርቲዎችንም ይመለከታል፡፡ ከአፋር እስከ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል፤ ከሀረር እስከ ሶማሌ ሲተገበር በትዝብት የተመለከትነው ጉዳይ ነው፡፡ መቼም ገና ከስር መሰረቱ ‹‹እኛ እናውቅልሀለን!›› በሚሉ ‹‹የፖለቲካ ሞግዚቶች›› የተፈጠረ ድርጅት በምደባ ቦታውን ያገኙ የአመራር አባላቱን በቅምጥል ኑሮ ከማንፈላሰስ በዘለለ፣ ‹‹እወክለዋለሁ›› ለሚለው ሕብረተሰብ ትርጉም ያለው ስራ ይሰራል ተብሎ የሚታሰብ አይደለምና ‹በኦሮሚያ ሙስና እንደሰላምታ እጅ መጨባበጥ ተዘውታሪና ተራ ነገር ነው›፣ ‹በአፋር ባጀት መቀለጃ ሆኗል›፣ ‹በሐረር ቤተሰባዊ ኢምፓየር ተገንብቷል›፣ ‹ቤንሻንጉል በድህነት ማቀቀ›፣ ‹ሶማሌ ክልል የአስተዳዳሪው አብዲ ርስተ-ጉልት ሆነ› ጂኒ ቁልቋል እያሉ ሮሮዎችን ማሰማት ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ህወሓትን እንደ ‹‹ግል አዳኝ›› በመቀበላቸው ብቻ ‹‹የአስተዳዳሪነት›› ካባ የተደረበላቸው ምስኪን የአመራር አባላት በቀላል ጉዳይ ላይ እንኳ የመወሰን ሥልጣን የላቸውምና ነው፡፡
ይህ እንግዲህ በቀጥታ ከኢህአዴግ ስነ-ተፈጥሮ ጋር የሚጋመድ ችግር ነው፡፡ ሆኖም የመንግስት ሥልጣን መዘውር ከጨበጠ በኋላ የጨፈለቃቸውን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የደረሱ የአያሌ ሰላማዊ ዜጐች ግድያ፣ እመቃ፣ ከስራና ቤት ንብረት መፈናቀል፣ ስደትን… አንድ በአንድ ጠቅሰን ለማውገዝ ብንሞክር ሰማይ-ብራና፣ ቀይ ባህር-ቀለም ሆነው ካልተመቻቹልን በቀር የሚደፈር አይመስለኝም፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ ውስጥ ታላቅና ታናሽ ንጉሠ-ነገሥት የሆኑት ህወሓትና ብአዴን ብረት ነክሰው፣ ሳንጃ ወድረው በትጥቅ ትግል ያለፉ ከመሆናቸው አኳያ ለየትኛውም አይነት ቅራኔም ሆነ ልዩነት ከመግደልና መጋደል ውጪ ያለ ሌላ ሰላማዊ አማራጭ ላይዋጥላቸው እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ከተገፋበት ጊዜ አንስቶ በኦሮሚያ፣ በአዋሳ፣ በሶማሌ… ግፉአን ያለቁበትን፤ እንዲሁም በድህረ-ምርጫ 97 የታየው የጎዳና ላይ ጭፍጨፋ ይህንኑ ሀቅ ያስረግጣሉ፡፡
ኩነቱም ግንባሩ በመጣበት አይነት የነፍጥ የበላይነት ያለፉት ሶቪየት ህብረት፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ ኩባ፣ ኤርትራ ባሉ ሀገራት ከታየው የሕዝቦች እልቂት፣ የተቀናቃኝ ድምፆች መታፈን፣ የጋዜጠኞች መጨፍለቅ… ጋር ቀጥታ ዝምድና አለው፡፡ እነዚህ ሀገራትንም ሆነ ኢህአዴግን የተለየ ሃሳብ ለማስተናገድ ትዕግስቱም ፍላጎቱም እንዳይኖራቸው ያደረገው ይህ ከውልደታቸው ጀምሮ ከደም-አጥንታቸው ጋር የተዋሃደው ተፈጥሮአቸው ይመስለኛል፡፡
በአናቱም ኢህአዴግ ከአባላቱ ይልቅ የአመራሩ ‹‹ፓርቲ›› ብቻ ስለመሆኑ ለመረዳት የውስጥ አሰራሩን መፈትሽ የተሻለ ይሆናል፤ እናንተም በቅርበት እንደምታውቁት በድርጅቱ ያልተፃፈ ሕግ ከላይ ወደታች የሚወርድ መመሪያን ትክክል ሆነም አልሆነ ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ የሚያስቀስፍ ሀጢያት ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመወያየት መሻት፣ ጥያቄ ማቅረብ፣ ሃሳብን መቃወም፣ ስህተቶችን ማጋለጥ… አሳድዶ በድንጋይ የሚያስወግር አሊያም ከሀገር ሀገር የሚያሰድድ ታላቅ ጥፋት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ይህ ሁናቴም ነው የአስተዳደር ድክመቶቹንም ሆነ አውዳሚ ጉድለቶቹን በፍጹም ለሕዝብ እንዳይደርሱ ገትሮ መያዝን የማይዘናጋበት ዋነኛ መንግስታዊ ስራ ያደረገው (የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በውሃ ቀጠነ ወደ እስር ቤት ሲያግዝ መክረሙን ልብ ይሏል) በጥቅሉ ድርጅቱ ለአመራሮቹ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በተደረገባቸው ዘመናዊ “V8” መኪናዎች እንዲምነሸነሹ እና በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት እንዲዘርፉ የሚያስችል ስልጣን ከማጎናፀፉ ባለፈ፤ እናንተ (ብዙሀኑ አባላት) ያተረፋችሁት ምንድር ነው? በአነስተኛና ጥቃቅን ከመደራጀት፣ ‹‹ኮብል-ስቶን›› ፈልጦ ከመደርደር የዘለለስ ማን ምን ሊጠቅስ ይችላል? እስቲ! የተራቆተችና በድህነት ወጀብ የተንገላታች ሀገራችሁን በዓይነ-ልቦናችሁ ለማስተዋል ሞክሩ፡፡
ያን ጊዜም ገና ጀንበር ስታዘቀዝቅ ስጋቸውን ለመቸርቸር ጎዳናዎችን የሚያጥለቀልቁ እምቦቀቅላ እህቶቻችን፣ ‹‹ማምሻም ዕድሜ ነው›› እንዲሉ የመፅዋች ዓይን እየገረፋቸው በልመና ቁራሽ ሕይወታቸውን የሚውተረተሩ አዛውንትና ህፃናት፣ በየጎዳናው በየሰፈሩ ሲንገላወዱ የሚውሉ ስራ-አጥ ወጣቶች፣ በቀን አንዴ ለመመገብ ላይ ታች የሚማስኑ ለፍቶ አዳሪዎች… ምድሪቷን እንዳጨናነቋት ይገለፅላችኋል፡፡ የዚህ ሁሉ መንስኤም የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን ፅንፈኛው ድርጅታችሁ በሚከተለው በተግባር ያልተፈተነ (የሀገሪቱን ተጨባጭ እውነት ያላገናዘበ) ርዕዮተ-ዓለም፣ ፖሊሲ፣ አድሎአዊ አሰራር፣ ሙስና እና ለኃላፊነት የማይመጥኑ ‹‹አስፈፃሚዎች›› ችግር ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ጥርጣሬ አይግባችሁ፡፡
እናም ጉዳዩ የሀገር ነውና በግልፅ እንወቃቀስ (እንነጋገር)፤ ስለምንድነው በአባልነት በምታገለግሉት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ‹ዛሬም በስኬት ጎዳና እየጋለብኩኝ ነው› ብሎ እንደ ቁራ እየለፈፈ በተግባር ግን፡- መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ፣ ኔት-ወርክ እንደ አደይ አበባ በዓመት አንዴ ብቻ ብቅ የሚለው? በአገልግሎት ተቋማት መጠቀምስ እንዲህ የአሲምባን ያህል ያራቀው ማን ነው? ፍትሕን የጠሉትን መበቀያ መሳሪያ አድርገው ያረከሱት እነማን ናቸው? ሰርቶ መብላት የማይጨበጥ ጉም የሆነብንስ በማን የተነሳ ነው? …በርግጥ ይህንን ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ብናቀርብለት እንደ መለስ ዜናዊ በተረት መሳለቁ ባይሆንለትም፣ ‹‹ሰለሜ ሰለሜ››ን እየጨፈረ፤ እነ‹‹ሚካኤል ስሁል›› በቀደዱለት ልክ ዳናኪራውን እያስነካው ‹‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም!›› ብሎ ከመዘባበት አይመለስም፡፡ መቼስ እንደዚህ ሕዝብ የተናቀ የትም አይገኝም፡፡
ኢህአዴግ መፍረስ ያለበት ለምንድን ነው?
‹‹አንተ ሌዎናርዶ የሮማ ጅል
የሰራሀትን ልታሻሽል
ልታፈርሳት ልትገነባት
ደግመህ ደጋግመህ ልትሰራት
ሰልሰህ ልትሰራት ስትችል
ጣኦት አደረግካት በሞትህ አጉል አጉል
ለራስህ ፍጡር እግዚኦ ልትል››
ይህ ግጥም በሰፈረበት ገፅ ላይ የተጠቀሰው የግርጌ ማስታወሻ ደግሞ ሊተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-
ታዬ የሚባል የኢህአፓ ታጋይ ‹ራሳችን የፈጠርነውን ድርጅት ማስተካከል አለብን› የሚል እምነት የነበረው ሲሆን፣ ዳ ቪንቺ እራሱ ለሳላት ሞናሊዛ ፍቅር እንደተማረከ ሁሉ እኛም የፈጠርነውንና የተበላሸውን ድርጅት አመለክነው፤ ማስተካከልም ተሳነን በማለት ፓርቲው ላይ እምነት ማጣቱን ‹ሞናሊዛ› በሚል ርዕስ በፃፈው ውብ ግጥም ገለፀ፡፡  (ገፅ 61)
እነሆም አብዮታዊ ግንባሩ፣ ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው ኢህዴን/ብአዴን፣ ያን ጊዜ ኢህአፓን መክሰሻ ባደረገበት ‹‹ድርጅታዊ አምልኮ›› ራሱም ተጠልፎ ከወደቀ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ታዬ እንዳለውም መሪዎቹ ኢህአዴግን ናቡከደናፆር አሰርቶት እንደነበረው አይነት እጅግ ግዙፍ ‹‹አምላክ›› (ጣኦት) አድርገው ሀገርና ሕዝብን እየገበሩለት (እየሰዉለት) ነው፡፡ ርዕዮተ-ዓለምም ሆነ ፖሊሲ (በተለይ መሬትን በተመለከተ) ‹‹የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው›› ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ፖሊሲውም እንዲህ ትውልድን እየገደለም እንዲሻሻል ያልተሞከረው በዚሁ እምነታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁኔታም ነው እናንተም የምትስማሙባቸውን ታላላቅ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ኢህአዴግን ከማፍረስ ውጪ አማራጭ እንዳይኖር ያደረገው፡፡
ከእንግዲህ ወዲያም ከጥፋቱ ታርሞ ለሀገር የሚጠቅም ዲሞክራሲያዊ የህዝብ ሥርዓት ሊያነበር ይችላል ብሎ ተስፋ ማድረግ ተላላነት ነው፡፡ እንኳን እናንተ ከተማ ላይ የተቀላቀላችሁት አባላት ቀርቶ፣ ከበርሃ አቅፈው ደግፈው እዚህ ያደረሱት አንጋፋ ታጋዮችና አንዳንድ አመራሮቹም በድርጅቱ ተስፋ ቆርጠው ጥለውት መሄድ ከጀመሩ ሰንብቷል፡፡ ታጋይ የውብዳር አስፋው ‹‹ፊኒክሷም ሞታ ትነሳለች›› በሚለው መጽሐፏ እውነታውን እንዲህ በማለት ገልፀዋለች፡- ‹‹የድርጅቱ አመራር የወሰዳቸውን የተሳሳቱ እርምጃዎች ቀድሞ ከነበረኝ የድርጅቱ ግንዛቤ ጋር በማጣመር ለዓመታት የታገሉለትንና የደከሙለትን አባላት በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ያላስቻለ ድርጅት፣ ለሕዝብ ነፃነትና ለዲሞክራሲ እታገላለሁ ቢል ከይስሙላ የማያልፍ ከንቱ መፈክር መሆኑን ደምድሜ፣ ከመጋቢት 5 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ ራሴን ከድርጅቱ አገለልኩ፡፡ ይህም በሕይወቴ ጉዞ ዋነኛውና ወሳኝ እርምጃ ነበር፡፡›› (ገፅ 16)
እንግዲህ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የድርጅት፣ የሴቶች ጉዳይና የመንግስት ሥራዎች ተሰማርታ ልጅነቷን በትግል የጨረሰችው የአቶ ገብሩ አስራት ባለቤት፣ የውብዳር አስፋው እንዲህ አይነቱን ከባድ ውሳኔ በማሳለፍ ከኢህአዴግ ከተቆራረጠች እነሆ አስራ ሶስት ዓመታት ነጉደዋል፡፡ በግልባጩ እናንተ ደግሞ እስካሁን ድረስ አንቀላፍታችኋል-ገና አልነቃችሁም፡፡ እናም እውነት እውነት እላችኋለሁ፡- ከዚህ በላዔ-ሰብ ሥርዓት ለመገላገል የምንችለው፣ ዛሬውኑ ይህንን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ዋነኛና ወሳኝ እርምጃ በቆራጥነት መውሰድ ስትችሉ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ…
(የዚህ ጽሑፍ ሃሰበ-መልዕክትን በቅንነት ትቀበሉታላችሁ በሚል መተማመን አፈፃፀሙን፡- በምን አይነት መንገድ ተቀራርበን ልንወያይ እንችላለን? በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይቻላል? ሃሳቡንስ ከግብ ለማድረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን በሌላ ዕትም ተገናኝተን በስፋት እንመክርባቸዋለን)
አትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11596/

