Tuesday, February 4, 2014

በልጅ ፍቅር የተዋጀው የነፃነት ትግል (ከንግስት ወንዲፍራው)

(የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሃፊ)

ልጄ ኤልዳና ሆይ ሰሞኑን ምን ያህል እንደምናፍቅሽ አውቃለሁ፡፡ እቤቴ ሆኜ ላንቺ ለውዷ ልጄ የናትነት ፍቅር መገለጫ የሆነውን የጡት ማጥባት ስራዬ ላይ ያልተገኘሁት ከጡቱ ከምታገኚው ነገር በላይ የሆነ ላንቺ የሚያስፈልግሽ ነገር ስላለ ነው፡፡ የዚህ ከምንም ነገር በላይ የሆነው ነገር ሰሙ ሃገር ይባላል፡፡Freedom: the quality or state of being free
ቀድሞ ሃገርሽ በአያቶችሽ እና በቅድመ-አያቶችሽ ደምና አጥንት ታፍራ እና ተከብራ ብትኖርም ዛሬ ግን ወያኔ ይሉት ከሃዲ እና አጉራሽ እጅ ነካሽ የሆነው ቡድን መንግስት ነኝ ብሎ ይቺን ከኔ ከምታገኚው ነገር በላይ የሆነችውን ሃገርሽን እንደ ዳቦ እየቆራረሳት በመሆኑ ይህንን ለመቃወም ካንቺ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቄ እንድገኝ ተገድጃለሁ፡፡
ሃገር ማለት ልጄ ነገ አንገትሽን ቀና አድርገሽ የምትራመጂበት የክብር መድረክሽ ማለት ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ እንደልብሽ የነፃነት እስትንፋስሽን እየተነፈስሽ ከፍ ስትዪ የምትቦርቂበት፣ ስታድጊ ጎጆሽን የምትቀልሺበት እንዲሁም ስታረጂም የምትሞረከዢበት የክብር ቤትሽ ማለት ነው፡፡ ይህ የክብር ቤትሽ ሙሉ ይሆን ዘንድ አንድ ነፃነት የሚባል ነገር ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ማለት ትንሽዬዋ ቤትሽ ደምቃ ለመታየት መብራት እንደሚያስፈልጋት ሁላ እቺ ሃገርሽም ነፃነት ይሉት ነገር ያስፈልጋታል፡፡
ያለ ነፃነት ሃገር ጨለማ ነች፡፡ እኔ እናትሽ ደግሞ ምስጋና ለአባትሽ ይሁንና ለእናንተ ለውድ ልጆቼ ጨለማ አላወርስም፡፡ ጨለማ ሃገር ከማውረስ ደሃ ሃገር ማውረስ ይሻላል፡፡ በነፃነት የጠጡት ውሃ ከወተት በላይ ይጣፍጣል፡፡
ልጄ ሁሉ ኢትዮጰያዊ እናት እናትሽ እንዲሁም ሁሉ ኢትዮጰያዊ አባት አባትሽ ነው፡፡ ሰዎች አንቺ እና እኔ ወይም አባትሽ በደም ተሳስራችኋል ይሉሽ ይሆናል ልክ ናቸው፡፡ ግን እኛ ከመላው ኢትዮጵያው ደም የተቀዳን እና አጥንት የተፈለጥን ፍጡራን ስለሆንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ካንቺ ጋር በቀጥታ በደም የተሳሰረ ነው፡፡ ይህንን ትስስር ማንም አይፈታውም ወይም አይቆርጠውም፡፡ አንቺም ብትሆኚ…፡፡ ዛሬ ካንቺ ርቀው ከሚገኙት ኤርትራዊያንም ጋር ቢሆን በደም የተሳሰርሽ ነሽ፡፡
ልጄ እኔ እና አባትሽ ከምናስፈልግሽ በላይ ሃገር እና ነፃነት ያስፈልግሻል፡፡ ሚሊዮን እናት፣ ሚሊዮን አባት እንዲሁም እጅግ ብዙ ሚሊዮን ወንድም እና እህቶች አሉልሽ፡፡ እነዚህን ሁላ የወለደችልሽ ግን አንድ ናት–ኢትዮጵያ፡፡ ከምንም በላይ እቺ እናት ታስፈልግሻለች፡፡ በእኔ እና በአባትሽ ከምትኮሪው በላይ በኢትዮጵያዊነትሽ ኩሪ፡፡
የሚያኮራ ማንነት፣ ታሪክ እና ጀግንነት አለሽ፡፡ ኩራትሽ ከሜዳ ወድቆ የተገኘ ሳይሆን የተከፈለበት ኩራት ነው፡፡ ከዋጋዎች ሁሉ በላይ የሆነው የሰው ልጅ ህይወት የተከፈለበት ኩራት፡፡
ሚኒሊክ በጀግንነቱ ያቀናው፣ ዩሃንስ አንገቱን ያስቀላለት፣ ቴዎድሮስ እራሱን የሰዋለት የታፈረ እና የተከበረ ማንነት አለሽ፡፡ እኔም ዛሬ በታላቋ ጎንደር ከተማ የተገኘሁ ይህንን አፈር የተነሰነሰበትን ማንነትሽን፣ በደም የተዋጀው ነፃነትሽ እና በጀግኖች አጥንት የታጠረ ዳር ድንበርሽን ለማስከበር ከሚደረገው ሰፊ እና ሰላማዊ ትግል አካል የሆነውን የሃገርሽ እና የጎረቤታችን ሱዳን ድንበር ጉዳይ ነው፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10910/

No comments:

Post a Comment