-ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉትን ፖሊሶች መለየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል
በቅርቡ የቀድሞውን የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ወርቅነህ ገበየሁን የተኩት የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል አቶ አሰፋ በዩ፣ ችሎት በመድፈር ወንጀል በተጠረጠሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ምክንያት ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
በጥር ወር መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ቅጥር ግቢ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ ሆነው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔርን ችሎት በመድፈርና ዳኛን በማመነጫጨቅ ወንጀል፣ የስድስት ወራት የእስራት ቅጣት ተወስኖባቸው ከነበሩት ኢንስፔክተር ሀብታሙ አሰፋ ሐጎስ ጋር የነበሩ፣ ነገር ግን በወቅቱ ሳይቀርቡ የቀሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን፣ ተቋሙ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀጠሮ መሠረት የፌዴራል ፖሊስ ነገረ ፈጅ ኮማንደር ደረጄ ወንድሙ የቀረቡ ቢሆንም፣ ችሎት በመድፈር ወንጀል ከተጠረጠሩ የፖሊስ አባላት መካከል የትኛው ተጠርጣሪ ድርጊቱን እንደፈጸመ መለየት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
ፖሊሶቹ 15 ሲሆኑ የችሎት መድፈር ተግባር ፈጽመዋል በተባለበት ዕለት የስፖርት ዜና እየተከታተሉ እንደነበር ኮማንደሩ ለችሎቱ አስረድተው፣ አንዱ በሕመም ምክንያት ያልቀረበ ቢሆንም 14 አባላትን ማቅረባቸውንም አክለዋል፡፡ ‹‹ነበሩ የተባሉትን ሁሉ ስላቀረብን ፍርድ ቤቱ አጣርቶ ዕርምጃ ይውሰድ ወይም ይቅርታ ያድርግልን፤›› በማለትም ኮማንደር ደረጄ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሕግ መተርጎምና ዳኝነት መስጠት መሆኑን ያስረዳው ፍርድ ቤቱ፣ ወንጀልን የመመርመር ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለፌዴራል ፖሊስ በመሆኑ፣ ሥልጣኑን በመጠቀም ተጠርጣሪውን መርምሮ ማወቅና ማቅረብ እንዳለበት አስረድቷል፡፡ አንድን ውስብስብ የወንጀል ድርጊት ሕጉን ተከትሎ በመመርመርና በማጣራት ወደ ሕግ ማቅረብ እንደሚችል የታመነበት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቱን እንዲጠብቁ ከተላኩ የፖሊስ አባላት መካከል የተጠረጠረን አባል መለየት እንዳልቻለና ፍርድ ቤቱ እንዲያጣራ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ለፍርድ ቤት የተሰጠው ሥልጣን ሕግ መተርጎምና የዳኝነት ሥራ መሥራት እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ችሎት በመድፈር ወንጀል ተጠርጥሮ በሚቀርብ ማንኛውም አካል ላይ ፍርድ ቤቱ ተገቢውን የሕግ ትርጉም በመስጠት ተገቢውን ቅጣት መጣል እንጂ፣ ይቅርታ የሚያደርግ ተቋም አለመሆኑንም አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም አጥፊው ሳይለይ በጅምላ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ ማድረግ እንደማይቻልም አክሏል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ችሎት በመድፈር ወንጀል የተጠረጠረውን አባል መለየት አለመቻሉን በማሳወቁ፣ ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ እልባት ለመስጠት የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል አቶ አሰፋ በዩ ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ባዘዘው መሠረት ቀርበው አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተር ጄነራሉ አቶ አሰፋ ችሎት በመድፈር የተጠረጠሩ ፖሊሶችን መለየት ስላለመቻሉ ሲያስረዱ፣ ችሎቱ ትዕዛዝ ካስተላለፈበት ቀን ጀምሮ ለማጣራትና ለመለየት የሞከሩ ቢሆንም፣ ‹‹ከ15 የፖሊስ አባላት መካከል የትኛው አባል ድርጊቱን እንደፈጸመ ማወቅ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ወደ ተቋሙ (ፌዴራል ፖሊስ) መልሶት አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ ወይም ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥ አቶ አሰፋ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ እልባት ለመስጠት በመቅጠር ዋና ዳይሬክተር ጄነራሉን ከምሥጋና ጋር አሰናብቷል፡፡
No comments:
Post a Comment