Friday, March 28, 2014

የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፈኑ

“ወያኔ እጅ ገብተዋል”

south sudan juba

የጋምቤላ ክልልን ሲመሩ ቆይተው ባለመስማማት የኮበለሉት የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸው ተጠቆመ። ዜናው በገለልተኛ ወገን ባይገለጽም ኖርዌይ በስደት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ በኢህአዴግ በጥብቅ የሚፈለጉ ሰው ነበሩ።
በመለስ ዜናዊ ውሳኔ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ወደ ደቡብ ሱዳን ከማምራታቸው በፊት ኬንያ እንደነበሩ፣ ከኬንያ ወደ ደቡብ ሱዳን ለምን እንደተጓዙ የዜናው ምንጮች በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ስማቸው እንዲደበቅላቸው የጠየቁ የጋምቤላ አስተዳደር ባልደረባ ለጎልጉል የአካባቢው ዘጋቢ እንደተናገሩት አቶ ኦኬሎ ደቡብ ሱዳን ሆቴል በተቀመጡበት መታፈናቸውን አረጋግጠዋል። “ወያኔ እጅ ገብቷል” ሲሉ ያከሉት እኚሁ ሰው “አቶ ኦኬሎ ብረት በማንሳት ወያኔን ለመታገል ከተነሱ ጋር ተቀላቅለዋል በሚል ስማቸው መመዝገቡንና ወደ ደቡብ ሱዳን ማቅናታቸው በመታወቁ ህወሃቶች እጅ ሊወድቁ ችለዋል” ብለዋል። ምንጩ ይህንን ይበሉ እንጂ አቶ ኦኬሎ አክዋይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀኑበትን ምክንያት በርግጠኛነት ሃላፊነት ወስዶ የገለጸ ወገን አልተደመጠም። ኢህአዴግም ቢሆን የቀድሞውን ሹመኛ ስለመያዙ ይፋ ያደረገው ነገር የለም።
ከደቡብ ሱዳን ቀውስ ጋር በተያያዘ የኑዌር ተወላጅ ከሆኑት ሬክ ማቻር ጦር ጋር በመሰለፍ የሳልቫ ኪርን ሃይል ሲወጉ ከተገደሉ ወታደሮች መካከል የኢህአዴግን ሰራዊት መለያ የለበሱ ኑዌሮች መገኘታቸው ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ያመለከቱት ምንጭ “ደቡብ ሱዳን እየወጋት ካለው ኢህአዴግ ጋር አብራ የቀድሞውን የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር ከምድሯ ላይ እንዲታፈኑ መፍቀዷ ቅሬታ ያስነሳል” ብለዋል።
ከቤተሰባቸው ተነጥለው በስደት ከሚኖሩበት ኖርዌይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያመሩት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ደቡብ ሱዳን በህወሃት ሙሉ ቁጥጥርና ፈቃድ የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን እያወቁ ወደዛ ማቅናታቸውን ባሥልጣኑ “ታላቅ ጥፋት” ብለውታል። ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በቅርቡ አቶ ኦሞት ኦባንግ መኮብለላቸውና በብዙዎች ዘንድ አውሮጳ እንዳሉ ቢነገርም በትክክል ያሉበት አገር በይፋ አለመታወቁን መዘገባችን ይታወሳል

Wednesday, March 26, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር 5 ነገረ- ኢትዮጵያ ጋዜጣ ርእስ አንቀጽ – ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል!

ለለውጡ ዝግጅት ያስፈልጋል! እንዲህም ተብሏል ለውጥን ማዘግየት ይቻል እንደሆን እንጂ ገድቦ ማስቀረት እንደማይቻል ከትርክት አልፎ በተግባር የታየ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴን አፍኖ መዝለቅ የማያዛልቅ ሙከራ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሀገራት ታይቷል፡፡ በዓለም ላይ የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ ራሱ ለውጥ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ‹‹እነዚያ ሰላማዊ ለውጥን የማይቻል ለማድረግ የሚሞክሩ ሁሉ ሀይል ያመዘነበት አብዮትን የማይቀር ያደርጉታል›› እንዲሉ ለውጥን ለመገደብ መሞከር በራሱ ከዚያም በላይ የሆነ ታላቅ አብዮትን ይጠራል፡፡
በሀገራችን ለበርካታ ጊዜያት ይህ ሀቅ በእውን ተከስቷል፡፡ 40 አመታትን ወደኋላ ብንጓዝ እንኳ የ1966ቱ አብዮት ያለበቂ ዝግጁነት የተካሄደ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በወቅቱ የኑሮ ውድነት፣ ብዝበዛ እንዲሁም ቅጥ ያጣ በስልጣን መባለግ የነበረ ቢሆንም፣ የአጼው ስርዓት የህዝብን ሰቆቃና ቅያሜ፤ የዓለምንና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከምንም ባለመቁጠሩ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አብዮት፣ በአግባቡ መርቶ ፍሬያማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ባለመሰራቱ አሁን ድረስ ለዘለቀው የፖለቲካችን ብልሹነትም ሆነ ለስርዓቱ አሳዛኝ መጨረሻ ጉልህ አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ህዝባዊ አብዮት መቼ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በእርግጠኝነት ለማወቅ ቢከብድም በአንዲት ሀገር ያለው ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ግን የለውጡን ነጋሪት ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ሀገራት የተነሱትን አብዮቶች ስናይ፣ ማናቸውም በአምባገነን የአገዛዝ ስርዓት ስር የሚገኝ ህዝብ ነጻነቱን በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለማወጅ ወደ ኋላ እንደማይል ነው፡፡ በቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና በሌሎችም ሀገራት የተስተናገደውን ህዝባዊ አብዮት ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ መሰል አብዮት ከወደ ዩክሬን ተስተናግዷል፡፡ የዚህ ሁሉ አብዮት መንስኤ በየሀገራቱ ሰፍኖ የቆየው አምባገንነት ነው፡፡ ወደ ሐገራችን ሁኔታ ስንመለስም ከ1966ቱ ጊዜ በባሰ የኑሮ ውድነት፣ የሐይማኖት ጣልቃገብነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የመሰረታዊ አገልግሎት መጓደልና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበው የህዝብን ጫንቃ አጉብጠውት ይገኛሉ፡፡
ይህን በሀገራችን የተንሰራፋውን ጭቆናና የኑሮ ውድነት ስናይ የህዝባዊ አብዮትን መምጣት እንድንገምት ያደርገናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሲጠራቀም በቆየ የህዝብ ብሶት ምክንያት ሊነሳ የሚችልን የህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ ማስቀረት አይቻልም፡፡
ትንታጉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ደጋግሞ ይለው እንደነበረው ዳግም አብዮቱ በኢትዮጵያ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ይህን ለውጥም የሚያስቀረው ኃይል አይኖርም፤ ያለው ብቸኛ አማራጭ (በተለይ በመንግስት በኩል) የሚመጣውን ለውጥ በአግባቡ ማስተናገድ ወይም ‹ማኔጅ› ማድረግ ነው፡፡
በእርግጥም ለውጡ ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አኳያ ሲታይ መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ ለሚመጣው ህዝባዊ እንቅስቃሴና ለሚከተለው ለውጥ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የተከሰተውን ህዝባዊ አብዮት በአግባቡ አለመምራትና አለማስተናገዳችን ያስከተለብንን አሉታዊ ተጽዕኖ የዛሬ 40 ዓመት አይተናል፡፡ አሁን ከዚያ ድክመታችን ትምህርት ቀስመን የቀረበ የሚመስለውን የለውጥ ትግል መምራትና ማስተናገድ እንዳለብን እሙን ነው፡፡
በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ሁለት ዋና ዋና አካላት ይበልጡን ከፊት የሚገኙ ይሆናል፡፡ አንደኛው መንግስት ሲሆን ሌላኛው በተቃውሞ ጎራ ያለውና የትግል አቀጣጣዩን ክንፍ (ነጻ ማህበራት ሊሆኑ ይችላሉ) የሚያካትተው አካል ነው፡፡ መንግስት ቢችል ለውጡን የማደናቀፍ ስራን ለመስራት መሞከሩ አይቀርም፡፡ ከዚህም አልፎ ጭራሹን የህዝብን እንቅስቃሴ ለመጨፍለቅ ሊሞክር ይችላል፡፡ ይህም እርምጃ እጅጉን አደገኛና ክቡር ህይወትን ሊቀጥፍ የሚችል እስከመሆን ይደርስ ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ እርምጃ የሚመጣው ለለውጡ ካለመዘጋጀት ስለሚሆን በመንግስት በኩል ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ነገረ-ኢትዮጵያ ማሳሰብ ትወዳለች፡፡
ይህን በማድረግም መንግስት ቢያንስ ለውጡን ‹ማኔጅ› በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት ይቻለዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የለውጡን እንቅስቃሴ በአግባቡ መርቶ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ለማስቻል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድና በነጻ ማህበራት በኩል በቂ ዝግጅት ማድረግን እንደሚጠይቃቸው ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ምንም ያህል ከስርዓቱ ወገን ለውጥን ለማስተናገድ ያለመፈለግና ያለመዘጋጀት ቢታይም እንኳ ህዝብ የተነሳለትን ዓላማ ማስቀረት እንደማይቻል ተገንዝበው፣ ለውጡን በተደራጀና በአንድነት መንፈስ ለመምራት የፓርቲዎችና የማህበራት ሚና የጎላ መሆኑ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም እነዚህ አካላት ጥቃቅን ልዩነቶች ሊኖራቸው ቢችል እንኳ በእንዲህ አይነት ወቅት ትብብራቸውን ማጠናከርና ለጋራ የህዝብ ጥቅም መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ እውን ከሆነ ማግስት ሌላ ችግር እንዳይከሰት ህዝብ አመኔታ የሚጥልበትና በቀጣይ የመሪነት ሚናን ለመወጣት ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ መውጣት ግድ ይላል! ለዚህም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል!
negere_ethiopia_032614
ሙሉዉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ !

Thursday, March 20, 2014

በጋዜጠኞች ላይ ያለ ማስረጃ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን!

ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) የተሰጠ መግለጫ
ማህበራችን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ የምዝገባ ሰርተፊኬት ለማግኘት የጀመረው እንቅስቀሴ በቅርቡ ከመንግስት አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የተቋቋመለትን አላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅና የመናገር ነፃነትን ከማበረታታት ባለፈም ከአህጉራችን አፍሪቃ ጋዜጠኞች ጋር በመተባበር የመላው አፍሪቃ ጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅና የመናገር ነፃነትን የሚያበረታታ አህጉራዊ ተቋም ለመመስረት ተነሳሽነትን ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የምስራቅ አፍሪቃ ጋዜጠኞችን በማስተባበር አህጉር አቀፍ እንቅስቃሴያችንን ለማስጀመር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተግባር ጋዜጠኛውን ሳይወክሉ የጋዜጠኛውን ስም የያዙት የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች በመቀናጀት በየሚዲያው እየቀረቡ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማትን ለማሸማቀቅ ያለመ ውንጀላና አሉባልታ የመንዛት ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርበው በጋዜጠኞች ላይ ከሽብር ፈጠራ እስከ ሀገር ማተራመስ የደረሰ የውንጀላ መዓት ቢደረድሩም አንዳችም ማስረጃ አላቀረቡም፡፡
ለምሳሌ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ (ቅጽ13 ቁጥር 737) ላይ ስማቸውን ደብቀው ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ጋዜጠኞች ሀገር ለማተራመስና ሽብር ለመፍጠር እየተዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ምን ማስረጃ አላችሁ” ለሚለው የጋዜጠኛዋ ጥያቄ የመለሱት “እኛ እና እነሱ እንተዋወቃለን፡፡” የሚል አስገራሚ መልስ ነው፡፡ ይህ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ጋዜጠኞችን ለማሸማቀቅ የተወረወረ በመሆኑ የኢጋማ፣ የኢነጋማና የኢብጋህ አመራሮች ነን የሚሉት ግለሰቦች ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ተቋማትን ያለ ማስረጃ መወንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲያቆሙ ይጠይቀል፡፡
በመቀጠልም በሪፖርተር ጋዜጣ (የዕሁድ እትም ቅፅ 19 ቁጥር 1446) የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም “ኢጋማ በምስረታ ላይ ያለውን የጋዜጠኞች መድረክ አስጠነቀቀ” የሚል ዜና ተመልክተናል፡፡ ሆኖም በጋዜጠኞች ስም ተሰባስበው ጋዜጠኛውን የሚጠቅም አንዳች እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ከመተኛታቸው ብዛት አልጋቸው ለረገበ ማህበራት ማስጠንቀቂያ ምላሽ በመስጠት ጊዜ በመሆኑም ምለሻችን በዝምታ መስራት ነው፡፡
የግለሰቦቹ የውንጀላ ንግግር የሚያስረዳው ከህግ፣ ከሞራል እና ከሙያዊ ስነምግባርም በላይ ራሳቸውን ለመሾም የሚፍጨረጨሩ መሆኑን ነው፡፡ ግለሰቦቹ በተለያዩ ጊዜያት መንግስት የፕሬስ ተቋማት ላይና ጋዜጠኞች ላይ የወሰዳቸውን ኢ-ህገመንግስታዊ እርምጃዎች እንደ ጋዜጠኛ ማህበር መሪ ከመኮነን ይልቅ የመንግስትን እርምጃ ሲያወድሱ ተስተውለዋል፡፡ በተጨማሪም በእስር ላይ ሆነው ህክምና በመከልከላቸው ለከፋ ስቃይ ስለተዳረጉ ጋዜጠኞችም ትንፍሽ ሲሉ አልታየም፡፡
እነዚህ የጋዜጠኛ ማህበራት መሪዎች ነን ያሉት ግለሰቦች እንደማህበር መሪ ሳይሆን እንደ ስለላ ተቋም ጋዜጠኞች እና አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ሃገር ለማተራመስና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መረጃ እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም
1ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች አለን የሚሉትን መረጃ ለመንግስት በአፋጣኝ ሳይሰጡ መቆየታቸው በሀገራችን ህግ መሰረት ሊጠየቁው እንደሚገባ እንዲሁም
2ኛ. የሶስቱ ማህበራት መሪዎች በጋዜጠኞች እየተቀነባበረ ነው ካሉት የሽብርና ሀገር የማተራመስ እንቅስቃሴ ጀርባ እንዳሉ የጠቀሷቸውን ኤምባሲዎች በግልፅ ጠቅሰው ለመንግስት እና ለህዝብ እንዲያስታውቁ እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ)
መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም

የአባ በላ ፍቅር እስከ መቃብር (ማህሌት ነጋ)

በማህሌት ነጋ
“ሃይለማሪም ደሳለኝ አብዩዝድ ነው። እንደውም ማታ ማታ (በህወሃቶች) ሳይገረፍ አይቀርም!” ብሎ ነበር ብርሃኑ ዳምጤ ከጥቂት ወራት በፊት በፓልቶክ ላይ።….
ESAT brings Aba Mela as a political analyst“ስለ አንድ ሰው ስንጽፍና ስንናገር ቢቻል አዎንታዊና መልካም ከሆኑ ነገሮች መጀመር ጥሩ ነው” ይሉ ነበር “የኔታ” በሚል ቅጽል ስም እንጠራቸው የነበሩ የዘጠናኛ ክፍል የአማርኛ አስተማሪያችን። ቀጭንና የዋህነት የተላበሰ ፊታቸው ላይ ችፍ ብሎ የማርክስን ግርማ ሞገስ ያጎናጸፋቸውን ገብስማ ሪዝ በእጃቸው እየዳበሱ ያስተማሩኝ ትዝ አለኝ።
ነገሩ የድሮ ትምህርት ቢሆንም የተማርኩትን በማሰብ እንደ አዞ ደንዳና ቆዳ ስለ ታደለው ብርሃኑ ዳምጤ ለመጻፍ ስነሳ ከልቅ አፉ ባሻገር ከማደንቅለት ባህሪው ብጀምር መልካም ነው ብዬ አሰብኩ።
ማንም በቀላሉ ሊክደው የማይችለው ሃቅ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) የፍቅር ሰው ነው። ብርሃኑ ለፍቅር ሲል ብዙ መስዋእትነት ከመክፈል አልፎ በስደት ዘመኑ ሳይቀር እንደ ዘላን ብዙ ተንከራቷል። የሚገርመው ነፍስ ካወቀ ጀምሮ እስካሁን ያፈቀረው አንድ ብቻ ነው። ለፍቅረኛው ሲልም ብዙ ተሰቃይቷል፣ ወደ ፊትም መሰቃየቱ አይቀሬ መሆኑን ለመተንበይ ቀላል ነው።
ታዲያ ብርሃኑ “ሆዴ! ያላንቺ ማን አለኝ!” እያለ በፍቅር የሚያቆላምጣት አይኗ የሚያማልሉ፣ አፍንጫዋ ሰልካካ፣ ጸጉሯ የሃር ነዶ የሚመስሉ የቆንጆ ቆንጆ የሆነች ኮረዳ እንዳትመስላችሁ። በተቃራኒው፣ አፍንጫም፣ አይንም የሌላት ትልቅና ወደፊት የተገፋ ጆንያ የሚመስል ግንባር ብቻ ያላት መሆኗን ጠንቅቆ ያውቃል። ያለባት አንድ ትልቅ ችግር የመኖ ነገር አይሆንላትም። በቀላሉ አትጠረቃም። ቢሆንም ነፍሱ እስኪወጣ ይወዳታል።
በፍቅር “ሆዴ! ሆዴ! ” የሚላትም ሌላ ሳትሆን በስተርጅና አክሮባት የምታሰራው ሆዱን ነው።
“ሆድ፣ ሆዴ! ያላንቺ ማን አለኝ!” እያለ ዘውትር በፍቀር የሚዳብሳት ፍቅረኛ። የሚያቃጥል ፣ የሚያንቀዠቅዥ፣ ህሊና የሚያስት ፣የሚያክለበልብ፣ ቀልብ የሚያሳጣ ከሁሉም በላይ የሚያዋርድ የሆድ ፍቅር ቢባል ማጋነን እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ።
የታደለ ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለሰላም መስዋእትነት ሲከፍል፣ በየእስር ቤቱ ሲሰቃይ የቁብና የእድር ዳኛ ለመሆን ብቃት የሌለው አጭቤ ግን በሆድ ፍቅር ተቃጥሎ የሆድ ማንዴላ ሆኖ እንደ ረከሰ ሴተኛ አዳሪ በየአደባባዩ ከንቱ ስብእናውን በስሙኒ እየቸረቸር ለከፈሉት ሁሉ እየደነሰ ይኖራል። ኑሮ ካሉት…መሆኑ ነው።
ታዲያ ሰሞኑን ከተቃዋሚ ጎራ አመለጥኩ እያለ እያለከለከ ቤን (ሆድፈርስት) እና ሰለሞን ቅንድቡ በተባሉ እርካሽ የሆድ ውጠራ የትግል አጋሮቹ በኩል የለመደውን ቱሪናፋ ሲቸረችር አያቴን አስታወሰኝ። አፈሩ ይቅለላትና አያቴ የአባ መላ አይንቱን የመለፍለፍ ልክፍት ያለበትን ቅል ስታይ “አሻሮ የበላ አሻሮ ያገሳል” ነበር የምትለው።
እውነት ለመናገር ነገሩ ሁሉ ብርሃኑ መኖ ፍለጋ መጣ መኖ ፍለጋ ተመለሰ ወይንም ተገለባበጠ መሆኑን ስለምናውቅ እራሱን ማግዘፍ ያልተሳካለት ምስኪን ሆድ ወዳድ ምን ቢናገር ሊያስከፋን አይችልም። በነገራችን ላይ አባ መላ የሚለው ስም ስለሚያንስበት ከዚህ በኋላ አባ በላ በሚል የማእረግ እድገት እዲሰጠው ፍቃዳችሁ ይሁን።
አንድ ምስክር እንዳለው አባ በላ መብላት የሚያቆመው ሲጠግብ ሳይሆን ሲደክመው ብቻ ነው። ታዲያ አባ በላ በመፈረካከስ ላይ ካለው ከወያኔ መንደር አምልጬ መጣሁ ብሎ እያለከለ እንደመጣ መጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ የመኖ ነበር። “ይከፈለኝ” አለ። ለከፋዮቹ ችግር የሆነው ምን ሰርቶ ምን እንደሚከፈለው ማጣራት ነበር። ከፓርክንግ ሎት ምንተፋ ባሻገር ሙያ የለው፣ ትምህርት የለው፣ እውቀት የለው፣ አመል የለው፣ ግብረገብ የሌው፣ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነበር።
የመጣው ባዶ እጁን ግን ደግሞ ትግስት የሌለው ቀዥቃዣ ቢሆንም “ሆደ ሰፊ” መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው። ይከፈለኝ ሚስጥር ይዤ መጥቻለሁ፣ የወያኔ ሰላዮች በአሜሪካና በአውሮፓ ስምዝርዝርና አድራሻ አለኝ አለ። በርግጥ ለዚህ ጠቃሚ መረጃ ክትፎ ምናምን ተገዝቶለት መረጃውም ለሚመለከታቸው የአሜሪካና አውሮፓ መንግስታት መመራቱን ሰምቻለሁ።
በኢሳት ላይ ካልወጣሁ፣ መድረክ ካልሰጣችሁኝ አለ። የሚገርመው ግን በኢሳት ላይ ቃለምልልስ ለማድረግ እንኳን ይከፈለኝ አለ። ኢሳቶችም ለዚህ አንከፍለም አሉት። ምንም እንኳን መጀመሪያ ይከፈለኝ ሲል የቀረበው በስካይፕ ቢሆንም ቢያንስ ለትራንስፖርት ይከፈለኝ አለ።። የሆድ ነገር፣ የሆድ ፍቀር፣ የሆድ ትግል ነው ነገሩ ሁሉ።
የተቃዋሚው ጎራ አስቸጋሪ ትግል እንጂ መኖና አረቄ እንደሌለው ሲገባው ነገሩ ሁሉ ሊጥመው አልቻለም። እርሱ ሃሳቡ ሁሉ በቀላሉ የማትረካውን ፍቅረኛውን “ሆዴን!” ሞልቶና ሸንግሎ ማሳደር ነው።
ያም ሆነ ይህ ስለ አባ በላ ብዙ መጻፍ አያስፈልግም። ጓዙን ጠቅልሎ፣ ሆዱን ታቅፎ እያለከለ በመጣበት መንገድ ሄዶ የድሮ ጌቶቹ እግር ስር እያለቀሰ ማሩኝ ቢልም እኛ ድምጹን ቀርጸን ስላስቀረን ይሂድ ተውት። ድሮም ቢሆን ጅብ በጨለማ እንጂ በብርሃን ኑሮ አይሳካለትም።
ያልተማረው ተንታኝ አባ በላ እንደ ጀብድ የሚቆጥረው ስራ ፈቶ ፓልቶክ ላይ ተጥዶ የቆጥ ያባጡን መቀባጠሩን ነው። ለማንኛውም አባ በላ መንግስት የለም ወያኔ አልቆለታል እያለ ከዘፈናቸው ዘፈኖች መሃል አለፍ አለፍ እያልን እናዳምጥ። ወጪት ሰባሪ የሆነው አባ በላ ጌቶቹን የሚያጋልጡ በርካታ ዘፈኖች ስለዘፈነ ቀስ በቀስ እያወጣን እንዝናናባቸዋለን። እነዚህን ከታች ለናሙና የመረጥኳቸውን የውስጥ አዋቂው የአባ በላን ንግግሮች (ዘፈኖች) በጥሞና ይከታተሉ።

ሃይለማሪያም ደሳለኝ “አብዩዝድ” ነው

Ethiopian PM Hailemariam Desalegn on Al Jazeeraሃይለማሪያምን ተዉት፣ እኔ ለሃይለማሪያም ማዘን ጀምሪያለሁ። እኔ እንደውም ከሳውዲ ከተመለሱት ሰዎች አንዱ ይመስለኛል። ምክንያቱም የት ጠፋ ይሄ ሰውዬ። በሳውዳአረዲያ ነበረ ማለት ነው። እና ሰሞኑን እንሰማለን ማለቴ ነው። አንዱ abused የሆነ ሰው ነው ማለቴ ነው። እርሱ እኮ ሰልፍ ሊወጣለት የሚገባው ሰው
ነው። ግን ጥሪ ለምን እንደማያቀርብ አይገባኝም። አለ አይደለም እንደዚህ abused እደረጋለሁ፣ እንደውም ማታ ማታም ሊገረፍ ይችላል። ምክንያቱም በጣም
ተደነባብሯል።
የሚያወራው ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። እርሱን ተዉት እንደ መሪም አትቁጠሩት። እሱ እንደ ሰው ህሊና ቢኖረው immediately resign ማድረግ
አለበት። እውነቴን ነው፣ ከልቤ ነው። መናቄ አይደለም። ምክንያቱም authority ሲባል de facto power ሊኖረው ይገባል። ዝምብሎ መቀለጃ ስትሆን፣ you have to resign። ብዙ ስራ አለ ለሱ የሚሆን። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የኮብል ስቶን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አለ። አንዱን ሊመራ ይችላል። በደቡብ የሚካሄደውን የኮብል ድንጋይ ምንጣፍ ቢከታተል ይሻለዋል። ምን አጨቃጨቀው ከነዚህ ሰዎች ጋር።

ሳሞራ ዘረኛ ነው
Samora Muhammad Yunis is the Chief of Staff of the Ethiopian National Defence Forcesአሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስትመለከት structurally እከሌ ሚኒስትር ነው ይሉሃል ምክትሉ ደግሞ ሌላ ሰው ነው። ዋነው ሰውዬ አይደለም አለቃው፣ ምክትሉ ነው አለቃው። እኔ በቅርብ ቦታውን አልጠቅስልህም የመከላከያ ሚኒስትሩ እዚህ መጥተው ነበር፣ ዋሺንግተን ዲሲ። አብሯቸው ኢታማዦር ሹሙ ሳሞራ ነበር።
የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ ያሉበት ዲነር ነው። ሌሎችም ባለስልጣኖች ነበሩ። እኔም ነበርኩ። ኢታማዦር ሹሙ መከላከያ ሚኒስቴሩን ይሰድበዋል፣ በዘሩ። ፈረጆች ባሉበት እኮ ነው። ቀለድኩ ነው የሚለው። እንዲህ አይነት ቀልድ አለ እንዴ። በወታደራዊ ስርአት ውስጥ መከላከያ ሚኒስቴር ማለት ትልቅ power ነው ያለው።
አንተ አስር አለቃ ሆነህ ሃምሳ አለቃው ሲመጣ ቆመህ ነው ሰላምታ የምተሰጠው… አንድ ኤታማዦር ሹም፣ምንም ልምድ የሌለው ጎሬላ ነው። በጣም ጨዋ ሰው
ነው መከላከያ ሚኒስቴሩ፣ እኔ ስለማውቀው ነው። በጣም ነው የተናደደው (አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ)። ደሞ እኮ አስተርጉሞ ለፈረንጆች ሊነግራቸው ይፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዘናዊ አሉ ብሎ ነው የሚያወራው። የዚህን ሰውዬ ብሄረሰብን እንደ ሌባ አድርጎ ነው ይሚቆጥረው።…እኔ እንደዛን ቀን ደሜ ፈልቶ አያውቅም።
ብዙ ሰዎችም የሚያውቁት በብዙ ነገር ነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱ መቼም የሚፋረደው እሱን (ሳሞራን) ነው። በመከላከያ ውስጥ የተጠላ ሰው ነው። ይሄንን ሰውዬ ሲያዋርደው ስታይ really በዚያን ለት ዲነሩ አንዳለ ነው የተበላሸው…። አንተ ሚኒስቴር ስለሆንክ አይደለም ዘበኛው (ህወሃት ከሆነ) ሊኒቅህ ይችላል።…አንድ ስርአት structural problem ካለብት ሚኒስቴሩን ሹፌር የሚያዘው ከሆነ…አሁን እዚህ ዋሺንግተን ኤምባሲ አንድ ሰለሞን የሚባል ሃያ አመት የሚያውደለድል አለ። ምን እንደሚሰራ አይታወቅም፣ ።።ሰላይ ነው ልጁ መሰለኝ…ሰላሳ አምባሳደር ይቀያየራል። እርሱን የሚነካው የለም። ሾፌር ነው መደበኛ ስራው። ግን he is powerful than the ambassador, even ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ የበለጠ። እንደዚህ አንደዚህ አይነት ሰዎች ናቸው እዚህ የሚመደቡት።….

አዜብ መስፍን አጭበርባሪ ናት

Azeb Mesfin, the wife of Meles Zenawiባክህ ተው አዜብ ምናምን ይለኛል። በሶስት መቶ ብር፣ በሁለት መቶ ብር ነው የምኖረው ምናምን ትላለች። ያልጠየቋትን ትለፈልፋለች። በሁለት መቶ ብር ነው እንዴ አሜሪካ በየግዜው የምትመጣው። ምን አይነት የምን ገንዘብ ነው? እኔ እሱ አይደለም፣ ስለሱ ችግር የለብኝም።…ይሄንን የሚገዛ ሰው ካለ ይግዛ stupid ሰው ካለ እንጂ አራት ሺ ብር ደሞዝተኛ የ100ሺ ብር ቦርሳ የምትገዛ ሴትዮ “አራት ሺ ብር ምናምን” ትላለች። በቃ ይሄው ነው።
First of all, የምትሰጣቸው ኮሜንቶች backfire የሚያደርግ ነው። መለስ መንጃ ፍቃድ የለውም፣ ባንክ አካውንት የለውም …ምን ማለት ነው? ቤተሰቡን take care የማያደርግ ፍጡር ምን አይነት መሪ ነው? እንዴት ነው መንጃ ፈቃድ የሌለው መሪ የሚኖረው በአለም ላይ?…እንዴት ነው ባንክ አካውንት የሌለው መሪ የሚኖረው? ይሄ irresponsibility ነው። ቤለሰብህን handle ማድረግ አለብህ…. መታወቂያ ሊኖርህ ይገባል። መታወቂያ የሌለው መሪ ነው እንዴ ሲመራ የነበረው። ምንድን ነው የሚያወሩት?…ስለገንዘብ የማያውቅ መሪ ነው?… እንዴት ነው ስለገንዘብ የማያውቅ ሰው ስለሃገር ኢኮኖሚ ሲወስን የነበርው? ይሄ ጥሩ ነገር አይደለም። ለማን ተይ እንዳላሏት አልገባኝም።
እሷ ገንዘብ የሚመስላት በቼክ የሚሰጥ ነው። How about የቤተ መንግስት ኦዲት የማይደረገው ገንዘብ…እማይወራረድ ገንዘብ አለ፣በሚሊዮን የሚቆጠር። ገንዘብ ሚኒስቴር የማያውቀው። እሱ ገንዘብ አልመሰላትም እንዴ?….How about ኤፈርት? የኤፈርት ስራ አስኪያጅ አይደለችም እንዴ?… ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገር ያመኛል። እንደዚህ አይነት childish የሆነ ፉገራ። እንደ ሃገር ደግሞ ሊያመን ይገባል።…አውቃለሁ የዚህ የዶክተር ጌታቸውም ጠበቃ እርሷ ነች። I know that, አጭበርባሪ ነች። የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ አድርባይነትን ተዋጉ ብሎናል ይሄ ሩም በአር ያነት እራሱን አስቀድሞ በአድር ባይነት ላይ ዘመቻ አውጇል።

የአቋም ለውጥ

ታዲያ ዛሬ አባ በላ ግርማ ብሩ አሞሌ ጨውና ብር ሲያሳየው እንደልማዱ ከሻቢያ አምልጨ ተመለስኩ እያለ ልፈፋ ጀመረ። አይ አባ በላ! በኢሳት ላይ በግንባር ሲቀርብ ሲሳይ አጌና “ከወያኔ ካምፕ ምን አስወጣህ?” ብሎ ሲጠይቀው ደረቱን ነፋ አድርጎ “ህሊናዬ እንቅልፍ ነሳኝ” አለ።
በረጅም አረፍተ ነገርም እንዲህም አለ፣ “በየግዜው የምናያቸው ነገሮች እየተሻሻሉ መምጣትን ሳይሆን እጅግ በሚያሳዝን ሁናቴ በአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ በተለይ ዲሞክራሲን ፍትህን፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ህሊናህ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እየሆነ ሲመጣ ፣አገሪቱ የጥቂቶች ሆና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ባእድ ሆነው፣ ወጣቶች ሌት ተቀን ከዛች አገር እግራችን ይውጣ በሚል አገራቸውን እስከሚጠሉበት፣ ሴት እህቶቻችን በየአረብ አገሩ በሚሸጡበት፣ ጋዜጠኞች በመጻፋቸው እድሜ ልክ በሚፈረድበት፣ የኑሮ ውድነት በአለም ደረጃ ፍጹም ልትሸከመው በማትችል ደረጃ፣ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ውስጥ የመንግስት ሰራተኛ እንዴት አድርጎ እንደሚኖር ሁሉ የማያውቅበት ሁናቴ ሲፈጠር ያንን ጉዳይ እንዲታረም ባለን ‘አክሴስ’ ሃላፊዎቹን ሁሉ እንትን ማድረግ እንሞክር ነበር።….ስር አቱ እርስበርስ መናበብም አልቻለም።….በጣም እሮሮ ያለብት ስርአት በመሆኑ ከዚህ መንግስት ጋር ሆነህ ለማስተካከል የምታደርገው ጥረት ዝም ብሎ ግዜ ማጥፋት ስለሚሆን እንደውም በሚሰራው ስተትና ወንጀል ላይ ታሪካዊ ሃላፊነት ይኖራል የሚል እንትን ስላለኝ ካለብኝ የዜግነትና የሞራል ጉዳይ አንጻር ጥያቄው አገር የማስቀደም፣ ህዝብን የማስቀደም ጉዳይ ስልሆነና የግል ጉዳይ ስላልሆነ የግዴታ ይህንን ስርአት በማንኛው መልክ ለማስተካከል ወይንም ለመለወጥ ከሚታገሉ ጎራ ዲሞክራሲያዊ ሃይል ጋር አብሮ መስራቱ ለአገር ይጠቅማል የሚል እምነት ላይ ደርሻለሁ። እና አሁን ሲሪየስ አቋም ነው ያለኝ።….”
“መቼም ይሄ በረጅሙ “በጄጄጄ!” የሚያስብል ጉዳይ ቢሆንም አያቴ “ጦጣ መንና ጫካ ገባች” የምትለው ተረቷን አስታወሰኝ።
አባ በላም ዝም ብሎ ህሊናዬ እንቅልፍ ነሳኝ የሚል ጨዋታ ጀመረ እንጂ አፈጣጠሩ ለህሊና ሳይሆን ለሆድ ስለሆነ ብዙ በአደባባይ መለፍለፉን ትቶ ሆዱን እየጠቀጠቀ ቢኖር ይመረጣል። እኔን ከአባ በላ በላይ የሚያሳዝኑኝ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ እርኩስ ጥንባቸውን ያወጣ ሆድ አደር ድጋሚ መቀጠራቸው ነው። ሳሞራ ዘረኛ፣ ሃይለማሪያም እርባና ቢስ አሻንጉሊት፣ አዜብ አጭበርባሪና ሙሰኛ፣ ስብሃት ሰካራምና ሴሰኛ፣ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ሌባ፣አባይ ወልዱን መሃይም፣ ቴድሮስ አድሃኖም ህጻንና እንጭጭ፣ ሽመልስ ከማል የማይረባ አድርባይ፣ አባ ዱላ ላንቲካ፣ ግርማ ብሩ እግር አጣቢ፣ በረከት ሴሰኛ….እያለ ፓልቶክ ላይ እንዳልጨፈጨፋቸው ዛሬ ሻቢያን ለመዋጋት ተመልሼ መጣሁ እያለ ያጃጅላቸዋል።…
አባ በላ ጠመዝማዛ መንገድ በከንቱ ተጓዘ እንጂ እውነታው እንዲህ ነው። የእርሱ ፍቅር እስከ መቃብር እንደነ ሰብለወንጌል የፍቅር ታሪክ የሚያማልል አይደለም። አባ በላ የሚያፈቅረው አብሮት የተወለደውን ሆድ ስለሆነ ጥቂት ቆይቶ አብሮት ይቀበራር። እኛም የሆድ ፍቅር እስከ መቃብር የሚለውን ታሪኩን ጽፈን የቀብሩ ስነስርአት ላይ እናስነብብለታለን። ምስኪን የሆድ አርበኛ! ስለ ህሊና ሳትናገር ዝም ብለህ የሰጡህን መኖ ጠቅጥቅ። መልካም መኖ ይሁንልህ ብለናል!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11482/

Monday, March 17, 2014

ድረስ ለፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ተወቃሾቹ የኦሮሞ ሕዝብና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ብቻ ነውን እንዴ?!



‹‹ዕርቅና ሰላም የሕይወት ቅመም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደውለታ ቢስ ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ የሚሆን መልስ እነሆ!›› በሚል ርእስ የጻፉትን ጦማር እጅግ የማክበርዎና ኢትዮጵያዊው የምሆን ወንድምዎ ደጋግሜ አነብበኩት፡፡ ፕሮፌሰር በትክክል ተረድቼዎት ከሆነ እርስዎ በጽሑፍዎ ለማስተላለፍ የፈለጉት ዋንኛ መልእክትዎ፣ አንድም ‹‹ዕርቅንና ሰላም መስበክ›› ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ጠላት ወይም ውለታ ቢስ አድርገው ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ መልስ ይሆናል በሚል እነሆ ያሉት ጦማር እንደሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ለረጅም ዓመት ካካበቱት ዕውቀትዎ፣ በትምህርት ዓለም በሥራ፣ በምርምርና ጥናትዎ ከሕይወት ተሞክሮዎና ልምድዎ በመነሳትና እንዲሁም ዕድሜዎን ሙሉ ከመረመሯቸውና በአካዳሚያው ዓለም አንቱ ከተሰኙባቸው፣ ከበሬታን ካተረፉባቸውና ጥንታዊ የኾኑ መዛግብቶቻችንን በመመርመር እስካሁን ድረስ እያካፈሉን ስላለው ሰፊ የሆነ እውቀትዎ ከምስጋና ጋር ዝቅ ብዬ እጅ እነሳለሁ፡፡ ከገለታዬ አስከትዬ ግን በተለያዩ ድረ ገጾች ከሰሞኑን ባስነበቡን ጽሑፍዎ ማዘኔን ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡
ይህ ጽሑፍዎ ከዕርቅና ሰላም ይልቅ ጠብንና ኹከትን፣ ከፍቅርና አንድነት ይልቅ መለያየትን የሚዘራ መስሎ ነው የታየኝ፡፡ መቼም ለእንደ እርስዎ ዓይነት ዘመኑን ሙሉ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሲመረምር ለነበረ ሊቅ/ምሁር ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን  ታሪከ ማስረዳት ‹‹ለቀባሪው አረዱት›› አሊያም ደግሞ ‹‹ልጅ ለአናቷ ምጥ አስተማረች›› እንዳይሆንብኝ እሠጋለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ፕሮፌሰር በዚህ ጽሑፍዎ ለዕርቅና ሰላም ይሆናል ብለው ባቀረቧቸው መፍትሔዎች ዙሪያ ጥቂት ሙግቶችን እንዳቀርብልዎ አስገድዶኛል፡
በሙያዬ የታሪክ ተመራማሪ፣ የአርኮዮሊጂና የቅርስ ባለሙያ ነኝ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድም ጥንታዊትና ሐዋርያዊት በምትሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ካሉ ሊቃውንት አባቶቼ እግር ስር ከማያልቀው ዕውቀት ምንጫቸው እጅግ በጥቂቱ ለመጥለቅ ሞክሬያለኹ፤ እስከ ሕይወት ፍጻሜዬም ከእነዚህ አባቶቼ የማያልቀውን ሰማያዊ ዕውቀታቸውንና ጥበባቸውን መጥለቄን እቀጥላለኹ ብዬ አስባለኹ፡፡ እናም ክቡር ፕሮፌሰር በአንዲት ቤ/ን ጥላ ስር መገኘታችንና ሁለታችንም የኢትዮጵያን ረጅም ዘመናት ታሪክ፣ የሕዝቦቿን ገናና ሥልጣኔ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶቿን ለመመርመር ምንተጋ ከመሆናችን የተነሣ በዚህ ጦማሬ ቋንቋ ለቋንቋ፣ አሳብ ለአሳብ እንግባባለን ብዬ እገምታለኹ፡፡
ፕሮፌሰር ‹‹ዕርቅና ሰላም ለሕይወት ቅመም›› ብለው የጻፉት ጽሑፍዎ እንደሚመስለኝ መነሻ ያደረገው ባለፈው ሰሞን በአሜሪካ ሚቺጋን ስቴት የሚኖረው ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ ጀዋር መሐመድ፣ አንዳንድ በውጭ አገርና በኢትዮጵያ ያሉ የኦሮሞ ልሂቃንና የብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ ዳግመኛ እንደ አዲስ በሰፊው መከራከሪያ ሆኖ በዘለቀው የኦሮሞ ታሪክ ትንታኔ፣ የሕዝቡ የነጻነት ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለአቢሲኒያ/ለነፍጠኛ ገዢዎች ቅኝ ግዛት ዘመቻ ዋንኛዋ አጋር ነበረች በሚሉትና በመሳሰሉት ታሪካዊና ፖለቲካዊ ትኩሳቶች ዙሪያ ሲንሸራሸሩ የነበሩና አሁንም ያሉ አሳቦች ይመስሉኛል፡፡
እርስዎም በዚህ ክርክር መነሻነት ተስበው ይመስለኛል ለዕርቅና ለሰላም መፍትሔ ይሆናል ባሉት ጽሑፍዎ የኦሮሞ ሕዝብ አውዳሚ፣ አረመኔና ጨካኝ እንደሆነ የነገሩን፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹ጋዳ›› የሚለው ሥርዓት አንዳንዶች እንደሚሉት አፍሪካ በቀል የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሣይሆን ሕግ አልባ፣ በጭፍን የሚጓዝ የማፊያዎች ጥርቅም እንደሆነም አስረግጠው ነገሩን፡፡ እነ ጃዋርና ተከታዮቻቸውም በሸሪያ ሕግ ሊገዙንና ሊዳኙን እያቆበቆቡ ያሉ ጠባብ ብሔርተኞች፣ የኢትዮጵዊነት/የአንድነት መንፈስ ነቀርሳና የሰይጣን መልእክተኛ ናቸው ሲሉም ፈረጇቸው፡፡
አስከትለውም የኦሮሞ ሕዝብና ኢትዮጵውያን ሙስሊሞችም አባቶቻቸው በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስና ሥልጣኔ ላይ ላደረሱት ውድመትና ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባቸው ለማሳሰብ ሞከሩ፡፡
ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጭካኔና አረመኔነትም ከአገር ውስጥ ካሉ ጸሐፊዎች እስከ ውጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች ድረስ የመሰከሩት ስለሆነ፣ ‹‹ጩኸቴን ቀሙኝ›› አሊያም ‹‹ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮኻል›› እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ኦሮሞዎች በኢትዮጵያና በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ላደረሱት አሰቃቂ ግፍና በደል፣ እንዲሁም ወደ አንድነትና ኅብረት እንዲመጡ ላደረጓቸው ንጉሥ ምኒልክ በሀውልታቸው ስር የይቅርታ ጉንጉን አበባ በማኖር ዕርቀ ሰላም እንዲያወርዱና ለባለውለታቸው ለምድራቸው/ለአፈራቸው ልጅ ለጎበና ዳጬም ሀውልት እንዲያቆሙላቸው ምክርዎን ለግሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸውን ያህል ታላቅ ምሁርና ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ የመረመሩ ሰው እንዴት የኦሮሞ ሕዝብንና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ብቻ ነጥለው በአገሪቱ ላይ ለደረሰው ውድመትና ጥፋት ተወቃሽና ይቅርታ ጠያቂዎች እንዳደረጓቸው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ መቼም ፕሮፌሰር ኢትዮጵያ በምትባል ግዛት ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ሕዝቦች በተለያዩ ዘመናት ባደረጉት ጦርነትና የግዛት ማስፋፋት ወረራ የየበኩላቸውን ጥፋትና ውድመት እንዳደረሱ ይስቱታል ብዬ አልገምትም፡፡
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ታሪካችን ዘመን፣ በታሪክ ምሁራን ዘንድ ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› ተብሎ በሚጠራው ዘመን በአማራነት ስም የሚጠሩ ገዢዎች፣ መሳፍንትና መኳንንት፣ የጎንደሩ በወሎ፣ የጎጃሙ በሸዋ፣ በትግራይ የእንደርታው፣ በአጋሜ፣ የአድዋው በአክሱም፣ በኦሮሞው ግዛትም የአርሲ፣ የባሌ፣ የሸዋና ወለጋ እያለ እርስ በርሱ እንዳልተላለቀና የአገሪቱን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች እንዳልዳረጉ ለምን የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ነጥለው ወራሪ፣ አውዳሚና ብቻ አድርገው እንደሳሉት በእጅጉ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን የሚያስተዛዝብም ጭምር ነው፡፡
ፕሮፌሰር በእንዲህ ዓይነት የአንድ ወገን ብቻ የታሪክ አተያይና ትንታኔና እንዲሁም ፍረጃ ዕርቅንና ሰላምን ማውረድ ይቻላል ብለው አስበው ከሆነ ይህንን ጽሑፍ እንካችሁ ያሉት ትክክል አይመስለኝም፡፡ በእኔ እሳቤ በአብዛኛው በአገራችን ታሪክ አንድን ብሔር ወይም ሕዝብ ሆን ብሎ ለማጥፋት ወይም ለመፍጀት የተደረጉ ዘመቻዎች ነበሩ ብዬ ለመውሰድ እቸገራለኹ፡፡ አብዛኛው የታሪካችን ገጽ የሚሳየን
ገዢዎች ለሥልጣን፣ በገብርልኝ አልገብርህም ሰበብ የኢኮኖሚ ጥቅምንና የፖለቲካ የበላይነትን ለመውሰድ በነበረ ውድድርና ፍጥጫ በተደረጉ ጦርነቶችና ወረራዎች ብዙዎች ምስኪኖች አምነውበትም ሆነ ሳያምኑበት ጭዳ እንደሆኑ ነው የማስበው፡፡
በተመሳሳይም በአገራችን በአብዛኛው በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ተደረጉ ጦርነቶች ውስጥም ቢሆን ሃይማኖት መሳሪያ ወይም ሽፋን እንጂ ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው በተነሱ ተፋላሚዎች የተደረጉት ጦርነቶች ዋና ምክንያት አልነበረም፡፡ ሃይማኖት ሽፋን ነው፡፡ ጠቡና መሠረታዊው ቅራኔ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንመራሃለን ወይም እናስተዳድርሃለን በሚሉት ገዢ መደቦች የሚነሳ የሥልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ጥያቄ ነበር፣ ነውም፡፡
እናም የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በበጎም ሆነ በክፉ ጎኑ የሚነሳበት ታሪክ ያለው ሕዝብ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ ፕሮፌሰር የኦሮሞ ሕዝብን ብቻ ነጥለው አውዳሚና የጥፋት ልጅ እንደሆነ በጻፉበት ብዕራቸውና ለዚህም መከራከሪያቸው ከጠቀሷቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጸሐፍት መካከል ለምን እነዚሁ ጸሐፊዎች በአንጻሩ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደልና ግፍ በተመለከተ የተዉትን ምስክርነታቸውን ለመጥቀስ/ለመጻፍ እንዳልደፈሩ ግን ግልጽ አይደለም፡፡
እስቲ ለአብነት ያህል አፅሜ ጊዮርጊስ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› በሚል በተዉልን የታሪክ ማስታወሻቸው ዐፄ ምኒልክና ሠራዊታቸው በኦሮሚያና በደቡብ የአገራችን ክፍሎች ባደረጉት የማቅናት ዘመቻ ወቅት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ስለደረሰው በደልና ግፍ የከተቡትን በጥቂቱ እንመልከት፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ኦሮሞ ሁሉ ተገዛ፣ በአማራ ሕግና ሥርዓት ሔደ፣ ካህናቱ አንድ ኦሮሞ አስተምረው አላጠመቁም፡፡ ይልቅስ ተፊተኛው ቂም የበለጠ ቂም በልቡ አኑረውበት መሬቱን በቀላድ ወሰዱበት፡፡ አንድ ቀላድ የቅስና አንድ ቀላድ የአወዳሽ እያሉ በዚሁ ስብከት ንጉሡን አሳመኑ፡፡ ስለ መንግሥት ያሰቡ መስለው ለንጉሡም አንድ ቀላድ፣ ለወታደር አንድ ቀላድ … መሬቱን ተካፍለው ኦሮሞን እንደ ባሪያ አድርገው ይገዙታል
እንጂ የክርስቶስን መንገድ አላሳዩትም፡፡ እነርሱም የእግዝሔርን መንገድ በሚገባ አልተማሩም፣ አስተማሪም ቢመጣም ይከለክላሉ …፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው የኦሮሞ ወራሪ ኃይል በአማራውና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል ዘርዝረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል ባሉበት ብዕራቸው ለምን ይህንም የኦሮሞ ሕዝብን በደል ወይም የታሪካችንን ሌላውን ገጽ ቦታ አንዳልሰጡት፣ ሊያነሡት ወይም ሊነግሩን እንዳልደፈሩ ግልጽ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰሩ መልእክቴ በኢትዮጵያ ምድር ዕርቅና ሰላም ለማውረድ ነው ካሉን ዘንድ ሚዛናዊ በመሆን አንዱን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የታሪካችንን ገጽ ሊያሳዩን በተገባቸው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የአንድ ወገን ብቻ የሆነ የታሪክ ትንታኔና ዕይታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዴየትኛው የጥፋት መንገድ ይዞን እንደነጎደ በተግባርም ጭምር ዐይተነዋል፡፡
በሌላም በኩል እስቲ እስካሁንም ድረስ ሳስበው ግርም የሚለኝን ከዚሁ ካነሳሁት ርእሰ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ አንድ ገጠመኜን እዚህ ላይ ጨምሬ ለማንሳት እወዳለኹ፡፡ ታሪኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርንበት ሰዓት የኾነ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው ካሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ዘንድ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጥላ ስር አብረን ያለን ጓደኛዬ በአንድ ወቅት ‹‹ራእይ ማርያም›› ከሚል የጸሎት መጽሐፍ ኮፒ የተደረገ ጽሑፍ ከአንድ ከሌላ ኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጓደኛው ጋር ይዞ በመምጣት እንዲህ አለኝ፡፡
‹‹ይቅርታ፣ ከልቤ አዝናለሁ … በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን ክቡር ደም ፈሳሽነት/ቤዛነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ፣ ሰማያዊ ዜጋ ሆነን የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርሳለን ብላ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሕዝቦችን የሚለያይና የሚከፋፍል መጽሐፍ መኖሩን እስከዛሬ አላውቅም ነበር፡፡›› በጓደኛዬ ንግግር ውስጥ እልክና ብርቱ የሆነ አንዳንች የቁጭት መንፈስ ነበር የሚነበብበት፡፡ ‹‹… ለመሆኑ ይህን መጽሐፍ አይተኸው ወይም አንብበኸው ታውቃለህ በማለት ‹‹የራእይ ማርያም›› መጽሐፍን አንድ ገጽ ኮፒ እንዳነበው በእጄ ሰጠኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
… ከስር እስከ ጫፍ፣ ከጫፍ እስከ ስር ድረስ በአምስት ሺሕ ዓመት የማይደረስበት ትልቅ ገደል አሳየኝ፡፡ ያንዱ ነፍስ በአንዱ ላይ ሲወድቅ ዐየኹ፡፡ እኔም ምንድናቸው ብዬ ልጄን
(ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ኢየሱስን መኾኑን ልብ ይሏል) ጠየቅኹት፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት፡- … አራስ፣ መርገም፣ ደንቆሮ፣ ‹‹እስላም››፣ ‹‹ጋላ››፣ ‹‹ሻንቅላ››፣ ‹‹ፈላሻ›› ጋር የተኙ፣ ፈረስ፣ አህያ፣ ግመል በግብረ ስጋ የሚገናኙ፣ ወንዱም ግብረ ሰዶም ወገሞራ የሚዳረጉ… እነዚህ ሁሉ ኩነኔያቸው ይህ ነው አለኝ …፡፡
በጊዜው ይህን ጉድ ካነበብኩ በኋላ እንዲህ ዓይነቱን ክፋትና እርግማን የሞላበት መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያኒቱንና እውነተኞቹን የወንጌል መምህራን የሆኑትን አባቶቻችንን እንደማይወክል ባውቅም ይህ የጸሎት መጽሐፍ ተብዬ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ታትሟልና በጊዜው የመከራከሪያ አሳብም ሆነ የምሰጠው ምላሽ አልነበረኝም፡፡ ግና ስለ ስለዚሁ የጸሎት መጽሐፍ የኩነኔ ፍርድ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ያህል፤ መቼም ሌላ ስምና መልክ እስካልተሰጠው ድረስ በመንፈሳዊው ዓለም አስተምህሮ/ሕግ ካልተፈቀደልንና የእኛ ከሆነችው ሴትም ኾነ ወንድ ውጭ መሔድ ዝሙት ነው፡፡
‹‹ከጋላ›› ወይም ‹‹ከሻንቅላ›› ‹‹ከእስላም›› ወይም ‹‹ከፈላሻ›› ጋር ስለተኛን ወይም ስለዘሞትን የተለየ ነገር ሊሆንም ሊደርስም አይችልም፣ በአምስት ሺሕ ዘመንን በሚያስኬድ ገደል ውስጥም ልንጣልም አንችልም፡፡ ደግሞስ ምን ዓይነት ሕሊና ያለው ሰው ነው ሰውንና እንሰሳን በእኩል ሚዛን አስቀምጦ ፈረስም ተገናኘህ ‹‹ሻንቅላ›› ወይም ‹‹ፈላሻ›› ምንም ልዩነት የለውም ያው ነው በሚል የሚጽፍ፡፡
አንድን ጎሳና ብሔር ለይቶ ከእነርሱ ጋር ከተኛህ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ይደርስብሃል/ያገኝሃል ብሎ እንዲህ ዓይነቱን መርገምን፣ ጥላቻንና ክፋትን የተሸከመ ድርሳን ቅድስት፣ ንፅሕትና ርትዕት በኾነች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም አሳትሞ በማቅረብ፣ ‹‹ፈላሻነቱንም›› ኾነ ‹‹ሻንቅላነቱን›› ወዶና ፈቅዶ ባላመጣው ሰው ሕሊና ውስጥ የጥላቻ መርዝ እንዲረጭና ልቦናው ክፉኛ እንዲቆስል ምክንያት ኾኗል፡፡
ይህ ትናንትና እንደ ዘበትና ቀልድ ያየነውና በጊዜው በይቅርታ መፍትሔ ያላበጀንለት ነገር ይኸው ዛሬ ከታሪካችን ማኅደር እየተመዠረጠ የብዙዎችን ቁስል እያመረቀዘ ቤተ ክርስቲያኒቱንም ኾነ ተከታዮቿን በጥላቻ ዓይን እንዲታዩ ምክንያት ከኾነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ታሪኮችን ዕድሉ ያጋጠመን ሁሉ ደጋግመን ሰምተናቸዋል፡፡ መፍትሔው ምን ይሁን፣ ምን መላ እንፍጠር ከማለት ይልቅ
ያለፈ ታሪክን ማንሳት ምን ይጠቅማል በሚል በማድበስበስ የተውናቸው ክስተቶች እያመረቀዙ በመካከላችን መፈራራትንና ጥላቻን አነገሡብን/አባባሱብን እንጂ መፍትሔ አልሆኑንም፡፡
ብዙዎቻችንን እያከራከረን ስላለው የትናንትና ታሪካችን ርእሰ ጉዳይ ስንመለስም አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል፤ ይኸውም አብዛኛው የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ በጦርነትና በወረራ፣ በገብር አልገብርም፣ በልግዛህ አልገዛም በተደረገ ግብግብና ጭፍጨፋ በደም የቀላ ታሪክ ነው ያለን መሆኑን፡፡
አንዱ የገዢ መደብ ሌላውን፣ ክርስቲያኑ ሙስሊሙን፣ ሙስሊሙ ክርስቲያኑን ያጠቃበት የጨፈጨፈበት በርካታ ዘመናቶች የታሪካችን አካል ኾነው አብረውን አሉ፡፡ አንዱ አገር የሌላውን አገር በጦርነት በመግጠም ሀብት ንብረቱን በመዝረፍ፣ መሬቱን በመቀማት፣ በምርኮና በባርነት በማጋዝ ያሳለፍናቸው የታሪካችን ቁስሎች በፍቅር ዘይት ለስልሰውና በዕርቀ ሰላም ፈውስ አግኝተው መፍትሔ ካላገኘን አንድ ብሔርን/ሕዝብን ወይም ሃይማኖትን ብቻ ነጥሎ እንደ ጥፋተኛና አውዳሚ አድርጎ ማቅረብ ወደምንናፍቀው የዕርቅና የሰላም ምንገድ ያመጣናል ብዬ አላስብም፡፡
ደግሞስ አማራው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከትግሬ፣ ወላይታው፣ ከጉራጌው፣ ሐረሪው፣ ከአፋር በደም፣ በአጥንት በተዛመደ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በጋራ ታሪክ  በተሳሰረ ሕዝብ መካከል ብሔርና ጎሳ ለይይቶ መወቃቀሱ ጥቅሙ ምንድን ነው፡፡ ትርፉስ ለማን ነው?! በእርግጥም ለእውነተኛው ዕርቀ ሰላም ቀናውን መንገድ ካላመቻቸን ላለፉት ሃያ ዓመታት ታሪክንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው እየተካሔዱ ያሉ የቂም በቀል ዘመቻዎች ፍፃሜያቸው እጅግ አስፈሪና አሳፋሪ እንደኾኑ ነው የታዘብነው፡፡
በሃይማኖትና በብሔርተኝነት ስም በአዲስ አበባና በሌሎች ክልል ከተሞች ቦግ እልም እያለ ያለውና ተዳፈኖ ያለው የረመጥ እሳት ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ መፍትሔ ካላበጀንለት (ያው እስከ ዛሬ ድረስ በአርባ ጉጉ፣ በበደኖ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በወተር፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ፣ በጅማ … የደረሰው አሰቃቂ እልቂት፣ ጥፋትና ውድመት ሳይዘነጋ) ይህ ዓለም ሁሉ የሚያደንቀውና የምንኮራበት፣
በቋፍ ያለው ለዘመናት አብረን በፍቅርና በወዳጅነት የቆየንበት አኩሪ ታሪካችን በነበር ልናወሳ የምንገደድባቸው ጊዜያቶች ሩቅ ሊኾኑ እንደማይችሉ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ያለፈው ሰሞን የእነ ጃዋር መሐመድና የኦሮሞ ወንድሞቻችን ኦሮሞነትን ከኢትዮጵያዊነት ነጥለው ያቀረቡበት ትርክትና የትናንትና ክፉ የታሪክ ጠባሳችን፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸውና እያንጸባረቁት ያለው ቁጣ፣ ቅያሜና ዛቻ የነገይቱ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱስ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለን እንድንጠይቅ፣ እንድንሰጋ ያስገድደናል ብዬ ለማለት እደፍራለኹ፡፡
አገሪቱን እያሥተዳደረ ያለው መንግሥትም ለጉዳዩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ያለ ቅጥ ያራገበው የብሔር ፖለቲካ ወላፈኑ እራሱንም ጭምር እየለበለበው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› በሚል ግትርነትና ዕድሜዬን ያራዝምልኛል በሚል እንዲሁ በአገም ጠቀም የተወው የጎሰኝነት/የዘረኝነት ጉዳይ ነገ መዘዙ ከየት እስከ የት ሊመዘዝ እንደሚችል መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ትናንትና በሆነው በሚያኮራው ታሪካችን ተከባብረንና ተዋደን፣ አሳፋሪና ክፉ ጠባሳ የተዉብንን የታሪካችንን ምዕራፍ ደግሞ በይቅርታ ዘግተን በፍቅርና በመቀባበል መኖር ካልተቻለን የሚጠብቀን ዕድል ጥላቻ፣ መከፋፋት፣ ጠላትነት፣ መለያየት … ብቻ ነው ሚሆነው፡፡
ይህ እንዳይሆንብን፣ ይህ ክፉ ነገር እንዳይደርስብን ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያሉ የዕድሜ ባለፀጋዎችና ምሁራን፣ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራኖቻችንና የፖለቲካ መሪዎችም ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት የሚመጡበትን ቀና የሆነ መንገድ በማመቻቸት አገሪቷን ከተደቀነባትና ካዣንበባት ጥፋት ሊታደጓት የትውልዱንም ልብ በፍቅር ዘይት አልስልሰው ለይቅርታ/ለዕርቀ ሰላም ሊያዘጋጁት ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ከእኔ ይበልጥ ከእኔ ይበልጥ የፉክክር መንፈስ ወጥተው ለአገርና ለሕዝብ የሚሆን የዕርቀ ሰላም መልእክት ይዘውልን ሊመጡ ይገባቸዋል፡፡
ነገሥታትን/መንግሥታትንና ክፉ መሪዎችን በመገሠጽ፣ በሕዝቦች መካከል ፍቅርንና ሰላምን፣ በአገራችንም ብሔራዊ ዕርቅን በማስፈን ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውንና መንፈሳዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ጊዜው አሁን ነው፡፡ አሊያ ግን ዕርቅንና ሰላምን ያወርዳሉ ያልናቸው አባቶቻችንም እርስ በርሳቸው ተለያይተውና ተወጋግዘው፣ ለነገ ህልውናችን በሚል ሰበብ የፖለቲከኞችን ጉያ የሚመርጡ ከሆኑ፣ ከእውነትና ከፍትሕ ጎን ለመቆም መንፈሳዊ ድፍረትና ወኔ ከተለያቸው እንዴት ባለ መንገድ ነው ፍቅርንና ዕርቅን ሰብከው አገሪቱንም ሆነ ትውልዱን ከጥፋትና ከሞት መንገድ ሊታደጉት የሚችሉት?!
በታሪካችን ለኾኑት ስህተቶች በግልፅ ይቅርታ ተጠያይቀን ዕርቅ ማውድ ካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚሻለው መነጋገርና መግባባት ነው፡፡ እንደ እውነቱም ከኾነ ትናንትና ለኾነው በደል እውቅና መስጠት ሳይቻል ዕርቅ ዕርቅ የሚለው ነገር ከጉንጭ አልፋ ወሬነት የሚያልፍ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ ዛሬ እንደገና ከበርካታ ዓመታትም በኋላ ተመልሶ እነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የምኒልክ ጦር በአያቶቻችን ላይ ያደረሰውን በደል አንረሳውም ወደሚል አዙሪት መልሶ እየከተታቸው ያለው ይኸው በይቅርታ ያልተወራረደው ታሪካችን ጥሎብን የሔደው ክፉ አበሳና ጠባሳ ይመስለኛል፡፡
እናም እንደ ፕ/ር ጌታቸው ያሉ ምሁራንና የዕድሜ ባለጠጋዎች የአንድ ወገን ታሪክን ብቻ በማጉላት ሳይሆን ሚዛናዊነት ባለው መልኩ ታሪካችንን በማቅረብ የሁላችንም የጋራ ቤታችን በሆነች ኢትዮጵያችን ተስማምተን፣ ተዋደን፣ ተፋቀርንና ተከባብረን የምንኖርባት አገር እንድትኖረን የታላቁን የሰላምና የይቅርታ አባት የኔልሰን ማንዴላን ዓይነት ሚና በመጫወት የትውልድ ባለውለታ ይሆኑ ዘንድ በእኔና በትውልዴ ስም አደራ እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!  nikodimos.wise7@gmail.com

የቁልቁለት መንገድ! – ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ


Temesgen
… በማስመሰል ታጥሮ መሆን በጠፋበት
ምን አገባኝ የሚል በተከማቸበት
የባይተዋር መንፈስ ከሞላ ባገሩ
ዘመኑን ማወቂያ ይሄ ነው ሚስጥሩ
ይሄን ጊዜ ጠርጥር እንደጠፋ ዘሩ፡፡
(ገጣሚ ደምሰው መርሻ/ያልታተመ)
አዎን፣ ገጣሚ ደምሰው እንዳለው እኔም በዚህ ዘመን “ዘሩ እንደጠፋ” አሊያም ሊጠፋ እንደተቃረበ እጠረጥራለሁ፡፡
ስለምን? ቢሉ …በኢትዮጵያችን ለህሊናው፣ ለሕዝብና ለሀገሩ የሚቆረቆር፣ የእውነት ተሟጋችና የሞራል ልዕልናን የተቀዳጀ ሙሉ ሰው ፈልጎ ማግኘት እጅግ አተካች ሆኗልና፡፡ የግል ጥቅም አሳዳጅ፣ አፋሽ-አጎንባሽ በሞላበት፣ እንደ ቴዎድሮስ ለሀገር ቤዛ መሆን፤ እንደ ግርማሜዎቹ እና ወርቅነህ የራስን ምቾት ወዲያ ጥሎ በጠገበ ሆድ ከወገን ጋር መራብና ከጎኑ መቆም፤ እንደ አቶ ሽፈራው ደሳለኝ አስፈሪ ሞት ከከበበው ሸለቆ ውስጥ በህይወት ለመውጣት ሲባል የጠላትን ጫማ ከመላስና ያላመኑበትን ተናግሮ ምህረት ከመጠየቅ ይልቅ በድፍረት ሞትን ፊት ለፊት መጋፈጥ ወይም ግንባርን ለአረር መስጠት እንደ ተረታ-ተረት ከተቆጠረ ዘመናት አልፏል (አቶ ሽፈራው ደሳለኝ ማን ናቸው? ለሚለኝ አንባቢዬ ‹‹የታኀሣሡ ግርግር እና መዘዙ›› የተሰኘውን የብርሃኑ አስረስ መጽሐፍ ገፅ 302ን እንዲያነብ እጋብዘዋለሁ) አሊያም ደግሞ የሰው ዘር በመሆን ብቻ የሚገኘውን የሞራል ልዕልና ከትውልድና ሀገር ጥቅም አኳያ ለማጠየቅ በዚህ አውድ ለማነሳው ተጠየቅ በአንፅሮ ለማፍታታት ይጠቅመኝ ዘንድ እኔው ራሴ እዚሁ ጠቅሼው አልፋለሁ፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጊዜ የድጋፍ ንግግር አድርጋችኋል በማለት በመንግስት ተይዘው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት አንዱ የሆኑት…›› ብለው ከአቶ ሽፈራው ደሳለኝ ጋር ከአስተዋወቁን በኋላ እንዲህ በማለት ትርክታቸውን ይቀጥላሉ፡- ‹‹…አቶ ሽፈራው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ተልከው ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ዳኛው ‹ሠርተሃል ለተባለው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ፣ አይደለህም?› ይላቸዋል፡፡ ‹የቱን ወንጀል?› ሲሉ አቶ ሽፈራው ዳኛውን ይጠይቃሉ፡፡ ዳኛው አቶ ሽፈራው ሠርተዋል የተባለውን የወንጀል ቃል ሊናገሩት አልወደዱም አልደፈሩምምና ‹አንተ የሠራኸውን?› ብለው ጠየቁ፡፡ አቶ ሽፈራው ‹እስቲ ወንጀል የተባለው ይነበብልኝ› ብለው አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄን ጊዜ ዳኛው ሳይወዱ ‹ይህን ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን፣ አወረደልን ማለትህን፤ …ለዚህ ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?› ይሏቸዋል፡፡ ‹የለም ተስተካክሎ ይጻፍልኝና እምነት ክህደቴን ልናገር› ይላሉ፡፡ ‹የለም በዚህ ላይ ጥፋተኛ ነኝ በል› ይሏቸዋል፡፡ ‹ትክክለኛ ቃሌ ይጻፍና ነው እንጂ እንዲሁ ጥፋተኛ ነኝ፤ አይደለሁም፤ አልልም› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹እሺ ምን ተብሎ ይስተካከል› ሲሏቸው፤ ‹ይህን የበሰበሰ የተጠረማመሰ አሮጌ ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን ነው ያልኩት› ሲሉ ዳኞቹ የተባለውን አልሰማንም ለማለት ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው ተደበቁ፡፡››
በዚህ ዘመን ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው እንደ ሰጎን አንገታቸውን ቀብረው በፍርሃት የሚኖሩ አድር፣ እበላ-ባይ፣ ፈሪ ሰዎች የአቶ ሽፈራውን ባመኑበት መቆም እንደ አጎል ጀብደኝነትና ሞኝነት ቢቆጥሩት አስገራሚ አይሆንም፡፡ የሆነው ሆኖ እንደ ብልህነት አሊያም ብልጥነት ተደርጎ የሚወሰደውን የአድርባይነት ‹‹ስልት›› ለማሳየት አንዲት ሀገርኛ ምሳሌ እዚህ ጋ ለንፅፅር ላቅርብና እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ለራሴ ጽሑፍ ‹‹F›› ከመስጠቴ በፊት ወደ አጀንዳዬ ልዝለቅ፡፡
ታሪኩ ዝናው በስፋት የናኘ ሽፍታ የመሸገበትን (ግዛቱ ያደረገ) ጥቅጥቅ ያለ ጫካ አቋርጦ ስለሚያልፍ መንገደኛ ገጠመኝ ነው፡፡ መንገደኛው ለሰዓታት ከተጓዘ በኋላ ድንገት ሽፍታው እጅ ይወድቅና ስንቅ የቋጠረበትን ስልቻ ጨምሮ ከላይ እስከታች ይበረበራል፤ ሆኖም ሰባራ ሳንቲም ሊያገኝበት ባለመቻሉ ከመጠን በላይ የተበሳጨው አያ ሽፍታ ሆዬ ንዴቱን ለማብረድ ሲል ‹‹ውዳሴ ዜማ አቅርብልኝ!›› በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጠዋል፤ በፍርሃት ነፍሱ እጉሮሮው የተወተፈችበት መንገደኛም ተንፈስ ብሎ ለመረጋጋት እየሞከረ እንዲህ ሲል አቀነቀነለት ይባላል፡-
‹‹አይኑ የተኳለ ጠላት የሚጋረፍ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ 2
ጠብ-መንጃ ገስጋሽ ጉብታ ተሻግሮ
ከዘብጥ የሚናደፍ
እንደሚካኤል ነህ ጠላትህም አይተርፍ!››
እነሆም የሀገሬ ምድር እንዲህ ባሉ ሀሞተ-ቢስ አወዳሾችና አስመሳዮች ተጥለቅልቃ እጆቿን ወደ ሰማይ ከዘረጋች (ሱባኤ ለመግባት) ሰነበተች፡፡ በርግጥም ከብዙሀኑ በተሻለ ማንሰላሰል ይሳናቸዋል ተብለው የማይታሰቡ ‹‹ምሁራን››ም ሆኑ ‹‹መንፈሳዊ››ነታቸው የበዛ የኃይማኖት መሪዎች በግል ጥቅመኝነት ታውረው ከስርዓቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን የጭቆና አገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም በሀሰት መስካሪነት የቅጥፈት ምላሳቸውን ሲያንበለብሉ መስማት ‹እግዚኦ› የሚያስብል አስደንጋጭ መናፍቅነት መሆኑ ቀርቶ እንደ ተራ ነጋዴ ንግግር፣ ተራ የዕለት ተዕለት አጋጣሚ ከሆነ ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ‹‹መንፈሳዊያን›› አባቶች በተከበረው ቤተ-መቅደስ ምኩራብ ላይ ከመእምናኑ ፊት ለፊት ቆመው ቃየልን ‹‹አቤል››፣ በርባንን ‹‹መሲህ›› በማለት ሲሰብኩም ለአመል እንኳ ድንቅፍ አያደርጋቸውም፤ ከግላዊ ጥቅማቸው አሻግረው የግፉአንን የስቃይ እሮሮ ማድመጥም ሆነ ለሌላው ማሳወቅ ጭራሹንም አይሞክሩትም፡፡ ‹‹ምሁራን›› ተብዬዎቹም አርቲስት ሰለሞን ተካልኝ ‹‹ውበት ከቅንድቡ የሚፈስ›› እንዲል፤ ‹አይኑ የተኳለ› እያሉ በሕፃናት ደም ሳይቀር የጨቀየውን ኢህአዴግ መራሹን መንግስት እንዴት እንዴት ‹ብፁእ› አድርገው የውዳሴ ከበሮ ሲመቱለት እንደሚያድሩ እዚህ ጋ ዘርዝሮ ለማቅረብ ማሰብ አባይን በጭልፋ አጋብቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ያለ ዕብደት ያስቆጥራል፡፡
ወጣም ወረደ እንዲህ አይነቱ የሞራል ዝቅጠት በትላንት ወይም በዛሬ የእድሜ ገደብ የሚለካ አለመሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፤ ምክንያቱም በነገሥታቱ የአገዛዝ ዘመን የጀመረና በጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅት እንደወረርሽኝ የተስፋፋ ስለመሆኑ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ‹‹ሀገር›› ለተሰኘ ማህተም መስዋዕት የሆኑትን አቡነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ታሪክ በታላቅ አክብሮት የሚዘክራቸውን ቀዳማይ አባቶችና እናቶችን ሳንዘነጋ ነው፡፡ እናም የሩቁን ትተን ከ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ወዲህ ያለውን እንኳ ብንመለከት ይህን መሰሉ ክስረት ዙሪያችንን ከቦ ሊውጠን የቀረው ስንዝር ታህል ርቀት ብቻ መሆኑን ለመረዳት የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁራን ትንታኔን ማገላበጥ አይጠይቅም፡፡ ያኔ ገና በለውጡ ማግስት ህወሓት እና ሻዕቢያ በአንድ አንቀልባ ካልታዘልን በሚሉበት የ‹‹ጫጉላ›› ዘመን፣ ከኤርትራ ምድር የወርቅ ጥርሳቸው ሳይቀር በጭካኔ ወልቆ ባዶ እጃቸውን የተባረሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በጉምቱው ምሁር ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ የተመራው አጣሪ ቡድን ‹‹ውሸት ነው! ይህ አይነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኤርትራ ይኖሩ
በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አልተፈፀመም!!›› በማለት አይኑን በጨው አጥቦ በድፍረት ሲያስተባብል፣ አንጀታችን እያረረ ‹‹ይሁና!›› ብለን በትዝብት ማለፋችን እውነት ቢሆንም፤ የዝምታችን ውስጠ-መልዕክት ያልገባው ፕሮፌሰሩ ግን ያረረው አንጀታችን ይበልጥ እርር ይል ዘንድ በተለመደው ቅጥፈቱ ታላቁ የዐድዋ ድል ባለቤትነትን ከሀገር ከፍታ፣ ቁልቁል ወደ ጎጥ ለማውረድ ያልፈነቀለው ቋጥኝ፣ ያልማሰው ስር አልነበረም (በነገራችን ላይ ህወሓት ዛሬም ከዐድዋ ድል ጀግኖች ጋር ጥቁር ደም እንደተቃባ በግላጭ የሚያመላክተው በዘንድሮው 118ኛው ክብረ በዓል ላይ የተስተዋለው አሳፋሪ ትእይንት ነው፡፡ ይኸውም በታሪካዊቷ ዐድዋ ከተማ በሚገኘው ሶሎዳ ተራራ ስር ‹ድሉን ለመዘከር› ከተሰቀሉት የእቴጌ ጣይቱ፣ የራስ አሉላ አባነጋ፣ የባልቻ አባነፍሶ እና የባሻ አውዓሎም ግዙፍ ምስሎች መሀል የተሸናፊው ሀገር ህዝብ ሳይቀር በድሉ ዕለት ሮማ በተሰኘው አደባባዩ ‹‹ቪቫ ምኒሊክ›› እያለ በታላቅ ጩኸት ያወደሰው የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ምስል አለመካተቱ ነው፡፡ …መቼም ይህ ለምን ሆነ? ብለን የክልሉን አስተዳዳሪ ጓድ አባይ ወልዱን ብንጠይቀው ‹‹በጦርነቱ ወቅት ምኒሊክ መሸሽ ጀምሮ ነበር›› የሚለውን ዝነኛ ህወሓታዊ ትርክት ገልብጦ፣ ‹‹በስራ መደራረብ በተፈጠረ ስህተት ነው›› ብሎ በክፍለ ዘመኑ ታላቅ ሽርደዳ አንጀታችንን ይበልጥ ድብን እንደሚያደርገው ቅንጣት ታህል አትጠራጠሩ)
ለማንኛውም እንደ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ያሉ በድሃው ሕዝብ ጥሪት የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዕድል ማግኘት የቻሉ በርካታ እበላ-ባይ ‹‹ምሁራን›› ስርዓቱ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚያምታታበትን ‹‹የሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት›› የፈረንጅ ጥናቶችን በጥራዝ-ነጠቅነት እያጣቀሱ ምክንያታዊ መስለው ሊያሳምኑን በከንቱ ብዙ ደክመዋል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሠራዊቱ ለባዕድ ሀገር ጥቅም ሲባል ሶማሊያን በወረረበት ወቅት አንዳንድ የዩንቨርስቲ መምህራን እና ‹‹የፖለቲካ ተንታኞች›› በመሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ ይሁነኝ ብለው ወደጎን ገፍተው አገዛዙ ቀን ከሌት ‹‹እመኑኝ!›› በሚል ጩኸት ያሰለቸንን ሰበብ፣ በጥናት እንደተረጋገጠ አስመስለው ለመተንተን ያደርጉት የነበረው እሽቅድምድም ሁሌም በሀዘን የምናስታውሰው ነው፡፡
የኃይማኖት መሪዎችም ምንም እንኳ በነቢብ የአገልግሎታቸው ዋጋ በፈጣሪ መንግስት መሆኑን ደጋግመው ቢነግሩንም፣ በሀልዮ የሚታየው የአሸርጋጅነት ግብራቸው ግን ምድራዊውን ጨቋኝ ስርዓት ደግፎ የሚይዝ ምሰሶና አቅፎ የሚያሞቅ ክንድ ከሆነ በርካታ አስርታት ተቆጥረዋል፡፡ የእስልምና እምነት የበላይ ወሳኝ አካል የሆነው መጅሊስ መእምናኑ ያነሱት ፍትሃዊው የመብት ጥያቄ ተቀልብሶ፣ ሕዝባዊ ውክልና የተሰጣቸው የኮሚቴ አባላት ለአስከፊው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተዳረጉበትን መንግስታዊ ሽብርተኝነት ለመሸፋፈን ከመተባበርም አልፎ ቅዱስ ቁራንን አዛብቶ እስከመጥቀስ መድረሱ በትዝብት ያሳለፍነው የትላንት ኩነት ነው፡፡ የክርስትና እምነት መሪዎችም በተመሳሳይ ሁናቴ የስርዓቱን የጭካኔ እርምጃዎች እንደ ቅዱስ ተግባር ለማፅደቅ ያልረጩት ጠበል፣ ያልጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አልነበረም፡፡ ሌላ ሌላውን እንኳን ትተን በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪ የአለማየሁ አቱምሳ ስርዓተ ቀብር ላይ ፓትርያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ‹ዲሞክራሲን ለማስፈን መስዋዕትነት የከፈለ፤ ሩጫውን የጨረሰ፤ ተጋድሎውን
በብቃትና በንቃት የተወጣ…› እያሉ አፋቸውን ሞልተው የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ ሀፍረት ብሎ ነገር ለቅፅበት እንኳን ዝር 3 አላለባቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በሰውየው ህልፈት እጃቸው እንዳለበት የሀሜት ወሬ የሚናፈስባቸው እነዚያ ጲላጦሳውያን ጓዶቹ እንዳሻቸው ቢያንቆለጳጵሱት መቼስ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው ብሎ በቸልታ ማለፍ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሰማዩን መንግስት ብቻ ያገለግሉ ዘንድ በቃሉ እንዲመላለሱ ግድ የሚላቸው ‹‹መንፈሳውያን››፣ እንዲያ የገዛ ወገኑን ‹‹ኦነግ!›› በሚል የሀሰት ውንጀላ በጥይት ሲደበድብና ሲያስደበድብ፤ መከራን በሕዝብ ላይ እንደምርጊት ሲለስን፤ አምባገነን ስርዓቱን በታማኝነት ሲያገለግል… ያለፈን ሰው ‹‹ዲሞክራት›› እያሉ በአደባባይ ማወደስ በቤተ-ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ራሱ የተነቀፈውን ለእግዚአብሔርና ለቄሳር ዕኩል መገዛትን እንደትክክለኛ ተግባር አምኖ መቀበል ነው ወደሚል ጠርዝ መገፋታችን አይቀርም፡፡
በግልባጩ በሁሉም እምነት ያሉ ‹‹መንፈሳዊ›› መሪዎች ስርዓቱ በድህረ-ምርጫ 97ም ሆነ በተከታዮቹ ዓመታት የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላትን እና ጋዜጠኞችን እንደ ጥጃ እያሰረ በግፍ ሲያሰቃይ ድርጊቱን ለመንቀፍም ሆነ ዘላቂ ዕርቅ እንዲወርድ ለመማለድ አንዳች ሙከራ አለማድረጋቸው በታሪክ ጥቁር መዝገብ በጉልህ ቀለማት ሰፍሮ የሚኖር ሀጢያታቸው ነው (የቅንጅት እስረኞችን ለማስፈታት የተሄደበት የ‹‹ሽምግልና›› መንገድ የአቶ መለስ ዜናዊ ቧልት ስለመሆኑ ከቶም ማንም ሊጠራጠረው አይችልምና እዚህ መጥቀሱ አስፈላጊ አይመስለኝም)
ሌላው የማሕበረሰባችን የሞራል እሴት በእጅጉ መዝቀጡን የሚያስረግጥልን ብዙሀኑ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተዘፈነበት ለመደነስ፣ በተደገሰበት አሳላፊ ለመሆን የሚያደርጉትን መገፋፋት ስናስተውል ነው፡፡ ስርዓቱ ከሚያራምደው ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› ርዕዮተ-አለም የተቀመረውን ‹‹ፌደራሊዝም አወቃቀር››ን ተንተርሶ ሀገሪቱን በዘውግ ከፋፍሎ እና በሕዝብ መካከል የጥርጣሬ መንፈስ አንብሮ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሙን በግጥምና ዜማ ማወደስ የእህል-ውሃ ጥያቄ ካደረጉት በርካታ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ እንዲህ አይነት የሙዚቃ ስራ በአንዳንድ ክልሎች መሬት የሚያሸልም ፈጣን አዋጪ አድርባይትመንት (ኢንቨስትመንት ላለማለት ነው) እስከ መሆን መድረሱ ከታፊና ነጋዴ አርቲስቶች በዘውጉ ዙሪያ ይረባረቡ ዘንድ ታላቅ ልማታዊ አብነት ሆኗቸዋል፡፡ ይህ ሁናቴም በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብን የንፁሃን መታጣት ከድንጋይ ወገራ የታደጋትን የኦሪቷ ዘማዊት ከማስመሰልም አልፎ እንደ ነገሥታቱ ዘመን የአዝማሪ ጨዋታ፤ የቤተ-መንግስቱ መዝናኛ እና አጀንዳ ማራገቢያነት እስከ መሆን ሞዴል ተሸላሚ አድርጓታል፡፡ ይሁንና ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ቴዎድሮስ
ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) የመሳሰሉ መክሊታቸውን እንደ ጉሊት ሽንኩርት ለሽያጭ ያላቀረቡ ከያኒያን፣ ደራሲያን፣ ገጣሚያን… የመኖራቸውን እውነታ ሳንዘነጋ፤ ሀገሪቱ ‹‹ሰው አይብቀልብሽ!›› ተብላ የተረገመች እስኪመስል ድረስ ብሔራዊ ጥቅም፣ ህሊና፣ ሞራል፣ እውነት የረከሱበትና የተዋረዱበት ዘመን ላይ መድረሷን የሚያስረግጡልን በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በብአዴኑ ካሳ ተክለብርሃን ፊት-አውራሪነት የሶማሌ ክልልን የጎበኙት አርቲስቶቻችን፣ ገና ድሮ ጆርጅ ኦርዌል ‹‹Animal Farm›› ብሎ በሰየመው መጽሐፉ ‹‹አራት እግር ጥሩ፤ ሁለት እግር መጥፎ›› እያሉ በመንጫጫት ስብሰባን ለመረበሽና ተቃውሞን ለማጨናገፍ አሳማው ናፖሊዮን እንዳሰለጠናቸው አይነት በጎች፤ ኢህአዴግ በጎጥ የካፋፈለውን ሕዝብ ‹‹በታሪኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን አንድ ሆኗል!!›› በማለት በሬ ወለደ የሀሰት ምስክርነታቸውን አምነን እንድንቀበል ለማድረግ ለሳምንታት ተንጫጭተው ሊያደነቁሩን ሞክረዋል፡፡ እነዚህ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የክልሉ ነዋሪዎች ገና ዛሬ (በኢህአዴግ እፁብ ድንቅ እና ፍትሀዊ አስተዳደር) ኢትዮጵያዊነት እንደተሰማቸው፤ ገና ዛሬ በፍቃደኝነት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ አስመስለው ለማሳመን የሄዱበት የቁልቁለት መንገድ አጥንት ድረስ በሚዘልቅ ሀዘን እንዳኮራመተን እነርሱም ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ ጉዳዩ ሆድ ሌላ፣ እውነት ሌላ ሆኖባቸው እንጂ፡፡ ግና፣ የቄሳሩ ጲላጦስም ‹‹እውነት ምንድር ነች?›› እንዲል፣ እውነት ለእነርሱ ዋጋዋ ስንት ነው? መቼም ከእውነት ይልቅ ግድ የሚሰጣቸው የሆድ ነገር ነው፤ እበላ አዳሪዎች ናቸውና፡፡
በጥቅሉ በኢትዮጵያችን ከምሁር እስከ ተርታው፤ ከጳጳሳት (ፓስተራት) እና ሼሆች እስከ መናፍቃውያን፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፤ ከጄነራል እስከ ወታደር፤ ከከያኒ እስከ ጽሑፍ ገልባጭ፤ ከቱጃር እስከ ጥሮ-ግሮ አዳሪ፤ ከመምህር እስከ ተማሪ… ስር የሰደደ አድርባይነት እና የሞራል ክስረት ለመንሰራፋቱ አይነተኛ ማሳያው አምባገነኑ ኢህአዴግ እንዲህ ሚሊዮኖችን ረግጦ እየጨፈለቀ፣ አስሮ እያንገላታ፣ ከሀገር እያሰደደና እየገደለ… ከሁለት አስርት በላይ መቆየት የመቻሉ ምስጢር ነው፡፡ ግና፣ የሕዝብን መከራ በማራዘም ኪስን ማደለብ፣ ግላዊ ፍላጎትን ማርካት ሁሌም አትራፊ ሊሆን እንደማይቻል መዘንጋት የለበትም፡፡ ማን ነበር ‹የተከፋፋለና አድርባይ ሕዝብን ከጭቆና ማላቀቅ፣ ሰማይን የማረስ ያህል አዳጋች ነው!› ያለው?
አዎን፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ በጉልበታም ስርዓታት የጭካኔ መዳፍም ሆነ በግላዊ ጥቅመኝነት እየተናዱ የመጡት የባህል እና የሞራል እሴቶች ትውልዱን ዛሬ ላይ ለደረሰበት አስከፊ ማሕበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው አሌ የማይባል ነው፡፡ ርግጥ ነው የችግሩ ስፋትና ጥልቀት እንደ ስርዓቱ የፖለቲካ ፍልስፍና በዘውግ የተከፋፈለ አይደለም፤ ብዙሀን እና ህዳጣን የሚል መስፈርትንም የተከተለ አይደለም፤ ኃይማኖታዊ መለያም የለውም፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አለቅጥ መንሰራፋቱ በግላጭ ይታያልና፡፡ ይህም ነው መፍትሔውን ስር ነቀል የማሕበራዊ አብዮት (ለውጥ) ብቻ እንዲሆን ያስገድደው፡፡
የቀደሙት ሁለት አብዮቶች በዋናነት ያነሷቸው የብሔር እና የመሬት ጥያቄ መክሸፋቸው (መቀልበሳቸው) ዛሬም ሶስተኛ አብዮትን የማይቀር ዕዳ አድርጎ የመውሰዱ ሁነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሥራ-አጥነት፣ ከነባሩ ባህል ማፈንገጥ፣ ሙስና፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ አክብሮትና 4 ተሰሚነት ያላቸው ታላላቆችን አለማደመጥ፣ አድርባይነት፣ ደንታቢስነት፣ ዶሮ ሳይጮኽ ደጋግሞ መክዳት፣ የ‹‹ስቀሎ፣ ስቀሎ…›› ሀሰተኛ ድምፅ መበራከት፣ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እና የመሳሳሉት ትውልድና ሀገር ገዳይ ደዌዎችን ለመፈወስ ከማሕበራዊ አብዮት ያነሰ መፍትሔ እንደሌለ ከተለያዩ ሀገራት ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በየትኛውም የዓለማችን ሀገራት የተከሰተ ሕዝባዊ አብዮት እንቅልፍ እንደሚነሳው በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለተከታታይ ቀናት ‹‹ተንታኝ›› ጭምር በመጋበዝ፣ ምስራቅ አውሮፓ ድረስ ተጉዞ የተሳካውን የዩክሬን አብዮት ከቀለም ጋር በማያያዝ ለማውገዝ ያቀረባቸው ፕሮግራሞች የፍርሃቱ መጠን አንዱ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላል፡፡ ግና፣ እውነት እውነት እልሀለሁ በመቶ ሺህ የሚቆጠር የታጠቀ ኃይል ቢሰለፍ፣ እልፍ አእላፍ ፊርማቶሪዎች በሕዝብ መሀል ቢሰገሰጉ፣ ሚሊዮናት ካድሬዎች ሀገር-ምድሩን ቢያጥለቀልቁ፤ አገዛዛዊ ጭቆና እና ማሕበራዊ ክስረት እስካለ ድረስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ፣ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ሊያመክነው የማይችል አብዮት መቀጣጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ይህንን ጽሑፍ ጄነራል መንግስቱ ነዋይ በተለምዶ ‹‹የታሕሳስ ግርግር›› እየተባለ የሚጠራውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፍ ተከትሎ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በሰጠው ቃል እቋጨዋለሁ፡-
‹‹…ዋ! ዋ! ዋ! ለእናንተም ለግዥአችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚደርስባችሁ መዓት የሚያሳቅቅ ይሆናል፡፡››
ትንቢቱ ከ13 ዓመት በኋላ ከእጥፍ በላይ መፈፀሙን ስናስታውስ፣ በጥቅመኝነት ስሌት ከስርዓቱ ጋር ተወዳጅተው የግፉአንን የመከራ ዕድሜ የሚያራዝሙ አድርባዮችም ሆኑ የአገዛዙ ልሂቃን ሕዝቡ ‹‹ሆ!›› ብሎ በአንድነት የተነሳ ዕለት ከመዓቱ ያመልጡ ዘንድ አይቻላቸውምና ዛሬውኑ ‹ንሰሀ ግቡ!› ብሎ ማሳሰብ ግድ ይላል፡፡ …ዋ! ዋ!! ዋ!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
March 16, 2014

Sunday, March 16, 2014

የስርዓቱ ደጋፊ የሆነችው ድምጻዊት ሃመልማል አባተ ለሁለተኛ ጊዜ ከአሜሪካ አፍራ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች


በአፍቃሬ ወያኔነቷ የምትታወቀው ድምጻዊት ሃመልማል አባተ አዲስ አልበሟን ለማስመረቅና የተለየያዩ ኮንሰርቶችን ለመሥራት ወደሰሜን አሜሪካ መጥታ የነበረ ቢሆንም በደረሰባት ቦይኮት በተመልካች እጦትና በፕሮሞተሮች መጥፋት አፍራ ወደ አዲስ አበባ መመለሷ ታወቀ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰብአዊ መብት ጥሶትና ንጹሃንን በእስር ቤት ያሰቃያል እየተባለ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የሚነገርለትን የወያኔ/ኢሕአዴግ ስርዓት በመደገፍ የምትታወቀው ድምጻዊት ሃመልማል አባተ በዋሽንግተን ዲሲ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶ በቨርጂኒያ ክሪስታል ከተማ በሂልተን ሆቴል የሲዲ ማስመረቂያ ኮንሰርት አዘጋጅታ 55 ሰዎች ብቻ የተገኙ ሲሆን አንድም አርቲስት በሲዲ ምርቃቱ ላይ አለመገኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በርካታ አርቲስቶች የሚገኙ እንደመሆኑ መጠን በሃመልማል አባተ ሲዲ ምርቃት ኮንሰርት ላይ አንድም አርቲስት አለመገኘቱ ኢቢኤስ የተባለው ቲቪ ሳይቀር እንዳስገረመው በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።



  (ሃመልማል በዲሲ አዘጋጅታቸው የነበረውና በተመልካች ድርቅ የተመታው የሲዲ ምርቃት ኮንሰርት ፍላየር ይህ ነበር)

ሃመልማል በወያኔ/ኢህአዴግ እየተረገጠ ያለውን ሰፊውን ሕዝብን ክዳ ለመሬት ቀሚው፣ ለመሬት ሻጩ፣ ለበዝባዡ፣ ለጨፍጫፊውና ለሰብአዊ መብት ረጋጩ ወያኔ ተቆርቋሪ ሆና በመቅረቧ ከጥቂት ዓመታት በፊት` በጀርመን ሃገር የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅታ ሕዝቡ ቦይኮት በማድረጉ 18 ሰዎች ብቻ የተገኙ ሲሆን ከ3 አመት በፊትም እንዲሁ ወደ ሚኒሶታ በመምጣት ኮንሰርት አዘጋጅታ ከ12 ያነሰ ሰው ብቻ በመገኘት በተመልካች ድርቅ ተመትታ ወደ ሃገሯ ተመልሳለች፤ ያሉት የመረጃ ምንጮች ሃመልማል ከስርዓቱ ጋር ያላት የጥቅም ግንኙነት የተረሳላት መስሎ ወደ አሜሪካ በድጋሚ ብትመጣም በዋሽንግተን ዲሲ 55 ሰዎች ተግኝተው አሳፍረዋታል። በዲሲ ኮንሰርት ሲዘጋጅ እስከ 5 ሺህ ሰው እንደሚገባ ልብ ይሏል።


ሃመልማል በዳላስ ከተማ በፋሲል ደመወዝ ስም በመጠቀም፤ (ሕዝቡ የፋሲል ደመውዝ አድናቂ በመሆኑና እርሱን ተከትሎ በመግባቱ) በኮንሰርቱ ላይ ቁጥሩ ጨመር ያለ ሰው ቢገባም በሎስ አንጀለስ ከተማ የቀድሞ ባለቤቷ እና የልጇ አባት በሚያስተዳድረው ሮዝሊን የሲዲ ምርቃትና ኮንሰርት ብታዘጋጅም በተመሳሳይ ቦይኮት ተደርጋ በተመልካች ድርቅ ተመትታለች። በዚህም ሞራሏ የተሰበረው ሃመልማል ከስህተቷ ተምራ ወደ ሕዝብ ከመመለስ ይልቅ ወደ ሃገር ቤት በመመለስ ነገሩን ለማብረድ ብትሞክርም እንዲህ ያለው ቦይኮትና በየከተማው ያሉ ፕሮሞተሮች ያለመጋበዝ ትግል ታግዞበት ወደ ሃገሯ ልትመለስ በቅታለች።

ዲያስፖራው ከወያኔ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ድምጻዊያንን ቦይኮት ማድረጉ የሚያስመሰግን ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ይህ ጉዳይ በርትቶ ሊቀጥል እንደሚገባው አስታውቀዋል። እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የስርዓቱ ደጋፊ የሆኑ አርቲስቶች በሃገር ቤት ከወያኔ ጋር በመሞዳሞድ የሚያገኙት ጥቅም ውጭ ሲመጡ ሊያገኙ አይገባም ይላሉ። ዲያስፖራው ሃገሩን የሚያከብረውን አርቲስት እንደሚያክብረው ሁሉ ከወያኔ ጋር ለሆዱ ያደረውን ድምጻዊም በማግለል ተመልካች አልባ ማድረግ እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ከሃመልማል አባተ ውጭ ነዋይ ደበበ፣ ሰለሞን ተካልኝና የመሳሰሉት ድምጻዊያን በዲያስፖራው ኪሳራ እንደደረሰባቸው ይታወሳል።

ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Wednesday, March 12, 2014

“ልጄ አካለ ስንኩል ነው እንጂ አእምሮ ስንኩል አይደለም”

አባትነት በተግባር - የዓመቱ ምርጥ አባት!

father 2


አካለ ስንኩል የሆነውን ልጁን በትከሻው በመሸከም በየቀኑ 14.4ኪሜ (9ማይል) በእግሩ በመጓዝ ለሚያመላልሰው አባት መንግሥት በአቅራቢያው ቤት እንደሚሰጠው ተነገረ፡፡
በደቡብ ምዕራብ የቻይና ግዛት የሚኖረው የአርባ አመቱ አባት አካለ ስንኩል የሆነውን የ12ዓመት ልጁን ት/ቤት ለማስገባት ካለው የጸና እምነት የተነሳ ልጁ ራሱን ችሎ መራመድ የማይችል በመሆኑ ለመጓጓዣ ባዘጋጀው ለየት ያለ ቅርጫት በመሸከም ከመስከረም ወር ጀምሮ እያመላለሰው መሆኑን የቻይናን ዜና ምንጮችን ጠቅሶ ዴይሊ ሜል ዘግቧል፡፡
ልጁ የሦስት ዓመት ህጻን በነበረበት ወቅት ከወላጅ እናቱ ጋር የተለያየው አባት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ልጁን ብቻውን ያሳደገው ሲሆን እናቱ ብትለይም ልጁን ብቻውን ለማሳደግ በመወሰን መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል የዚያኑ ጊዜ መወሰኑን ተናግሯል፡፡ ልጁ እያደገ ሲመጣ ት/ቤት ለማስገባት በአካባቢው ያሉትን ሲጠይቅ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ከአካባቢው ርቆ ወደሚገኝ ት/ቤት ለማስገባት ይወስናል፡፡ ሆኖም ት/ቤቱ ከሚኖርበት ገጠር 7.2ኪሜ (4.5ማይል) የሚርቅ በመሆኑ ልጁን ራሱ ተሸክሞ ለማመላለስ በመወሰን ከመስከረም ወር ጀምሮ እያመላለሰው እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
father 6“ልጄ አካለ ስንኩል ነው እንጂ አእምሮ ስንኩል አይደለም” የሚለው አባት በእርሱ ግምት እስካሁን ከ2500ኪሜ በላይ ተጉዟል፡፡ ዕለታዊ ሁኔታውን ሲገልጽም ጠዋት 11ሠዓት ላይ በመነሳት ለልጁ ቁርስ ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም 7.2ኪሜ (4.5ማይል) ልጁን ተሸክሞ ይሄዳል፡፡ ት/ቤት አድርሶ ወዲያው ወደቤቱ በመመለስ ለኑሮው የሚሆነውን ዕለታዊ ሥራውን ሲያከናውን ይቆያል፡፡ ከሰዓት በኋላም የመጣበትን 7.2ኪሜ እንደገና በመመለስ ልጁን ከት/ቤት ያመጣል፡፡ በዚህም በቀን 18ኪሜ ከቤቱ ት/ቤት እንደሚመላለስ ይናገራል፡፡
በሚያደርገው ደስተኛ እንደሆነ የተናገው አባት ልጁ በት/ቤት ውጤቱ ከክፍሉ አንደኛ መሆኑ እንደሚያኮራው ይናገራል፡፡ “ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ አውቃለሁ፤ ሕልሜ ኮሌጅ እንዲገባ ነው” በማለት በልጁ ያለውን ተስፋ ይናገራል፡፡
በአካባቢው የሚገኝ የዜና ዘጋቢ ጉዳዩን ይፋ ካደረገው በኋላ የአካባቢው የመንግሥት መስተዳድር በልጁ ት/ቤት አቅራቢያ ቤት እንደሚከራይለት ለአባትየውና ለልጁ ቃል ገብቷል፡፡ ት/ቤቱም ወደፊት ለእንደነዚህ ዓይነት ልጆች የሚሆን የማደሪያ ቦታ ለማመቻቸት ማሰቡን ገልጾዋል፡፡
father 3father 4father 5father 1
http://www.goolgule.com/father-of-the-year/